ከየፈርጁ

                                ፍቅር በበር ሲገባ፣ ክብር በጓሮ ይወጣል፡፡
                                       
ከፈሪሳውያንም አንድ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ፡፡ እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፣ ሽቱ የሞላበት የአልባጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች፡፡ 


በስተኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፣ በራስ ጠጉርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች፡፡የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ፣ ይህስ ነቢይ ቢሆን፣ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደሆነች እንዴትስ እንደነበረች ባወቀ ነበር፣ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ፡፡ 


ኢየሱስም መልሶ ስምዖን ሆይ የምነግርህ ነገር አለኝ አለው፡፡ እርሱም፡- መምህር ሆይ፣ ተናገር አለ፡፡ ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ፡፡ የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው፡፡ እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው? ስምዖን መልሶ፡- ብዙ የተወለት ይመስለኛል አለ፡፡ እርሱም በእውነት ፈረድህ አለው፡፡ 


ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፡- ይህቺን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች፣ በጠጉርዋም አበሰች፡፡ አንተ አልሳምኸኝም (ጉንጬን እንኳ) እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም፡፡ አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፣ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች፡፡ ስለዚህ እልሃለሁ፣ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል፡፡


 እርስዋንም፡- ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት፡፡ ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው፡- ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማነው? ይሉ ጀመር፡፡ ሴቲቱንም፡- እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት፡፡

የሉቃስ ወንጌል 6፣36-50
(በቅንፍ ውስጥ ያለው የእኔ ነው ለመጨመር አስቤ ግን አይደለም፡፡)


                                   ንጉሥ ቀንድ አበቀሉ!
በድሮ ጊዜ አንድ ባለሟል (በአሁኑ ዘመን አጠራር የፕሬዚዳንት አሊያም የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ እንደማለት) ነበር ይባላል፡፡ ሥራው ንጉሡን ማማከር ነውና ስለንጉሡ የማያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ውስጣቸውን ሳይቀር አብጠርጥሮ ያውቃል፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ከእንቅልፉ በማለዳ ነቅቶ፣ በሰላም ያሳደርከኝ በሰላም አውለኝ ብሎ በማለዳ ወደ ሥራው ሲሄድ፣ ባየው ያልተለመደ ነገር ጠላታችሁ ይደንግጥ ክው ብሎ ይቀራል፡፡ ንጉሡ ቀንድ አብቅለው ነበር፡፡ “Pause” የሆነ ያህልም ላፍታ ዓይኑን በንጉሡ ላይ ተክሎ ከቆየ በኋላ ወደ አዕምሮው ሲመለስ ንጉሡ ‹‹አሁን የተመለከትከውን ነገር በፍፁም ለማንም ትንፍሽ ማለት የለብህም!›› ብለው ማስጠንቀቂያ አዘል ትዕዛዝ ይሰጡታል፡፡ እሺ ብሎ ከንጉሡ እልፍኝ ቢወጣም እንግዳው ጉዳይ ግን ውስጡ ታምቆ ካልወጣሁ እያለ አስቸገረው፡፡ በመጀመርያ ለሚስቱ ሊነግራት አሰበና የንጉሡን ትዕዛዝ ፈራ፡፡ ታዲያ ግራ ቢገባውና እንግዳው ነገርም ገንፍሎ ሊወጣ መሆኑን ሲረዳ መሬት ቆፈረና አፉን ቀብሮ ‹‹ንጉሥ ቀንድ አበቀሉ›› ብሎ ለመሬት ተናገረ ይባላል፡፡ ሰው ሐሳቡን በነፃነት ይገልጽና ይናገር ዘንድ ካፈኑት ለግዑዝ አካል እንኳ መናገሩ የማይቀር እውነት ነው፡፡ በባል የምትጨቆን ሚስት አንተ ሰማይ ፍረደኝ፤ አንቺ ምድር ፍረጂኝ እንድትል፡፡ 
                                                              መስታወትህን ተጠቀምበት!
አንድ ጊዜ አንድ ሰው የቤት ሠራተኛ ሊቀጥር ወደ ደላላ ሄደ ይባላል፡፡ ለደላላውም ‹‹አሪፍ የቤት ሠራተኛ እፈልጋለሁ ታገኝልኛለህ?›› ይለዋል፡፡ ቀልጣፋው ደላላም፣ ‹‹ምን ዓይነት ሠራተኛ? ቀይ፣ ጥቁር፣ አጭር፣ ረጅም፣ ወፍራም፣ ቀጭን…›› እያለ እንደ ቱባ ክር አንደበቱን መተርተር ሲጀምር፣ ሰውየው፣ ‹‹እንደዚያ ማለቴ አይደለም፤ ባለሙያ፣ ታዛዥ፣ ጨዋ፣ የማትናገር፣ የማትጋገር፣ እኔ የምላትን ብቻ የምትሰማ ሠራተኛ ነው የምፈልገው፡፡ ስለ መልኳ እንኳ ብዙም ግዴለኝም፤›› ይለዋል፡፡
‹‹ታዲያ ምን ችግር አለ ሞልቷል›› በማለት ደላላው አንዲት ሠራተኛ ከመቅጽበት ይዞ ከተፍ ይልና፣ ‹‹እነሆ ጌታዬ የማትናገር የማትጋገር ጨዋ ሠራተኛ›› ብሎ ያቀርብለታል፡፡ ሰውየውም ለደላላው ኮሚሽኑን ከፍሎ ሠራተኛዋን ወደቤቱ ይዞ ሄደ፡፡ ሠራተኛዋም ሥራዋን ጀመረች፡፡ በመካከላቸው ከአለቃና ከሎሌ ወይም ከአዛዥና ከታዛዥ ውጪ አንዳችም ሌላ ግንኙነት የለም፡፡ ይኼን አድርጊ እሺ፣ ያን አታድርጊ እሺ፡፡ ይኼን ሥሪ፣ ያን አትሥሪ፣ እሺ፤ በዚህ ግቢ፣ በዚያ ውጪ እሺ፡፡ እንዲህ ነው ነገራቸው፡፡ ታዲያ ሰውዬው ብዙ ጊዜ ሥራ ሲሄድ ወይ ቁልፉን ረስቶ ይሄዳል፣ ወይ ኮቱን ገልብጦ ይለብሳል፣ ወይ አንድ እግር ካልሲ አድርጎ ይሄዳል፡፡ ቢሮ ሲደርስ ነው ልብ የሚለው፡፡
ሠራተኛዋ ብዙ ጊዜ ስህተቱን ልትነግረው እየፈለገች፡፡ ‹‹ጋ…ጋሼ የሸሚዝዎን አዝራር ባግባቡ አልቆለፉትም›› ገላምጧት ይወጣል፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ፣ ‹‹ጋሼ የኮትዎ ኮሌታ ተወላግዷል›› ፀጥ ብሏት ይወጣል፡፡ ‹‹ጋሼ ሁለት የግራ እግር ጫማ ተጫምተዋል›› እንዳልሰማት ሆኖ ያልፋል፡፡ ሰዓት ካልረፈደም ያስተካክለዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን አስተያየቷ አይመቸውም፡፡ አስተዳዳሪዋ ምግብ ከማብሰልና ልብስ ከማጠብ ውጪ ሌላ ቃላት ባትተነፍስ ደስ ይለዋል፡፡ ሠራተኛዋም ይኼ ነገር ስለገባት ‹‹ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባበትም›› ብላ በዝምታዋ ቀጠለች፡፡ በኋላ ግን ሰውየው ለብዙ ጊዜ ‹‹ፐርሰናሊቲ››ን ባለመጠበቅ፣ በዝርክርክነትና ግዴለሽነት በመሥሪያ ቤቱ ተገምግሞ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው፣ ችግሩን አስተዋለ፡፡ መስታወቱን እንዳልተጠቀመበትም ተረዳ፡፡ ለካንስ ተማረችም አልተማረችም፣ ሠለጠነችም አልሠለጠነችም፣ ሠራተኛው መስታወቱ ነበረች፡፡


                                              እንደራሴዎቻችን (?)

እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ብዙውን ጊዜ ኢቴቪን የምከፍተው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ የተባለ ሰሞን ነው፡፡ ለምን ቢሉ የሚናገሯቸው በዋዛ የተዋዙት ቁምነገሮች ይመስጡኛልና ነው፡፡ የእውነት ለመናገር ጠቅላይ ሚንስትራችን አንደበተ ርዕቱ ናቸው፡፡ ቅመም ንግግራቸው  የባተሌውን ቀልብ ሳይቀር የሚስብ ነው፡፡ የሰሞኑንም የፓርላማ ንግግራቸውን ለመስማት ከቴሌቪዥኔ ፊት ተሰይሜያለሁ፡፡ 
እንግዲህ ብዙ ጊዜ ሌሎች አካላት ሪፖርት ሲያቀርቡ የፓርላማውን ድባብ መመልከት መንፈስን ዘና ሚያደርግ ነገር አለው፡፡ እንዴት?. . . ቢሉ ‹‹ካሜራ ማኑ›› ተሳስቶ አሊያም ሆነ ብሎ በቴሌቪዥናችን መስኮት የሚያስቃኘን አንዳንድ ግርም የሚሉ ትዕይንቶች አሉና፡፡
 ለምሳሌ አንዳንዴ አንደኛው የተከበሩ ‹‹እንደራሴ›› ካንገታቸው ጎንበስ ደግሞ ቀና ሲሉ ያሳየናል፡፡ ታዲያ በሪፖርቱ መስማማታቸውን ከመግለጽ ውጪ ጭንቅላትን ማነቃነቅ ምኑ ላይ ነው ክፋቱ ይባል ይሆናል፡፡ እውነት ነው፤ ክፋትማ የለውም፡፡ ችግሩ እኚያ የተከበሩ ‹‹እንደራሴ›› ጭንቅላታቸውን እንዲያ መወዝወዛቸው እርስዎ እንዳሰቡት በሪፖርቱ መስማማታቸውን ለመግለጽ ሳይሆን፣ እንደ የቁርጥ ቀን ባላጋራ በድንገት ከመጣባቸው እንቅልፍ ጋር ትንቅንቅ ገጥመው መሆኑ ነው እንጂ፡፡ (በእርግጥ የወከሉት ሕዝብ ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳ እንጂ በእንቅልፍ የሚያዳፋ ባይሆንም)
ብዙ ጊዜ ግን ሪፖርቱን የሚያቀርቡት የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ መላው የተከበረው የፓርላማ ዕድምተኛ ማለፊያ ቡና እንደጠጣ ጎበዝ የተነቃቃ ይሆንና በፓርላማው ሳቅና ደስታ ይሆናል፡፡ 


                                         ዕጣ ፈንታ?
ልጅ እግሩ አባወራ አንዲት ሚስትና ለሥራ ያልበቁ አራት ልጆች አሉት፡፡ በአንድ የግል ክሊኒክ ውስጥ በጥበቃ ሥራ ያገለግላል፡፡ እፍኝ ከማትሞላ ደመወዝም ስድስት ራሱን ያስተዳድራል፡፡ አምላክ ያሳይዎ በአዲስ አበባ ኑሮ፣ ስድስት ራሱን በዚህች ደመወዝ ሲመራ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉሮሯቸውን ደፍነው ከሚያድሩበት ጊዜ ይልቅ ጦም ማደሩ ሲያይል፣ አውጥቶና አውርዶ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ውሳኔውንም ለትዳር አጋሩ አሳወቀ፤ የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ሚስትና የልጆቹን እናት ወደ ዓረብ አገር መላክ፡፡

 ለጊዜው መለያየቱ ቅስም ቢሰብርም፣ ያለ አጋር መክረሙ አጥንት ድረስ ዘልቆ ቢሰማም፣ ያለ እናት ኦና ቤት ማደሩ አንጀት ድረስ ዘልቆ ቢያምም፣ ጦም ውሎ ከማደር ይሻላልና ተስማሙ፡፡ የነገን ወፍራም ዳቦ እያለሙ፡፡ እንባ ተራጭተውም ተሰነባበቱ፡፡ አዎ ተበድሮና ተለቅቶ፣ ግማሽ አካሉን ወደ ዓረብ አገር ላከ ምስኪን ወንድማችን፡፡
ዳሩ ምን ይሆናል እንዳለመውና እንዳሰበው በግርድና የተገኘውን ዶላር ሳይሆን የልጅ እግሩ አባወራ ዕጣ ፈንታ ሬሳዋን መታቀፍ ነበር፡፡ ግማሽ አካሉ አገር ለቃ በሄደች በጥቂት ጊዜ ውስጥ በሄደችበት ጢያራ አስከሬኗ ተላከ፡፡ ‹‹የግፍ ግፍ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉም ሁለቱም ኩላሊቶቿ በቦታቸው አልነበሩም፡፡

አቤት ባይ በሌለበት ዓለም ላይ እንደመሆኑ ለማን አቤት እንደሚል ለጊዜው ያወቀው ነገር የለም፡፡ የአራት ልጆቹን እናት አስከሬን የሙጥኝ ብሎ ለያዥ ለገናዥ እስኪያስቸግር ድረስ ተንሰቅስቆ ከማልቀስ በቀር፡፡ ‹‹ወንድ ልጅ ብቻውን ነው የሚያለቅስ፤›› እንዲሉ እኚያ በሕይወት የተለዩን ሎሬት፣ ባለታሪካችንም የአጋሩ ትዝታ አንዴ በሥራ ቦታው፣ ሌላ ጊዜ ከማጀቱ፣ እንዲሁም በሕፃናቱ ብቻ በሄደበት ሁሉ እንደ ጥላ እየተከተለው መቆሚያና መቀመጫ አሳጥቶታል፡፡



         ያልተባነነበት “ኢንቨስትመንት

 አንድ ጋዜጣ ላይ ነው አንዱ የገጠመውን እንዲህ ሲል ያሰፈረው፡፡ ‹‹ከታክሲ ስወርድ አንዲት አዛውንት ‹‹የኔቢጤ›› አየሁና ከታክሲ የተመለሰልኝን የመልስ ዝርዝር ሳንቲሞች ሰጠኋቸው፤ በኋላም አንድ ትንሽ ልጅ እየሮጠ ቀረበኝና …››
‹‹ጋሼ፣ ጋሼ ሁለት ጊዜ ተሸወዱ›› አለኝ፤
ግራ እየገባኝ፣ ‹‹እንዴት ?. . . ምን ማለት ነው?›› ብለው፣
‹‹ገንዘብዎን ሁለት ጊዜ ተበሉዋ›› ይለኛል፤
‹‹እኮ እንዴት?››
‹‹አንድም ለታክሲው ከፍለው፣ ደግሞም መልሱን ለየኔቢጤዋ ሰጥተው፤›› ሲለኝ፣
‹‹ታዲያ መሸወዴ የቱ ጋ ነው?›› ማለት፤
‹‹የተሳፈሩበት ሚኒባስ ታክሲኮ የራሳቸው ነው፤››
‹‹እኮ የማ?››
‹‹የየኔቢጤዋ የራሳቸው ነዋ፤››
‹‹እንዴት ሊሆን ይችላል?››

ባለታሪኩ በማመንና ባለማመን መካከል ሆኖ ወደ ጉዳዩ ከመሄድ በቀር ያደረገው አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡
አሁንማ ግራውንድ ፕላስና አፓርታማም እያላቸው አከራይተው የሚለምኑ ሰዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ ታዲያ ይኼን ወሬ ያቀበለኝ ሰው፣
‹‹ምክንያቱ ሌላ ነው›› ነው ያለኝ፡፡
‹‹ምንድነው ምክንያቱ ?››
‹‹ሱስ››
‹‹ምን?››
ምንም እንኳ በልመና ያለፈላቸውና እንደ መኪናና ቤት የገዙ ‹‹ነዳያን›› ቢኖሩም ቅሉ እንደ ሀሺሽ፣ ጫትና ሲጋራ ሁሉ ልመናም ሱስ ስለሆነባቸው ሥራዬ ብለው፣ ሐሩሩና ብርዱ  እየገረፋቸው መለመንን የሙጥኝ ያሉ ብዙዎች ናቸው፡፡

ይሁንና ልመና አለቅጥ በመስፋፋቱ ምክንያት የከተማችን ነዋሪዎችና የውጭ ዜጎች በእጅጉ ተማረዋል፡፡ በቦሌ መስመር ብቻ እነርሱ ካጥር ጥግ ቁጭ ብለው ሕፃናት ልጆቻቸውን በልመና ‹‹ሥራ›› (ለመሆኑ ልመና ሥራ ነው እንዴ ?… ባንድ ወቅት ከትልቁ የመንግሥት ሚዲያ ‹‹በልመና ሥራ የተሰማሩ ዜጎች›› ሲል ስለሰማሁ ነው ቃሏን መጠቀሜ) ያሰማሩ እናቶች ቤት ይቁጠራቸው፡፡ አሁን አሁንማ ጤነኛ የሚመስለው፣ ሠርቶ መብላት የሚችለው ሁሉ መለመን ‹‹ፋሽን›› የሆነ ይመስላል፡፡

ጡት ያልጣለ ሕፃን በጉያቸው ይዘው በተሞላቀቀ አማርኛ ‹‹ነፍሱ ዳቦ መግዢያ ሙላልኝ›› የሚሉ ወጣት ሴቶችንም ማየት የዘወትር ገጠመኝ ነው፡፡
ታዲያ ‹‹ኧረ ይኼ ነገር ወዴት እየወሰደን ነው?›› ብዬ የጠየቅሁት አንድ ወዳጄ፣ ‹‹እባክህ ተወኝ ልመና የዘመኑ ያልተበላበት ኢንቨስትመንት መሆኑን ስላላወቅክ ነው፤›› ሲል ፈገግ አሰኝቶኛል፡፡

በዚህ ርዕስ ዙሪያ ሳስብ ሁሌ ሆዴን የሚበላኝ ነገር፣ ገና ከአሁኑ ትናንሽ እጆቻቸውን ወዳላፊ አግዳሚው በመዘርጋት የልመናን ሀሁ የተማሩት ጡት ከጣሉ አንድ ሐሙስ የሆናቸው ሕፃናት ናቸው፡፡ በተኮላተፈ አንደበታቸው ‹‹አባባ አባባ ለታቦ መግሺያ. . .›› ብለው፣ በልመና የሕይወትን አቡጊዳ ከጀመሩ መመረቂያቸው ምን ይሆን? ኧረ ይኼ ነገር መቋጫው የቱጋ ነው?
 በአንድ ወቅት ልመናን ታሪክ ለማድረግ በሚል ቆርጠው በመነሳት ቁጥሩን በውል የማላውቀው በርካታ ገንዘብ የሰበሰቡት ሰዎችስ ወዴት ገቡ? ያነገቡት ዓላማስ ከምን ደረሰ?
‹‹ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለው ዝነኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መቼ ይሆን የሚፈጸመው? በማለት ሳስብ ግራ ይገባኛል፡፡ ምክንያቱም በእኔ ዕድሜ ስለ አገራችን የተባለውና እየሆነ ያለው ለየቅል ስለሆነ፡፡ ሐውልታቸው ከአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ሕንፃ ቅጥር ግቢ የቆመላቸው ክዋሜ ንክሩማህ እንኳ ይኼንን ጥቅስ ቃል በቃል ከተናገሩት ግማሽ ምዕት አለፈኮ፡፡

                                          የሚያስጨንቅ ፍቅር
አንዲት የሦሥት ልጆች እናት የሆነች ዘመድ አለችኝ፤ ጥሎባት ዘመዶቿን አለቅጥ የምትወድ፡፡ የሷ መውደድ ከሌላው ለየት ያለ ነው፡፡ በቃ አለ አይደል ሳይጠይቋት ቢቀሩ ሥልክ መታ፣ አሊያም ባካል ተገኝታ ‹‹ምን አስቀይሜህ ነው ያልጠየከኝ፣ ያስለመድከኝን ነገር የነፈግኸኝ፣ እኔኮ እወድሀለሁ፣ ባለቤቴም ስላንተ አንስቶ አያባራም፣ ለልጆቼማ ካፋቸው ውስጥ እንዳለ ከረሜላ ነህ፣ . . .›› እያለች የፍቅር መወድሷን የምታዥጎደጉድ፡፡ በልቼ የጠገብኩ፣ ጠጥቼ የረካሁ፣ ለብሼ ያልሞቀኝ፣ ምቾት አንገላቶኝ ሳለ፣ ያልደላኝ የማይመስላት፡፡

 አንዳች ነገር አድርጌላት እንዳይመስላችሁ፤ ሻሽ እንኳ ገዝቼላት አላውቅም በቃ ዝም ብላ ትወደኛለች፡፡ እንዲህ አይነቱን ፍቅር ፈረንጆቹ /Unconditional love/ ይሉታል፡፡ በእከከኝ ልከክልህ /Tit for Tat/ ላይ ያልተመሠረተ ወረት የማያውቀው ፍቅር፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ከርስዎ ዘመድም ውስጥ ቢፈልጉ አያጡም፡፡ እርስዎ ለነርሱ ልዩ ሰው ነዎ፡፡ አንዳንዴ መላእክት የሆኑ ሁሉ ሊመስልዎ ይችላል፡፡ አይድረስብዎ እንጂ እንኳንስ ክፉው ደርሶብዎ፤ በበጎው ጊዜውም ሁሌ ፍቅራቸው ትኩስ ነው፣ አያረጅም፡፡ አገኙ፣ ያው፤ አጡ፣ ያው፤ አማሩ፣ ያው፣ አስቀሙ ያው፤ ያው ነው ፍቅራቸው፡፡ አቤት ደስ ሲል እንዲህ አይነት ሰብዕና!  . .  .  ይታደሏል እንጂ አይታገሉም ይሏል ይሄኔ ነው፡፡

ታዲያ እንዲህ አይነት ፍቅር እኔ በበኩሌ ጭንቅ ይለኛል፡፡ ለምን ቢሉ ባለዕዳ ያደርገኛልና ነው፡፡ የፍቅር ባለ ዕዳ፡፡ በተወደድኩኝ ልክ ካልወደድኩ የፍቅር ባለ ዕዳ ነኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በተሰፈረልኝ ቁና ሙሉ ፍቅር ከፊሉን እንኳ መመለስ የማልችል ምስኪን መሆኔን ሳስበው ምን ዓይነት መቅመቆ ብጋት ነው እንደነዚያ ሰዎች ቅንጣት ፍቅር የሚጣባኝ? ብዬ አስባለሁ፡፡ የዕዳ አይነት አውቃለሁ የፍቅር ዕዳን ያህል ግን ከባድ አላየሁም፡፡ የፍቅር ዕዳ ያለበት ሰው ነፍሱን ከሞትጋ እንኳ ያወራርዳል፡፡



                                            ዱቤ ከልል


በድሮ ጊዜ ‹‹ዱቤ ከልል›› የሚሉት ኮፍያ አደራረግ አለ አሉ፡፡ ኮፍያን ከወደ ግንባር ዝቅ አድርጎ አይንን በመከለል ከአበዳሪ ዕይታ የመሰወር ጥበብ ነው፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን የዘመኑ ‹‹ፍሪኪዎች›› ይጠቀሙበታል፡፡ ከዕዳቸው ለመሸሽ ሳይሆን ለ‹‹መፈረክ›› ወይም ለመዘነጥ፡፡ 







                                             የወገን እዳ

ገና ከናት አገሩ መለየቱ ነበር፤ ዙሪያ ገባው ሁሉ ነጭ በሆነበት በባዕድ ምድር፤ እሱን የሚመስሉ ሁለት ሰዎች ያይና ፊቱ ሁሉ ጥርስ በጥርስ ሆኖ፡-
‹‹በጣም ደስ ይላል እናንተን በማግኘቴ ኢትዮጵያውያን ናችሁ አይደል?›› ይላቸዋል፡፡ ሰዎቹም ለጊዜው ስሙን በማልጠቅሰውና ያገራችን ብሔር ከሆነው አንዱን ጠርተው ‹‹የለም፤ እኛ እንዲህ ነን›› ብለውታል በእንግሊዝኛ፡፡



                                               ሕጋዊ ሽፍቶች (?)
ወደ ባሕር ዳር እየሄድን ነው፡፡ በመኪናችን ውስጥ ሶስት ትርፍ ሰው አለ። የሆነ ቦታ ላይ ትራፊክ ፖሊስ ከች አለብን። እንዲህ ነው ያደረገው። ያው ትራፊክ ፖሊስ የተባለ ሁሉ እንደሚያደርገው በመጀመርያ መኪናውን አስቆመ፣ ቀጠለናም በረዳቱ በኩል እየመጣና (በነገራችን ላይ መኪናችን ረዳት አልነበረውም። ይልቁንስ ትራፊክ ፖሊስ በመጣ ቁጥር እንደ ወያላ «የሚያክት» አንድ ነጠላጋቢ የለበሰ ባላገር ነበረ፤ የደሀ ቦርጭ በመሰለ ድቡሉቡል የቆዳ ወንበር ላይ የተቀመጠ። 


ይህ ሰው በጣም ነበር ያሳዘነኝ፤ ምክንያቱም ባህርዳር ድረስ ሁለት መቶ ሃያ ብሩን ሆጨጭ አርጎ ከፍሏል፤ ግና እንኳንስ በወጉ እንደ ሰው ወንበር ይዞ መቀመጫውን ሊያሳርፍ ይቅርና አንዴ ሲወርድ አንዴ ሲወጣ ፣ በር ሲከፍት ደግሞ ሲዘጋ፣ በጣፋጭ የሰሜን ለዛው «እህ ጌታው» ሲል ባህርዳር ዘልቋል።) ወደ ትራፊክ ፖሊሱ ልመለስ (የቱጋ ነበረ ያቆምኩት?) አዎ በረዳቱ በኩል እየመጣና  በር አስከፍቶ ሰው እየቆጠረ እንደቀደሙት ስለትርፍ ሰው አንዳችም ባይገደውም፣ ታርጋውን አየት እያደረገ
«በቃ ይሄ የታርጋ ነገር መደበኛ ሆነ አይደለ?» ሲል
ሾፌሩ ሁለተኛው ትራፊክ ፖሊስ የሰጠውን የቅጣት ወረቀት ጸጉሩን እያከከ ያሳየዋል።
«ምንድነው መውጫ አልያዝክም እንዴ?»
«አረ ጋለብክ ብሎኝ ነው»
«ራዳር ይዞ ነበር?»
«ሜዳ ላይ ነው ያለው ወላሂ የለበሰው ልብስ እንኳ ከውስጥ የለበስከው አይነት ነው እንዲያውም ገጭቼው ነበረ።»
«ገጭቸው ነበረ?... ገላግለሀው ነበራ»
ይሄኔ ተሳፋሪው በሳቅ አውካካ።
አብሮኝ ይጓዝ የነበረውም ወዳጄ
«ድሮ ድሮ መኪናን በየመንገዱ ሚያስቆሙ ሽፍቶች ነበሩ አሁን ግን ዘመን ተቀየረና ትራፊኮች ሆነዋል።» ቢል ወይ ግሩም ብዬ አፌን በጄ ጫንኩ።


                                   ሕይወት በሯጩ አይን
የመወዳደሪያው ስፍራ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ሰዎች ተጨናንቋል። ታዋቂና ስመጥር ሯጮች፣ ስፖርቱን የሚወዱ ሯጮች፣ ለመሮጥ ብለው የሚሮጡ ሯጮች፣ የድሉን አክሊል ለመሸለም የሚሮጡ ሯጮች፣ ለተሳትፎ የሚሮጡ ሯጮች፣ ከታዋቂ አትሌቶች ጎን እየሮጡ ካሜራ አይን ውስጥ ለመግባት የሚሮጡ ሰዎች… ብቻ ሁሉም አሉ።

የውድድሩ ፊሽካ ተነፋ፤ ህዝበ ዓዳም እየተግተለተለ ይሮጥ ገባ፤ ማራቶኑ ተጀመረ። ግማሽ ኪሎ ሜትሩም ሳይጠናቀቅ ከአራቱ ሁለት እጅ ያህሉ ወደየት እንደገቡ ታጡ። ገና አርባ አንድ ኪ.ሜ. ያህል ይቀራል። አሁንም ጥቂት እንደተሮጠ ቀርቶ ከነበረው ሲሶው ያህል ረገፈና በጣት የሚቆጠሩ ሯጮች ብቻ ቀሩ።

በመጨረሻው ዙርም አንድ ሰው እጆቹን እንደ ክንፍ ዘርግቶ ክሩን ሲበጥስ ተስተዋለ። ይህን ሰው ቀርቤም ሳስተውለው አርባ ሁለት ኪሎ ሜትሯን ጥጥት አርጎ ገና ምንም ያልሮጠ መስሎ ይታያል። ደግሞም «ለእኔ የሕይወት ትርጉሟ የሚፈታልኝ በንዲህ አይነት ወቅት ነው።» የሚል ይመስላል።


                                   ሕይወት በሐኪሙ እይታ
ሰዎች ስለሕይወት ያላችሁ ትርጉም እንዴት ነው? ተብለን ስንጠየቅ እንደየማንነታችን የምናስቀምጠው የሕይወት ፍልስፍና ይኖረናል። ምንም እንኳ  የሁላችንም አመለካከት ለየቅል ቢሆንም ቅሉ፣ ማጠቃለያችን አንድ ያደርገንና በኖህ መርከብ እንደነበሩት እንስሶች ያዛምደናል። 
እኔም በተለያዩ የህ/ሰብ ክፍሎች የሕይወት ትርጉም ስትቃኝ ምን እንደምትመስል ለማወቅ ፈልጌ በያጋጣሚው የማገኛቸውን በተለያየ ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ላናግር ሞክሬያለሁ፤ እስቲ አብረን እያንዳንዳቸው እንደየግብራቸው የሚሉትን እንስማ።
በመጀመርያ ያገኘኋቸው ቀዶሐኪም ናቸው። የሕይወት ትርጉም በርስዎ እይታ እንዴት ነው? ብዬ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ መልስ ከመስጠታቸው በፊት ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል ይዘውኝ ሄዱ፤ እዚያም ስንደርስ የሙያ ባልደረቦቻቸው አንድ የቀዶ ጥገና ህክምና ሊያደርጉ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ተመለከትኩ። ሁሉም ጌሾ ቀለም ያለው የመለያ ልብሳቸውን ለብሰው አፋቸውንና አፍንጫቸውን ሸፍነውና ጓንታቸውን አጥልቀው ቀጥሎ ሊያደርጉ ያሉትን ነገር ሊያደርጉ አንድ ነገር የሚጠብቁ ይመስላሉ።

እኔም እንደ ሐኪሞቹ ከለበስሁ በኋላ የሚሆነውን ለማየት እችል ዘንድ ዕድል አገኘሁ። በቀዶ ጥገናው ጠረጴዛ ላይ ህመምተኛው ተኝቷል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም በፍጹም ጸጥታ ስራው ተጀመረ። ህመምተኛው ማደንዘዣ ተወጋ፤ ከዚያም አንደኛው ሐኪም የመቅደጃ ቢላቸውን ይዘው ወደህመምተኛው ራቁት ሰውነት ተጠጉ። ቢላዋቸውንም ልቡ አካባቢ ሲያሳርፉ አይኖቼን ጨፈንሁ። ጥቂት ቆይቼም ስገልጥ አካባቢው በደም ጨቅይቶ ኖሮ ረዳት ሐኪሞቹ ደሙን እያደራረቁና አስፈላጊውን ነገር እያደረጉ ናቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላም የህመምተኛው ልብ እንደ ኳስ እየነጠረች ታየችኝ። ከዚያም በኋላ ቀጥሎ ያለውን ነገር እመለከት ዘንድ አቅም ስላነሰኝ በድጋሚ አይኖቼን ከደንሁ።
«ለእኛ ቀዶሐኪሞች የሕይወት ትርጉም በቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ይጎላል። አየህ የሕይወትና የሞት ሽረት የሚታየው የሐኪሙ ቢላዋ በህመምተኛው ሰውነት ውስጥ ዘልቆ ከገባበት ሰዓት አንስቶ ነው። የሰውዬውም ዕጣ ፈንታ ያኔ ይወሰናል። የሕይወቱ ገመድ ወይ ይረዝማል አሊያም ያጥራል። ያኔ ነው እንግዲህ የህይወት ምንነት፣ የመኖር አስፈላጊነት፣ ምን ያህል እንደሆነ የምረዳው።» በማለት ሐኪሙ ከቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ እንደወጣን መነጽራቸውን በማውለቅ አይናቸውን ያሻሹ ጀመር። 




                                 ሕይወት በአትክልተኛው ዕይታ
«ሰማዩ ከምድር ሲላቀቅ፣ የወፎች መንጫጫትን ተከትሎ ከአድማስ ባሻገር ማለዳ ጀምበር ፍንጥቅ ስትል ከመኝታዬ በመነሳት የአትክልት መሣሪያዎቼን  ይዤ ወደ አትክልቶቹ ስፍራ እሄዳለሁ። እዚያ ስደርስም…» አሉኝና አትክልተኛው እንደ ኤደን ገነት የሚያምረውን የአትክልት ስፍራ ዙሪያ ገባውን ገረመሙት። ከዚያም ፈገግ እያሉ…«እዚያ ስደርስ ታዲያ ሕይወት ሕይወት ይለኛል መኖር መኖር ይሸተኛል። አፈሩን እየኮተኮትሁ አረሙን ስነቅል፣ አበባ እየተከልሁ የተጠሙትን ሳጠጣ፣ የወደቁትን እየደገፍሁ የተሰበሩትን ሳቀና የሕይወትን ጣፋጭ ትርጉም፣ የመኖሬን እውነት እወደዋለሁ። እነዚህ የምታያቸው የዛፍ ችግኞች የእኔ ህይወት እየለመለመች ትሄድ ዘንድ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ለእኔ አንዲት ችግኝና  የሰው ሕይወት ተመሳሳይ ናቸው። ሕይወት ደግሞ ካለ እጽዋት ባዶ ናት።» በማለት ችርችም ብሎ ወደበቀለው ጥድ መቀሳቸውን እያንቀጫቀጩ ተለዩኝ።



        ሕይወት በመምህሩ አይን
ምንም ፊደል ያልተጻፈበት ጠመኔ ይዤ ወደ ማስተምርበት ክፍል ስገባ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ አስተውላለሁ። አዲስን ነገር ሊቀበል በተዘጋጀ ዓዕምሮ ውስጥ አንዳች ነገር ማስቀመጥ፣ መጻፍ ወይም ማተም። እንዲያ የሚሆነው ታዲያ ጠመኔዋን ከጥቁር ሠሌዳ ጋር በማገናኘት ለማስተማር አሀዱ ስል ነው። ጠመኔዋ አንድ ፊደል፣ ሁለት ፊደል እያለች ቃል ከቃል፣ ሐረግ ከሐረግ፣ ከዚያ ዓረፍተ ነገር በመጨረሻም ምንባብን ስትጽፍ፣ እየተፈረፈረች እየቦነነች እያለቀች ትመጣለች። ታዲያ ጠመኔዋ ስታልቅ ለተማሪዎቼ እንግዳ ነገር አስገንዝባ አንዳች ነገር አስጨብጣ መስዋዕት ሆና ነው።

ሕይወትም እንደ ጥቁር ሰሌዳ በምመስላት ዓለም ላይ የራሷን ፊደል ከትባ፣ የራሷን ቃላትና ምንባብ መስርታ ትከስማለች። በሰሌዳው ላይ ያለ ጽሁፍ ግቡን ከመታ በኋላ በማጥፊያ ለሌላኛው ትምህርት ይጻፍበት ዘንድ እንደሚጠፋ ሁሉ ሕይወትም አንዴ የምድር ላይ ቆይታዋን ካሳካች በኋላ በሞት ትጠፋለች። ሌላ አዲስ ሕይወት መጻፍ /መፈጠር/ አሊያም መተካት አለበትና፤ ታዲያ ሕይወትን ስመለከታት በሁለት ነገር እመስላታለሁ የመጀመርያው ሊጻፍበት እንደተዘጋጀ፣ ወይም እየተጻፈባት እንዳለ፣ አሊያም እንዳለቀ ጠመኔ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በጥቁር ሰሌዳ ላይ እንደተጻፈ ምንባብ። ትርጉሟም የሚገባኝ በጠመኔዬ የዘራሁት ዘር በቅሎ ሲያፈራና የቀለም ልጆቼ ግማሹ ሐኪም፣ ግማሹ መሐንዲስ፣ ከፊሉ ያገር መሪ ወዘተ ሲሆን ነው። 



                                 ሕይወት በዋናተኛው ዐይን
ከጠራው ሰማይ ስር የጠራ ውሀ አለ። በውሀው ዳር ካለው አሸዋ ላይ ወንዶችና ሴቶች ፣ ህጻናትና አዋቂዎች በየፈርጁ ጸሐይ እየሞቁ ሲታዩ ከፊሎቹ ደግሞ እየዋኙ ነው። ከነርሱ እንደ አንዱ ለመሆን ፈለግሁና ወደነበሩበት አመራሁ። በዚህን ጊዜም በባህሩ ውስጥ እየዋኙ ከነበሩት ሰዎች አካባቢ ግርግርና ሁካታ ተፈጠረ። ሁናቴውንም ለማወቅ እየሮጥኩ ሄድኩ።

«አሁንኮ አጠገቤ በሰላም እየዋኘ ነበረ፤ ሳያውቀው ወደ ጥልቁ ወርዶ ነው የሰመጠው።» ይላል አንድ ሰው የልቅሶ ቃና ባለው ድምጽ። በርግጥ የሚያለቅሰው ሰውዬ ፊቱ በእምባ ይታጠብ አይታጠብ አያስታውቅም እየዋኘ ስለነበረ።
ከጥቂት ጊዜም በኋላ አንድ ሰው የሰመጠውን ሰው ተሸክሞ እየዋኘ ወደ ዳር ሲመጣ ታየ። ከውሀ እንደ ወጣም ሰጥሞ የነበረውን ሰው በጀርባው እንዲንጋለል ካደረገው በኋላ የጠጣውን ውሀ ያስተፋው ጀመር። ሰውየውም ቀስ በቀስ ነፍስ እየዘራ መጣና በመጨረሻ ሊድን ቻለ። እኔም የኋላ ኋላ ነፍስ ሰውዬው ነፍስ አድን አሊያም life Saver መሆኑን ተረዳሁ።

የሕይወት ትርጉም ለእርሱ በውቅያኖስ ላይ እንደምትጓዝ መርከብ ናት። መርከቧ ረጅም ርቀት ስትጓዝ የምታርፍበት ወደብ ለመድረስ በማዕበል፣ በአውሎ ነፋስና፣ በግዙፍ አሳ ነባሪዎች እንደምትፈተን ሁሉ፣ ሕይወትም በጎዳናዋ ላይ አያሌ ፈታኝ ነገሮች ይገጥሟታል። ቢሆንም ግን በውሀ ውስጥ የሰመጠችን ሕይወት ደርሶ ከሞት እንደ ማስመለጥ ያለ አስደሳች ነገር የለም። 
                         
                                   ሕይወት በአንጥረኛው ዐይን
ጥሬው ብረት ገና መደበኛ ቅርጹን ሳይዝ ወደ እሳቱ ይገባል። አንጥረኛውም ከሰል በማቀጣጠያው ውስጥ ከጨመረ በኋላ ወናፉን ያናፋዋል፤ ወናፉ ከሰሉን ያፍመዋል፤ ከሰሉም ብረቱን ያግመዋል፤ ያኔም አንጥረኛው የጋመውን ብረት በሜንጦ ይይዝና ያወጣዋል፤ አውጥቶም ከጠፍጣው መቀጥቀጫ ብረት ላይ ያስቀምጠዋል። ክንደ ብርቱው አንጥረኛም በከባድ መዶሻ እየቀጠቀጠ የሚፈልገውን መሳሪያ ቅርጽ ይይዝ ዘንድ ግድ ይለዋል። የኋላ ኋላም ያ ጉማጅና ቅርጸ ቢስ የነበረ ጥሬ ብረት ከብዙ መቀጥቀጥ በኋላ ማለፊያ ማረሻ፣ ወይም ዶማ፣ ካልሆነም ቢላዋ ወይም ደግሞ አስገራሚ ፋስ ይሆናል።
አየህ ጥሬው ብረት የሚፈለግበትን ዓይነትና ቅርጽ ይይዝ ዘንድ በእሳት ውስጥ ማለፍ የግድ እንደሚሆንበት ሁሉ፣ ህይወትም በመከራ እሳት ትፈተናለች። በችግር መዶሻም እየተቀጠቀጠች ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ትጓዛለች። እናም ለኔ አንድ ተራ ብረትን በእሳት ፈትኖ ቢላዋን አሊያም ድግር ማውጣትን ያህል የመሰለ ታላቅ እርካታ የለም። የህይወቴ ህይወት እኩል ይሆናል እሳት ሲደመር የጋመ ብረት አበቃሁ። 


   ሕይወት በወንጀል መርማሪው ዐይን
በምድራችን ላይ በየዕለቱ መልካቸውንና ዘዴያቸውን እየቀያየሩ ብዙ ወንጀሎች ይሰራሉ። አንዳንዶቹ የወንጀል ዓይነቶች ቀላልና ብዙም የማያለፉ ይሆኑና ፋናቸውን ለማግኘት ጊዜ የማይወስድ ይሆናል። ሌሎቹ ደግሞ እጅግ ውስብስብ ከመሆናቸው የተነሳ ቀንድና ጭራቸውን ለመያዝ አንድ የተወታተበ ልቃቂትን የማስተካከል ያህል ይሆናል።

በተለያዩ የወንጀል ምርምር ዑደቶች ውስጥ የአንድን ውትብትብ ወንጀል ጭራ ለመያዝ አያሌ ቀንና ሌሊቶች፣ ብሎም ብርቱ ጥረትና ትዕግስት ይጠይቃል። ነገር ግን እውነት ምናልባት ታማ ባልጋዋ ላይ ትውል ይሆናል እንጂ ፈጽሞ ስለማትሞት ፈለግዋን አሽትቶ ለማግኘት ብርቱ ወንጀል መርማሪ መሆን ያስፈልጋል። ለወንጀል መርማሪዎች እንደተጎለጎለ ማግ የሆነን ውል አልባ ወንጀል እንደ መፍታት የሚያረካቸው ነገር የለም። 


                                 ሕይወት በመቃብር ቆፋሪው ዐይን
ነገር ዓለሙ ጸጥ ረጭ ባለበት ትልቅ የመቃብር ስፍራ ውስጥ ነኝ።  ጸጥታው የሚባላ አፍ ያለው ይመስላል። ግቢውን ካጣበቡት መቃብሮች ጋራ ተዳምሮ ዝምታው ነፍሴን አራዳት።

አንዳንድ ጊዜ በሐውልቶች ላይ የሚጻፉ የህይወት ታሪኮችን ማንበብ ያስደስተኛልና፣ እያነበብሁ በሁለት ልብ ሆኜ ስራመድም፣ ከቅርብ ርቀት ድም… ድም… ድም…. የሚል ድምጽ ይሰማኝ ጀመር። ስፈራ ስቸር አይኖቼን ድምጹ ከሚመጣበት አቅጣጫ ስወረውር አንድ አካሉ የፈረጠመ ሰው መቃብር እየቆፈረ ነው። በቀስታም ወዳለበት ሳመራ ዱክን ሰምቶ ኖሮ ቀና ብሎ ተመለከተኝ። በፊቱ ላይ የተንቸረፈፈው ላቡ ትናንሽ ቦዮች እየሰራ በመጨረሻም አንድ ትልቅ ቦይ በመስራት ይቀላቀልና በአገጩ ጫፍ እየተንጠባጠበ ከመቃብር ጉድጓድ ውስጠ ወጥቶ በተቆለለው አፈር ይመጠጣል።

«የሕይወት ትርጉሟ  ከአስክሬንና የመቃብር ጉድጓድ ጋር የተያያዘ ነው።» አለኝና ጨወታውን ጀመረልኝ።«የሕይወቴ ድውር የተጠነጠነው ከሙታኖች መንደር ነው። እነዚህ ሁሉ መቃብሮችም የእኔ እንጀራ የተጋገረባቸው ናቸው። ህይወቴ የምትረካውና መኖሬን የምወደውም ጥሩና ያማረ የሬሳ ጉድጓድ የቆፈርኩ ዕለት ነው። 

                     ሕይወት በእሳት አደጋ ተከላካዩ ዐይን
በሰፊው ግቢ ውስጥ ቀያዮቹ የእሳት አደጋ መከላከያ መኪኖች ግምባራቸውን ወደ ግቢው መውጫ አፍጥጠው እንደ ኃያል ሠራዊት በተጠንቀቅ ቆመዋል። ግቢውን እንደ ዘለቅሁም በመደዳ ከሚታዩት ቢሮዎች ውስጥ ወደ አንደኛው ጎራ አልኩ። ቢጫ የእሳት መከላከያ ቱታ የለበሱና ቆብ የደፉ የድርጅቱ ዋነኛ ሠራተኞችም እየተሯሯጡ መኪኖቹ ላይ መሳፈር ጀመሩ። በወቅቱ ሁሉም በጥድፍያ ላይ ስለሆኑ እኔን ከቁብ ቆጥሮኝ የሚያናግረኝ ሰው አልነበረምና ዝም ብዬ ምክንያቱን ለማወቅ ወደ አንደኛው መኪና ሳመራ አንደኛው ሠራተኛ እየተጣደፈ «ፈጠን ብለህ ግባና እንሂድ» አለኝ። ሳላመነታም ገባሁ። ወዲያውኑ እኔ ከነበርኩበት ጋራ ሁለት መኪኖች በከፍተኛ ፍጥነት የአደጋ ኡኡታቸውን እያሰሙ ከግቢው ተፈተለኩ።

ከአደጋው ስፍራም ስንደርስ አካባቢው በጭስ ጉም ታፍኖ ነገር ሁሉ አይታይም ነበር። ወዲያውም መኪኖቹና ሠራተኞቹ ወደተግባራቸው ሲሰማሩ እኔ ጥጌን ይዤ እየሆነ ያለውን እመለከት ገባሁ።

ብዙ ጩኸትና ዋይታ ከአካባቢው ይጎርፋል። እንደ ጀማሪ ፍቅረኞች ተቃቅፈው የተሰሩ ቤቶች በእሳት እየጋዩ እንዳሉም አሁን ግልጽ እየሆነልኝ መጣ። ከረጅም ሰዓት የማጥፋት ትግል በኋላም እሳቱ ጠፍቶ ሁሉም መረጋጋት ሲጀምር ወደ አንደኛው የእሳት አደጋ ሠራተኛ ቀርቤ የተለመደ ጥያቄየኝ ሰነዘርኩለት።

እጅግ ተዳክሞ ስለነበረ ብዙ ሊለኝ አልቻለም። ብቻ «አሁን ካየኸው ሌላ የምልህ የለኝም። ሕይወት ከመቼውም የበለጠ በንደዚህ አይነት ሰዓት ትርጉሟ ፍንትው ብሎ ይታይሀል። በተለይማ ከእሳት ላንቃ ውስጥ አንዲትን ነፍስ መንጭቀህ ስታወጣ፣ ጣፋጭነቷ ምን ያህል እንደሆነ ትገነዘባለህ።» ብሎኝ እዚያው እንደተገተርኩ ወደ መኪኖቹ አመራ።  


      ሕይወት በጋዜጠኛው ዐይን


በመጨረሻም እኔ ራሴን ጠየቅሁ። ለእኔስ ለጸሀፊው፣ ለጋዜጠኛው ህይወት እንደ ምንድናት?  
ጋዜጠኛ ሆነህ ስትሰራ ዘወትር ሚዛናዊ የሆነ ዜና ለመስራት የሐቅን ምርኩዝ መደገፍ መቻል አለብህ።
ለምን ቢባል ክምር እውነት የመሰሉ እውነቶች እጀርባህ ላይ የመርግ ያህል ይጫኑህና መጻጉዕ ሊያስመስሉህ ይችላሉና። ያኔ ታዲያ የሐቅን በትር ጨብጠህ ያልያዝክ እንደሁ ጉድ ፈላ… በአጭር ቃል አለቀልህ ብልህስ?... ምን እንደሚፈጠር ገመትክ?... እንደ ፍርስራሽ የተጫነህ ወይም ቃሉን ላሳምርልህና የተቆለለብህ ባዶ እውነት ጨፍልቆና ትንፋሽ አሳጥቶ ይገልሀልና ነው።

ሕይወትም እንዲያ ናት። በኖርካት ቁጥር አያሌ ቁልሎች፣ ብዙም ክምሮች አሉ። ያጎበጡህና ያስጎበደዱህ። ካጎበጠህ ነገር ቀና ለማለት ደግሞ እውነትን ፈልፍለህ ስታገኝ ብቻ ነው።

ሚዛኑን የጠበቀ ጋዜጣዊ ስራና ጣፋጭ ህይወት ይመሳሰላሉ። ሲያጣጥሟቸው ሀቅ ሀቅ እየሸተቱ ነገን መኖር ያስመኛሉና።


                          ሕይወት በሐዋርያው ዮሐንስ ዐይን

ስለህይወት ትርጉም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ያሉትን ጽሁፍ ያነበበ ሰውም  የሚከተለውን አስገራሚ ደብዳቤ ጻፈልኝ።

ውድ ዳዊት እንደምንአለህ?

 ይህቺን መልእክት የምጽፍልህ ከተለመደው ስፍራ ሆኜ እንዳይመስልህ። ማለቴ ምድር ላይ ከሚኖሩት መካከል አይደለሁም። በእርግጥ ባንድ ወቅት እንደ አንተና እንደ መሰሎችህ በምድር ላይ ነበርኩ። አሁን ግን ፈጽሞ አይደለሁም። እኔ በሰማዩ ስፍራ የምኖርና ዜግነቴም ሰማያዊ የሆንኩኝ ነኝ። ምድር ላይ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ አስራሁለቱ ደቀመዝሙሮች አንደኛው ነበርኩ። ኢየሱስንም በጣም እወደው ነበር። እሱም ወደ አምላኩና ወደ አምላካችን ካረገ በኋላ ከሐዋርያት ጋር ሕይወት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በብርቱ ሰርተናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በጻፍኳቸውና ለምድር ነዋሪዎች ባበረከትኳው ሶስት መጽሐፎች ማለትም የዮሐንስ ወንጌል፣ የዮሐንስ መልዕክትና፣ የዮሐንስ ራዕይ እታወቃለሁ። ሐዋርያውና ወንጌላዊው ዮሐንስ ነኝ።

ስለ ሕይወት የተለያየ ሙያ ያላቸው ሰዎች የሰጡትን ትርጉም አየሁና ቢገርመኝ ነው ይህን የጻፍኩልህ። ወዳጄ ባጭር አነጋገር ሰዎቹ የሚሉትና ትክክለኛው ሕይወት ትርጓሜ ለየቅል ነው። አንተ ጋዜጠኛው ራስህ ስለህይወት ያለህ ትርጉም ይኼ መሆኑ አሳዝኖኛል።

ዳዊት ለመሆኑ የህይወት ትርጉሙ እውን እናንተ እንዳላችሁት ነው እንዴ?... ፈጽሞ አይደለም። ትክክለኛው የህይወት ትርጉምን ለማወቅ ትፈልጋለህ?... እንግዲያውስ ከመደርደሪያህ ላይ አቧራ የጠጣውን መጽሐፍ ቅዱስህን አንሳና አቧራውን አራግፈህ አንብብ። እዚያ ላይ የህይወት ትርጉም እንደ ማለዳ ጮራ ፍንትው ብሎ ይታይሀል።
በል ታዲያ ትክክለኛውን የህይወት ትርጉም እንዳገኘህ ለተሳሳቱት ሁሉ የህይወት ትርጉሙ ይኼ ነው ብለህ ከስህተት ጎዳና መልሳቸው።

ወደ እኛ ለመምጣት ትጋ። በጽድቅ ጎዳና ተመላለስ። የምስራቹን ወንጌል በጊዜውም ሆነ አለጊዜው ስበክ። እግዚአብሔር ይረዳሀል። ጊዜህ ደርሶም ወደ እኛ እስክትመጣና ሰማያዊ ህይወትህን መምራት እስክትጀምር ድረስ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር፣ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና የመንፈስ ቅዱስ እውነት ያግኝህ።

ሐዋርያና ወንጌላዊ ዮሐንስ
ከአዲስቷ ጽዮን

አስገራሚውን  ደብዳቤ አንብቤ እንደ ጨረስኩ ለዘመናት የመጽሐፍት መደርደሪያዬን ከማጣበብ ውጪ አንዳችም ጥቅም ሰጥቶኝ ወደማያውቀውና አቧራ ወደጠገበው መጽሐፍ ቅዱስ እጄን ሰድጄ መዝዤ በማውጣት የእውነት ማንበብ ጀመርኩ።

እንደ መጀመርያም ለምን የዚህን ሐዋርያ ሶስት መጽሐፎች አላነብለትም አልኩና ከዮሐንስ ወንጌል ጀመርኩ። በመጽሐፉ የመጀመርያ ምዕራፍም እንዲህ የሚል ቃል ሰፍሯል።

«በመጀመርያው ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመርያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ 
አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች ብርሃንም በጨለማ ይበራል፣ ጨለማም አላሸነፈውም።»
 (ዮሐ. ፩፡፩-፭)

በጣም ተገረምኩ። በእርሱ ሕይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሀን ነበረች ነው የሚለው። ምን ለማለት ነው? ብዬም ራሴን ስጠይቅ ከጽሁፉ ያገኘሁት መልስ፡-
፩. ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ መኖሯን
፪. ያም ሕይወት ኢየሱስ መሆኑንና
፫. ሕይወትም ወይም ኢየሱስ የሰው ብርሀን መሆኗን ነው።

(ንባቤን ቀጥያለሁ። ያነሳሁት ነጥብ ስለ ሕይወት ትርጉም ነውና፣ ሕይወትን የተመለከተ ነገር ሳገኝ በማስታወሻ ደብተሬ ላይ አሰፍራለሁ። ደግሞም እንዲህ የሚል ቃል አገኘሁ።)
«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት  እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።»
(ዮሐ.፫፡፲፮)

(በጣም የሚገርም ቃል ነው። የዘላለም ሕይወት ነውኮ ሚለው። እንዴት ያለ ነገር ነው?... በማን ያመነ ነው የዘላለም ሕይወት የሚያገኘው?.... ንባቤን ልቀጥል፣)

«በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት  አለው። በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።»
(ዮሐ. ፫፡፴፮)

(ምን አለ?... በልጁ የሚያምን?... በማ ልጅ?... እንዴ ሐዋርያ ዮሐንስ ምን እያለ ነው?... ለማንኛውም ንባቤን ልቀጥል…)

«… ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፣ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ፣ የህይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር…»
(ዮሐ. ፬፡፲)

(ምናለ?... የሕይወት ውኃ?... ሐዋርያ ዮሐንስ ምን ለማለት እየፈለገ ነው?... እውን እኛ ከምናውቀው የምድር ውኃ ውጪ ሌላ የሕይወት ውኃ የሚባል ነገር አለ?... ይገርማል… እሺ ሐዋርያው በጣም ኃይለኛ «ኢሹ» ነው ያነሳኸው… ·ረ ቀጥልልኝ ትካርህ ጥሞኛል። )

«… እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፣  እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ  ይሆናል እንጂ።»
(ዮሐ. ፬፡፲፬)

(ሐዋርያው ግራ እያጋባኸኝ ነው። ኢየሱስ እንዲህ አለ እያልክ ነው ያለኸው። ታዲያ ይህ የምትለው ነገር እንዴት ሰዎች ሳይረዱት ቀሩ?... ለምንስ በምድር ላይ ብዙ ሐይማኖት ተፈጠረ?... በክርስትና ስር ራሱ እጅግ በርካታ ሐይማኖቶች አሉ፤ ይህ ለምን ሆነ?... ደግሞም የኢየሱስ ዘር የሆኑት አይሁዶች ራሳቸውኮ አልተቀበሉትም፣ … ለማንኛውም እስቲ ማንበቤን ልቀጥል። )

«እናንተም በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው  ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።»
(ዮሐ. ፭።፴፱)

(ከዚህ በላይ ግራ መጋባት ምን አለ?... በጃቸው ያለው መጽሀፍ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩና የሚመሰክሩ ከሆኑ፣ ሌላ ኢየሱስ መጠበቅ ስለምን አስፈለጋቸው?... አሁንስ ቢሆን እየሆነ ያለው እንዲህ አይደለም እንዴ?... ኢየሱስ ብቻ ነው የሕይወት ቁልፉ ተብሎ ሳለ ብዙ ሰዎች ግን ቁልፉን አጥተውታል። ቁልፉ በጃቸው ሆኖ ሳለ አላስተዋሉትም፣ ወይ ንቀውታልና ሌላ የሕይወት በር ቁልፍ እየፈለጉ ናቸው። ሲገርም… ለማንኛውም ወደ ንባቤ ልመለስ…)

«ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፡- የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ  ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምን ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።»
(ዮሐ. ፮፡፴፭)

(እውነታው ግን ብዙዎች ይህንን ቃል አላነበቡትም ወይም አልበራላቸውም ስለዚህም ኢየሱስ የሕይወት እንጀራን ቸል ብለውታል፤ ዳሩ ሰው ካልታዘዘ፣ ካላነበበና ካልሰማ እንዴት ቃሉ ይበራለታል?... እኔን ጨምሮ የብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ አቧራ ከመጠጣት አልፎ ሸረሪት አድርቶበታል።)

«ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።»
(ዮሐ. ፮፡፵

(ወይ ግሩም አያችሁልኝ ሌላ ጉድ?... አያችሁ የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ምን እንደሆነ?... የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የአብ ፈቃድ ነው። ያም በልጁ ስናምን ብቻ ነው። ደግሞኮ ሞተን አንቀርም ምክንያቱም በመጨረሻው ቀን እኔ አስነሳዋለሁ ይላልና ኢየሱስ። አሁን ሕይወትና የሕይወት ትርጉም እየገባኝ ነው። ንባቤን ቀጥያለሁ።)

«እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።  የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ  ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ስጋዬ ነው።… እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ።»
(ዮሐ. ፮፡ ፶፩-፶፬)

«ሥጋ ምንም አይጠቅምም እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።…»

«… ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም። ኢየሱስም ደግሞ ለ አስራሁለቱ እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ። ስምዖን ጴጥሮስ፡- ጌታ ሆይ ወደማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ  እኛስ አንተ ክርሰቶስ የህያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ  አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት።»
(ዮሐ.፮፡፷፰)

(ታዲያ እስከዛሬ የሄድኩበት መንገድ ትክክል አይደለም ማለት ነው? … እስከዛሬ ድረስ የዘላለም ሕይወት እንዴት ማግኘት እንዳለብኝ ማንም የነገረኝ አልነበረም። «ኢቭን» ከናትና አባቴ የወረስኩት ሐይማኖት በራሱ ሰንበትንና በዓላትን ከማክበር ውጪ አንዳችም ቁም ነገር አላስተማረኝም። የናትና አባቴ ሐይማኖትማ ትልቅ ቦታ ሚሰጠው ለአዳኙ እናት እንጂ ለልጇ እንዳልሆነ ጸሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። … እውነት ለመናገር ይኸው እስካሁን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ከጀመርኩበት ሰከንድ አንስቶ አንድም ቦታ ላይ ስለ እናቲቱ አማላጅነት የሚናገር ስፍራ አላገኘሁም። ይልቁንስ የወንጌሉ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ የሚያትተው ስለ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ ምንድነው ምጠብቀው?... እውን የዘላለም ሕይወት ማግኘት አልፈልግምን?... በጣም እፈልጋለሁ። እንግዲያውስ በኢየሱስ ክርስቶስ ልመና?)

1996 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

                                   አዲስ አበባ ጽዳት ርቧታል!
 እነዚያበአንድ ወቅት ጋሽ አበራ ሞላን ተከትለው በመላው አዲስ አበባ እንደ አሸን ፈልተው የነበሩትና ዝማሬያቸው ሁሉፅዳት፣ ፅዳት” የነበረውን ወጣቶች ምን ዋጣቸውመፈክራቸው ብዙ ነበር፡፡ አንዳንዱ አስተማሪ፣ አንዳንዱአስፈራሪ፣ ሌላው አሳፋሪ፡፡
 ለምሳሌ “ፅዳትን ከድመት እንማር “ከምትሸናበት አፅድተህ ተኛበት “ ትሸናናትሸነሸናለህ!” “በየግንቡና አጥር ሥር የሚሸና ውሻ ብቻ ነው ወዘተ የሚሉ ነበሩ፡፡ ኧረ ሲፀዳዳ የተገኘን ሰውአምስት ብር አስከፍለው “ቢል” የሚሰጡም የተደራጁ ወጣቶች እንደነበሩ ትዝ ይለኛል፡፡
ታዲያ በዚያን ጊዜ ነው አሉ አንዱ ፊኛው የተወጠረ አልፎ ሂያጅ ሊተነፍስ ሱሪውን ቢያላላ ፊት ለፊቱካለው ግንብ ላይ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ያነባል፡፡ “በየግንቡና በየአጥሩ ሥር የሚሸና ውሻ ብቻ ነው” ይላል፡፡ሰውዬው ጽሑፉ ብዙም ግድ ሳይሰጠው፣ ደግሞም ሳይፈራና ሳያፍር፣ “ታዲያ ለዛሬ ውሻ ብሆን ምን ይለኛል?. . ምንም” ብሎ ራሱን ጠይቆ ደግሞም ለራሱ መልስ ሰጥቶ ተግባሩን አከናውኖ ሄዷል ተብሎም ሰምተናል፡፡ ስለገዛ ንፅህናው ግድ የሌለው ሰው ስለአካባቢው መበከል ደንታ አይሰጠውም፡፡ 
የሆነው ሆኖ ሕዝብ በብዛት በሚገኝበት፣ በሚገባና በሚወጣበት አካባቢ ደረጃውን የጠበቀመታጠቢያ ቤት ያለው መፀዳጃ ቤት ተሠርቶ ዜጎች ወይ በነፃ አሊያም ኪስን በማይጎዳና ማንኛውም ኅብረተሰብያገልግሎቱ ተጠቃሚ በሚሆንበት መልኩ አገልግሎት የምናገኝበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?  የሚመለከተው አካልእንዲህ ቢያደርግ በአንድ ድንጋይ ከሁለት በላይ ወፎች የመግደል ያህል ይመስለኛል፡፡ አንድም በመፀዳጃ ቤትእጦት ምክንያት በያገኝበት ለሚፀዳዳው የኅብረተሰብ ክፍል እፎይታ ይሰጣል፤ ብሎም ለሥራ አጥ ወገኖች የሥራዕድል ይከፍታል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አዲስ አበባችን ትፀዳለች፡፡

የክት ልብሱ እንዴት የውሃ ሽታ ሆና ቀረች ለሚሉ ወገኖች የተሰጠ ቀና ምላሽ
እፍኝ በማትሞላ ደሞዜ ‹‹አልበላም አልጠጣም›› ብዬ የገዛኋት አንዲት ጥቁር የቻይና ‹‹ሱፍ››፣ የክት ልብስ ነበረችኝ፤ ብዙ ጊዜ ከነጭ ሸሚዝጋ እለብሳት ስለነበረም ብዙ ሰዎች ሐኪም ያዘዘልኝ ይመስላቸው ነበር፡፡ ‹‹ሳይተርፋት አበድራ፣ . . .›› እንዲሉም የቤት አከራዬ ‹‹ፍንዳታ›› ልጅ፣ ባንድ የተረገመች ቀን ከምወዳት የክት ልብሴ አለያይቶኛል፡፡ 

እንዲህ ነው የሆነው አንድ ቀን  ጸጉሩን እየቋጨብኝ፡- ‹‹ባክህን ሠርገኛ ነኝና ሱፍህን አውሰኝ፡፡›› ይለኛል፡፡ ምን ችግር አለው፣ ውሀ ለሚጨርሰው ልብስ ብዬም ያልጠየቀኝን ነጯን ሸሚዜን ጨምሬ አውሰዋለሁ፡፡ በሠርጉም ዕለት ደመቀበት፣ ‹‹ካይን ያውጣህ››ም ተባለ፡፡ በኋላም ባለው ቀን ልብሴን መመለስ ‹‹ረሳ››፡፡ ከሩቅ ሲያየኝ ሲሸሸኝ፣ እኔም ላለማሳፈር ያላየሁ ለመምሰል ስጥር፣ ድንገት ደግሞ የሆነ ቦታ ስንገናኝ ቀንዷን እንዳሏት ላም ፈጥኖ በሌላ መንገድ ሲቀይስ ብዙ ጊዜ ሆነ፡፡ ወደቤቱም በጣም አምሽቶ ነው የሚገባው፡፡ ‹‹ለማኝ እንትን›› ሳይልም ወደ ሚሄድበት ይሄዳል፡፡

 እናም አንድ ቀን ሲብስብኝ አፍ አውጥቼ ልብሴን መልስ እንጂ ብሎ መጠየቅ ከሱ ይልቅ ቢያሳፍረኝ ከኔ ይልቅ ልጁን ይቀርበው ለነበረ ጎረቤቴ አማከርኩት፤ ጎረቤቴም ያገኘውና፡- ‹‹የሰው ልብስ ተውሶ አለመመለስ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ባለታሪካችንም ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው?  ‹‹ከፈለኩ አልሰጠውም! ምን ያመጣል?›› . . . እውነትም በጊዜው ምንም የማመጣው ነገር ስላልነበረ፤ እሱም ሳይመልስልኝ እኔም ዳግመኛ አፌን 
                                  
                              እስቲ ደሞዛቸውን ልቀበልላቸው

ሳላበላሽ በሰላም ተለያየን፡፡አንድ ጓደኛ ነበረኝ፣ ሁሌ ደሞዝ ሲደርስ ደርሶ የሚከፋው፡፡ ለምን መሰላችሁ? መላ ደሞዙ ቀድሞ በብድር ስላለቀ ነው፡፡ ከሚቀጥለው ወር ደሞዙ ላይ ‹‹ኢንአድቫንስ›› በመውሰድም ሠራተኛውን ይመራ ነበር፡፡ ታዲያ ሁሌ ደሞዝ ሊቀበል ሲሄድ አንድም ቀን ‹‹እስቲ ደሞዜን ልቀበል›› ብሎ አያውቅም፤ ይልቁንስ ‹‹እስቲ ደሞዛቸውን ልቀበልላቸው፡፡›› ነበረ እንጂ የሚለው፡፡

                                                                   የገንዘብ ዕዳ
ገና የመጀመርያ ደረጃ ክፍል ተማሪ እያለሁ አንድ ጓደኛ ነበረኝ፤ በዚያች እድሜው ሸንኮራ አገዳ ሸጦ ምስኪን ቤተሰቡን የሚደጉም፡፡ ትዝ ይለኛል ጓደኛዬ ከትምህርትቤት እንደተመለስን ቶሎ ብሎ ቢላዋውንና ሸንኮራውን ይይዝና ከቤታቸው ጥቂት ፈንጠር ብላ ወደ በቀለችና ዘወትር ከጥላዋ  ስር፣ ሥራ አጥ ወገኖች ቁጭ ብለው ‹‹ድድ ከሚያሰጡባት›› የግራር ዛፍ ስር ቁጭ በማለት ሸንኮራውን ይቸረችር ነበር፡፡ ገና በብላቴናነቱ ቤተሰቡን የማገልገል የዕዳ ቀንበር አርፎበታልና፡፡ ‹‹ያባት ዕዳ ለልጅ›› ይሏል እዚህጋ ነው፡፡

 ታዲያ አንድ ጊዜ አንድ የሠፈራችን ጉልቤ ልጅ
‹‹ሸንኮራ ቁረጥልኝ!›› ይለዋል፤
‹‹የስንት?›› ጓደኛዬ እየፈራ
‹‹የአምስት ሳንቲም፡፡››
‹‹እሺ፡፡››
ግማሽ አንጓ ቆረጠለት፡፡ ጉልበተኛውም ልጅ አምስቷን ሳንቲም ሳይከፍል ሲሄድ ጓደኛዬ እምባው እየመጣበት፡-
 ‹‹ሂሳብ አልከፈልከኝም እኮ፣ አምስት ሳንቲሜን ክፈለኝ እንጂ!›› ይለዋል እየተከታተለ
ጉልቤውም ልጅ በሰፊው አፉ ሸንኮራውን እያሸረመደ
‹‹ይከፈልሃል!›› ይለዋል ቆጣ እያለ
‹‹መቼ ነው ምትከፍለኝ?››
‹‹ነገ!››
ነገ ነገን ሲወልድ፣ ሳምንት ሲሆን፤ ሳምንት ሳምንትን ወልዶ ወር ሲጠባ፤ ወርም ወርን እየወለደ አመት ሲሆን፤ ጉልቤው ልጅ የውሀ ሽታ ሆነ፣ ዕዳውንም በዚያው ረሳ፡፡ ጓደኛዬ ግን ‹‹የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም›› እንዲሉ፤ ድንገት የሆነ ቦታ ወይ ኳስ ሜዳ አሊያም ትምህርት ቤት ልጁን ሲያየው ይሮጥና፡-
 ‹‹አምና የተበደርከኝን የአምስት ሳንቲም ሸንኮራ ሂሳብኮ አልከፈልከኝም›› ሲለው

ጉልበተኛው ልጅ ደረቱን እየነፋ የሚያውቃትን ቃል ‹‹ይሰጥሀል!›› ይላል፡፡ መቼ እንደሚሰጠው ግን እንኳን ጓደኛዬ እሱ ራሱም አያውቅም፡፡ ለጉልቤውም ልጅ ቅፅል ስም አወጣንለት፣ ‹‹ይሰጥሀል›› ብለን፡፡ ይኸው እስከዛሬ ከዚያ የህፃንነት ጓደኛዬጋ ስንገናኝ ስለ ‹‹ይሰጥሀል›› ትዝታ ስናነሳ፤ ምንም እንኳ ጓደኛዬ  ትልቅ ደረጃ ላይ ቢደርስም ቅሉ፤ አምስት ሳንቲሟን ግን ፈጽሞ አይረሳትም፡፡ ዕዳ ናትና፤ የገንዘብ ዕዳ፡፡


                                       ያጋደለ ሚዛን
ሐኪሙን፣ መሐንዲሱን፣ ያገር መሪውን፣ ጋዜጠኛውን፣ ወታደሩን፣ ወዘተ. . . ሁሉ የሚቀርፁ መምህራን ወዳጆች አሉኝ፡፡ ባንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምሩ፡፡
 ታዲያ እነኚህ ወጣት መምህራን በትምህርት ቤቱ አስተዳደር ስብዕናቸውን የሚነካ ነገር ተፈጽሞባቸውና በደል ደርሶባቸው በማያውቁት ነገር ከሥራ ይባረራሉ፡፡ እነርሱ እንደሚሉት የተባረሩበት ምክንያት ከዲሞክራሲ መብቶቻቸው አንዱ የሆነውን ማኅበር  በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በማቋቋማቸው ነው፡፡ ነገር ግን ለሠራተኛው የሚሟገት አካል ሲመጣ ደስተኛ ያልሆነው የትምህርት ቤቱ አስተዳደር አንዳችም ዓይነት ሥራ በማይገኝበት በክረምት ያለ ቤሳ ቤስቲን ከሥራ ያፈናቅላቸዋል፡፡
 መምህራኑም ጉዳዩን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት ያመራሉ፡፡ አንቀጽ ጠቅሰውም በፍትሕ አገር ግፍ እንደተዋለባቸው ያስረዳሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም ትምህርት ቤቱ ያባረራችሁ ማኅበር በመመሥረታችሁ አይደለም፤ ይልቁንስ በዚህ ምክንያት ነው እንጂ ብሎ እነርሱ የማያውቁትን ነገር ጭብጥ ያስይዛቸውና ለዚያ መልስ ይሰጡ ዘንድ ግድ ይላቸዋል፡፡
 መምህራኑም ከበቂ በላይ የሰው ምስክር ስለነበራቸው መልስ ይሰጣሉ፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ከመንፈቅ በላይ እሰጥ አገባና የፍርድ ቤት መመላለስ በኋላ፣ የፍርዱ ሚዛን ወደ ትምህርት ቤቱ አጋደለና የመምህራኑ ዕጣ እንባን ወደ ላይ ረጭቶ፣ ‹‹አንቺ እናታችን አንቺ ውዷ የእኛ፣ መች እናገኝ ይሆን ያልተዛባ ፍርድ እኛ?›› በማለት ማንጎራጎር ነበር፡፡

                                           ዝምታ ወርቅ ነው!!
በአንድ ማለዳ ወዳጄ ከቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወደ ፒያሳ በሚወስደው መንገድ ላይ ፒያሳ የሚሄድ ታክሲ ከሌሎች ተሳፋሪዎች ጋር ችሎት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በርከት ብለው ይጠብቃሉ፡፡ ሰዓቱ እየረፈደ ነው፡፡ ሁሉም ተሳፋሪ ቶሎ ታክሲ አግኝቶ ወደ ሥራ ይሄድ ዘንድ ጓጉቷል፡፡ ነገር ግን ታክሲዎች በሙሉ ከመነሻው ማለትም ከቀጨኔ መድኃኔዓለም እየሞሉ ስለሚመጡ ችግራቸው የከፋ ሆነ፡፡ በዚህን  ጊዜ አንድ ከፒያሳ የመጣ ታክሲ በአጋጣሚ ከመጨረሻው ሳይደርስ መንገድ ላይ ተሳፋሪዎቹን በሙሉ አውርዶ ባዶ ስለነበረ፣ ችሎት አደባባዩ ላይ ያዞርና ወደፒያሳ ለመሄድ ተኮልኩለው የነበሩትን መንገደኞች ማሳፈር ይጀምራል፡፡ በአካባቢው የነበሩ ሁለት የፀጥታ አስከባሪዎች ግን ታክሲው እንዳይጭን ያዙታል፡፡ ‹‹እንዴ ምን ችግር አለው?›› አለ ረዳት፤ ‹‹አደባባይ ላይ ተሳፋሪዎች ወርደው ታክሲው ባዶ ከሆነ እዚህ ብንጭን ምን ችግር አለው?›› አለ ሾፌር፤ ‹‹ምንድነው ችግሩ?›› አሉ ተሳፋሪዎች፤ ‹‹አይቻልም! አዙረህ ሄደህ ከመነሻው ጫን!›› አሉ የፀጥታ አስከባሪዎቹ፡፡
በዚህ መሀል እሰጥ አገባው እየከረረ፣ እየከረረ መጣ፡፡ ‹‹ባዶ አይደለሁ እንዴ? እዚህ ብጭን ችግሩ ምን እንደሆነ ልትነግሩኝ ትችላላችሁ?›› ይጠይቃል ረዳት፡፡ ፖሊሶቹም እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው፣ ‹‹ጭራሽ ችግሩን አስረዱኝ ይላል እንዴ?›› ይሉና አንጠልጥለው ወደ አንድ የግለሰብ ግቢ ያስገቡታል፡፡ አስገብተውም እንደ በርበሬ ደልዘው፣ እንደ ኑግ ወቅጠውና እንደ ተልባ አድቅቀው ባፍና ባፍንጫው ደም ቡልቅ ቡልቅ እያለ ቢልኩት ተሳፋሪዎች በሙሉ በጣም ተገርመውና ደንግጠው፣ ደግሞም ነግ በኔን ፈርተው በሹክሹክታ ‹‹ምን ዓይነት ጉድ ነው መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር ለምን እንዲህ ዓይነት ድርጊት ይፈጸማል? ዴሞክራሲ አለ በሚባልበት አገር እንዴት እንደዚህ ይደረጋል? ታዲያ የቱ ጋ ነው ነፃነት ያለው?›› እያሉ ሲያጉረመርሙ፣ ‹‹የፀጥታ አስከባሪዎቹ›› ሁሉንም ሰዎች አስወርደው ታክሲው ከመነሻው እንዲጭን ፈርደውበታል፡፡ እንግዲህ ሾፌርና ወያላ እንዲሁም ተሳፋሪዎች ለምን? ብለው ስለጠየቁ ነው ይህ ሁሉ ድርጊት የተፈጸመው፡፡
እኔ የምለው?
1.       የፀጥታ አስከባሪዎች ሥራቸው ፀጥታ ማስከበር ወይስ ሰላም ማደፍረስ?
2.      የፀጥታ አስከባሪዎች ሥራ ችግር መፍታት ወይስ በቆመጥ ሰው መነረት?
3.      በሰው ግቢስ ያለፈቃድ ሰውን አስገብቶ መደብደብ ይቻላል?
4.      አንድ ሰውስ ጥፋት እንኳ ቢኖርበት በ48 ሰዓታት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት መወሰድ ይገባዋል እንጂ እንዲያ ይደረጋል? ነውር አይደለም?
5.      ለሕግ ያልተገዛው እነርሱ ሕግ አዋቂዎቹ ወይስ ሕግ አላወቀም የተባለው ረዳት?

እዚህ ላይ መንግሥት የፖሊስ ሠራዊቱን ሲያሠለጥን በአብሮነት ሕገ መንግሥቱን፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉንና ሌሎች ሕጎችን በሥልጠና ወቅት በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እንደሚያስተምር አልጠራጠርም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመናገር ነፃነት አለመኖር ፈርጀ ብዙ ችግሮች አሉት፡፡ ለምሳሌ እንደ ሰደድ እሳት ለተስፋፋው ሙስና ይህ ዓይነቱ ችግር ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ ሕዝቡ የሙስና ወንጀል እንዳለ ያውቃል፡፡ በዚያ ሰንሰለት ውስጥም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያሉትን አብጠርጥሮ ያውቃል፡፡ ግን በሰዎቹና በሥራቸው ላይ አንዳች ለማለት አቅም የለውም፡፡ ምክንያት ቢሉ ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱ የተገደበ ነውና፡፡ ለደኅንነቱም ይሰጋልና፡፡ ለዚህ ነው ሥርዓታችን እንደ ፍልፈል ውስጥ ለውስጥ የሚሄድን እንጂ ግልጽ የሆነ ማንነትን በሕዝባችን ውስጥ ያላዳበረው፡፡ መንግሥትና ሕዝብ እጅና ጓንት መሆን የሚችሉት መንግሥት አንዳችም ገደብ የሌለበት ሐሳብን በነፃነት የመናገርና የመጻፍ ነፃነት ሲያጎናጽፍ ነው፡፡ አለዚያ ግን በክፍተቱ ንፋስ ይገባና ለጥፋት ኃይሎች መሣሪያ ይሆናል፡፡ ፖሊሲዎቿንና መመርያዎቿን ‹‹ኮማ›› ሳይቀር የምንኮርጅላት አሜሪካ ዴሞክራሲዋን፣  ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመጻፍ ሕጓንም ልንኮርጅላት ይገባናል፡፡

                                                                             ጣና
አጣፍቶ የወግ ኩታ ደርቦ የወኔ ባና፣
ደረቱን ገልብጦ እያየ ደመና፣
የጎጃሜው ኩራት ያውላችሁ ጣና።

ምንም እንኳ ዕለቱ እሁድ፣ የሄድኩበትም ሰዓት ረፋዱ ላይ የነበረ ቢሆንም በተንጣለለው የጣና ሀይቅ ላይ ሁለት ታንኳዎች ብቻ ነው ያየሁት።  አብዛኛዎቹ ታንኳዎች ሀይቁ ዳር ታስረው በንፋሱና በውሃው በሚፈጠረው ትንሽዬ ማዕበል ዥዋዥዌ ይጫወታሉ። …ጎብኚውን ምን ዋጠው?

የጣና ሀይቅ ዙሪያ ገባ ለጎብኚዎች እንዲመች ተደርጎ ነው የተሰራው። ሀይቁን «ወክ» እያረጉ ይጎበኙት ዘንድ ቢሄዱበት ቢሄዱበት የማያልቅ ደገጃውን የጠበቀ የእግረኛ መንገድ አለ። ወደፊት ደግሞ ጥሩ ተስፋ ሊፈነጥቁ የሚችሉ ሪዞርቶች እየታነጹ ነው።



                               ባሕር ዳር
...አመሻሽ ላይ ከውቧ ባህርዳር ገባን።  ታዳጊ ደላሎች አፋፍሰው አልጋ ወዳለበት አንድ ሆቴል እኔና ሦሥቱን ጓደኞቼን ይዘውን ሄዱ። ቡና ቤቱ አንድ መጸዳጃ ቤት ብቻ ስለነበረውም ተንፈስ ለማለት ወረፋ መያዝ ነበረብን። በዚያ ላይ የአልጋ ክፍሎቹ በራሳቸው ጽዳት የሌላቸውና በየአጎበሮቹ ላይ ቁና ሙሉ ቢንቢ የሰፈረባቸው ናቸው። «በቡሀ ላይ ቆረቆር» እንዲሉም ከቡና ቤቱ የተለቀቀውና የጆሮን ታምቡር የሚጠልዘው አገርኛ ሙዚቃ፣ በስካር ለዛ አብረው ከሚያንጎራጉሩ ጠጪዎችጋ ተዳምሮ ባየሩ ላይ ሲናኝ ፣ከዚያ ድካምጋ ሌቱ እንዴት እንደሚነጋ ሲታሰበኝ ግራ ገባኝ። ይሁን እንጂ ሀምሳ ሀምሳ ብራችንን ቀድመን የከፈልን ቢሆንም ቅሉ፣ ለእራት ፍለጋ ስንወጣ ሌላ የተሻለ አልጋ በአምስት ብር ልዩነት ብቻ አግኝተን አዳራችንን እዚያ አደረግን።

ታዲያ ለክፋቱ፣ ኩነኔ እንደገባ ሰው ሌቱ አይንጋልህ ቢለኝ፣ እኔ ያረፍኩበት ክፍል ከጎኑ ጽዳት የናፈቀው መጸዳጃ ቤት ነበርና ፤ አዳሬ እስከዛሬ ከገጠሙኝ መጥፎ አዳሮች መካከል አንደኛው ሆኖ ተመዘገበ። እንዲቹ ሌቱን ሙሉ የተበከለ አየር ስምግ አደርኩ።
በዚያች ጥቂት ቀናትም ባህርዳርን በምሽት ላያት ሞክሬያለሁ፣ በዕድሜዬ ካየሁዋቸው ውብ መንገዶቿ ላይም «ወክ» በልቻለሁ።

ባህርዳር ደረጃውን በጠበቀ «ፕላን» የተቆረቆረች ውብ ከተማ ናት። መሀልና ዳር ላይ ተተክለው ያለከልካይ ከሚዘናፈሉት ዘንባባዎችዋና ልዩ ልዩ ዛፎችዋ ባሻገር ለጥ ባሉትና ሰፋፊ ስፓልት መንገዶቿ ላይ ተሳፋሪ አንግበው ሽቅብ ቁልቁል የሚሉት  ባጃጆቿ ልዩ ውበቷ ናቸው።
በባህር ዳር አንድም የገበጣ መጫወቺያ ቆሬ የመሰለ መንገድ አላጋጠመኝም። ይልቁንስ በየመንደሩ ከጫፍ ጫፍ የተዘረጋውና በብልሀተኛ ባለሙያዎች የታነጸው የ«ኮብል ስቶን» መንገድ በውበት ላይ ውበት ጨምርሏታል እንጂ።

ዩና አፍንጫን ሰንጎ የሚይዝ ጠረን፣ ደግሞም አይንን «የሚያቅለሸልሽ» ቆሻሻ ፈጽሞ አላየሁም።  ይልቁንስ በየመንደሩ የተንጠለጠሉት የቆሻሻ ቅርጫቶች ህዝቡ ለጤናና ውበት ቅድሚያ ሰጥቶ ምን ያህል እየሰራ እንደሆነ  ይናገራሉ እንጂ።
ህንጻዎቿ ውበት ብቻ ሳይሆን ከእድሜ ጫፍ መድረስ እንደሚችሉ አሰራራቸውና የተሰሩበት ቁስ ያሳብቃል።

ነገር ግን «ውስጡን ለማንትስ» እንዲሉ ወደ ማጀቷ ስንዘልቅ እንደብዙዎቹ አሉን የምንላቸው ከተሞች ውቧ ባህርዳርንም  የሚያሳጡ፣ ከዘመናዮቹ እኩል የማይራመዱ፣ አንካሳና  በእድሜ ጫና የጎበጡ  ሰቀላ ቤቶች ድካም ተጫጭኖናል ማረፍ እንሻለን የሚሉ ይመስላሉ።
በየታዛውና ደጀሰላሙ ጥቂት የማይባሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለማየት ብችልም፣ በዘልማድ «የኔ ቢጤ» የሚባሉትንና በሰው እጅ የሚተዳደሩ ወገኖች በቁጥር ሁለት ወይም ሦሥት ነው ያጋጠሙኝ እነርሱም የአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን።

ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ግን አንድ ታዳጊ የአካል ጉዳተኛ በጣም አስደምሞኛል። ይህ ሁለት እግሮቹ በልጅነት ልምሻ የተጠቁት ልጅን ከሩቅ ሳየው መንገድ ዳር ተቀምጦ የሚለምን ነበረ የመሰለኝ፣ ነገር ግን ጠጋ ብዬ ሳየው እየለመነ ሳይሆን መፋቂያ እየሸጠ ነበር። ጓደኛዬ በጣም ተደስቶና ተገርሞም የአስር ሳንቲሙን መፋቂያ በአስር ብር ገዝቶታል።

                                        (ከባሕርዳር ደርሶ መልስ የጉዞ ማስታወሻዬ የቀነጨብኩት)


                                 የጎጃም ጤፍ
ክረምት ሳይል በጋ
ቆላ ሳይል ደጋ
ለዘመናት ያገሬን ጉሮሮ የዘጋ
ባለውለታችን የጎጃሙ ማኛ
አሁን ድረስ አለ ዘብ ቆሞልን ለኛ።

በሰፊው ሁዳድ ላይ ከሩቅ ሲታይ እንደ ጠጠር የፈሰሰው ነገር ሌላ ሳይሆን የጤፍ ክምር ነው። እንዲህ ለዕይታ የሚያታክት የጤፍ ክምር ከተፈጠርኩ አይቼ አላውቅም። ዙሪያ ገባውን ቢያማትሩ አይንን ሰንጎ የሚይዘው ሌላ ሳይሆን የጤፍ ክምር ነው። እንዴት ነው ጎበዝ «ምንም ቢያርሱ እንደ ጎመን አይጎርሱ» የተባለው ተረት ምናልባት እዚህ አገር «ምንም ቢያርሱ እንደ ጤፍ  አይጎርሱ» ይሆን እንዴ?... ግን ግን ፡- «ለምን ታዲያ የጤፍ ዋጋ ሰማይ ነካ?»…«ለምን ስ እንደ ውሻ ምላስ የሳሳ እንጀራ ሶስት ብር ተሸጠ?»… ይሄ የማየው ጉድ፣ አይደለም ኢትዮጵያን ድፍን ዓለምን መመገብ አይችልምን? (እዚህጋስ ሳላጋንን አልቀርም፤ እንዲያው ያየሁትን ነገር በደንብ ለመግለጽ ፈልጌ ነው።)
                                          ዓባይ በረሀ

  እንዴት አይነት ተፈጥሮ ነው ጎበዝ?   ትንፋሽን ጸጥ ያደርጋል ዓባይ በረሃ። ... ላፍታ ነፍሴ በሲዖል ያደረች መሰለኝ። እንዲህ ዓይነት ውበትና አስፈሪነት የተዋሀደበት ተፈጥሮ አይቼም ሆነ ሰምቼ አላውቅም። የጀግናው ቁርጭምጭሚት ቀጤማ የሚሆንበት፣ የኃያሉ ወገብ እንደ አራስ ሴት ደርሶ ውሃ ሚሆንበት፣ የብርቱው ክንድ ሚዝልበት፣ የፈሪው ሩህ  ጸሀይ እንደጎበኘው ቂቤ ሚቀልጥበት ቦታ ነው ዓባይ በረሀ ማለት።
እንግዲህ የበርካታ አገራት መመኪያና ተስፋ የሆነው የዓባይ ወንዝ ከአፋፍ ሆነው ቁልቁል ሲያዩት፣ በአንድ ትንሽ ካፊያ የተፈጠረ የቦይ ውሀ ነው እሚመስል። ወዲያውም የተወሰኑ ጥያቄዎች ራሴን ጠየቅሁ « ለመሆኑ አባይ ቢሞላ ቢሞላ አለው መላ መላ» የተባለው ዘፈን ምን ለማለት ይሆን? እውን አባይ ሞልቶ ያውቃልን? ከሞላስ እስኬት ነው የሚሞላው?... ያለም ውሃስ በሙሉ ቢጠራቀም ይሞላዋልን? (ይህቺኛዋ እንኳን የጅል ወይም የልጅ ጥያቄ ሳትሆን አትቀርም።)
ከላይ እንዳልኩት በዚያ መስመር ገና የመጀመሪያ ጉዞዬ ነውና፣ አቡነ ዘበሰማያትን በሆዴ ስንት ጊዜ እንዳነበነብኩ መናገሩ ዋጋ የለውም። ብቻ እንዲቹ ልቤ እንደተንጠለጠለችና ነፍስና ስጋዬ እንደተወራጩ ያን ግርማው የሚያርድ፣ ሞገሱ የሚያሸብር ቦታ ከ አንድ ሰዓት ምናምን ጉዞ በኋላ ጨርሰን ወደ ሜዳማው መልክዓ ምድር ገባን።


No comments:

Post a Comment

ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡