ስለጋብቻ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ብዙ ስፍራዎች ላይ ተጽፏል። ትዳር መልካም
እንደሆነ፣ ጋብቻ ቅዱስ መኝታውም ንጹህ እንደሆነና የእግዚአብሔርም ክቡር ሀሳብ እንዳለበት ወዘተ…
እግዚአብሔር አስቀድሞ ሰውን ሲፈጥር በመጀመርያ ብቻውን እንዳልነበረ በመጽሐፍ
ቅዱስ ዘፍ. 1፡36 ላይ ይናገራል። ይህ ስፍራ ምን ያህል እግዚአብሔር ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ እንዳልወደደ የሚያሳየን
የመጀመርያው ክፍል ነው። ለዚህም ነው "ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው::" የሚለው። በነገራችን ላይ
እግዚአብሔር በመጀመርያ አዳምን (ወንድን) ብቻ ነው የፈጠረ የሚመስለን አይደል?.. ግን በማስተዋል
ስናነብ "እግዚአብሔርም ሰውን ፈጠረ፣ ወንድና ሴት አድርጎም ፈጠራቸው::"
ይላል። (ዘፍ. 1፡27)
እግዚአብሔር ትክክለኛው ሰዓት እስኪመጣ ድረስ ሄዋንን ከአዳም አላወጣትም
ነበር። አዳም ለጊዜው ብቻውን በሚመስል ብቸኝነት ነበር ይኖር የነበረው። ይህ ህይወት ወደፊት መቀጠል አልነበረበትምናም፣
እግዚአብሔር ‹‹ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደልም፣ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት›› አለ። ስለዚህ የሚመቸውን ረዳት
ይመርጥ ዘንድ በምድር ላይ ያሉ እንስሳትንና አራዊትን ወደርሱ አመጣለት። ነገር ግን አዳም ያን አሳ ሲል ያኛውን
ነብር ሲል፣ ይህን ወፍ ሲል፣... ስም ከማውጣት በስተቀር እንደ ራሱ ያለ ረዳት ሊያገኝ አልቻለም ነበር።
አንዳንድ ጊዜ ይህን ቃል ሳብሰለስል፣ እኛ አዳሞች በህይወት ጉዟችን ላይ
የሚያጋጥሙን ሴቶች በተለይ በዚህ በፍቅር ዙርያ የምናውቃቸው ሴቶች ሁሉ ትክክለኛዋ ሄዋን ጊዜዋ ደርሶ እስክትፈጠርልን ድረስ
እግዚሀር ስም እንድናወጣላቸው የሚያመጣልን ይመስለኛል (ምን ያህል ትክክል እንደሆንኩ ባለውቅም)።
‹‹እገሊት አመሏ ነጭናጫ ነው፣ ያቺኛዋ ቁጡ ናት፣ ይህቺ እንዲህ ናት፡፡››
እያልን አዳም ትክክለኛ ረዳቱን እንዳለገኘና ይልቁንስ ለእንስሳቱና ለአራዊቱ፣
ለባህር ፍጥረታቱና ለሰማይ ወፎች ስማቸውን ብቻ አውጥቶ እንደ ላካቸው እኛም ለህቶቻችን ስም ብቻ አውጥተን
እንልካቸዋለን፣ ትክክለኛዋ ሄዋን ጊዜዋ ደርሶ እስክትፈጠርልን ድረስ።
መጽሐፍ ቅዱስ አዳም ሄዋንን እስኪያገኝ ለምን ያህል ጊዜ እንደተሣቀየ
ባይነግረንም እኔ ግን ይህን ህልቆ መሣፍርት ፍጥረታት ሲሰይምና እንደርሱ ያለ ረዳት ሲፈልግ አያሌ በጋና ክረምት ያሳለፈ ነው
የሚመስለኝ።
የሆነው ሆኖ እግዚአብሔር አዳም ትክክለኛ ረዳቱን እንዳላገኘ ሲረዳ አንድ
ነገር አሰበ። አስቀድሞ ከአዳም ጋር ባብሮነት የፈጠራትና እስከ አሁን ድረስ በአካል ያልተገለጸችውን ሴት ከተደበቀችበት የአዳም
አካል ማውጣት እንዳለበት።
ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፣
አንቀላፋም፣ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በስጋ ዘጋው። እግዚአብሔር አምላክም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ
ሰራት፣ ወደ አዳምም አመጣት፣ አዳምም አለ «ይህቺ አጥንት ከአጥንቴ ናት፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፣ እርስዋም ከወንድ ተገኝታለችና
ሴት ትባል።» (ዘፍ. 2 ፡21-22)
እንግዲህ ወደ ጽሁፌ አንኳር ጉዳይ ልምጣና ይህ የከበረ ትዳር የሚፈጸመው
በማን ነው? ትዳርን የሚሰጥ ሚስትን የሚያዘጋጅ ማነው? ደላላ… ወይስ እግዚአበሔር ብለን ስንጠይቅ ያላንዳች ጥርጥር
እግዚአብሔር ነው እንላለን። እግዚአብሔር በዚህ የህይወታችን ታላቅ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ሊገባ የግድ ነውና፡፡
ምናልባት ይህን ጽሁፍ የሚያነቡ ብዙዎች እንዴት እንዲህ ትላለህ ለይስሐቅ
ርብቃን ያመጣለት ዔልዔዜር አይደለም እንዴ? ሊሉ ይችላሉ። እኔ ግን ርብቃን አስቀድሞ እግዚአብሔር ለይስሐቅ ስላዘጋጃት እንጂ
በዔልዔዘር አማጭነት (ደላላነት) ነገሩ አልተከናወነም ነው መልሴ። ለዚህምኮ ነው ይስሐቅ ርብቃን ገና ሲያያት የወደዳትና ከናቱ
ሣራ ሞትም የተጽናናው። (ዘፍ. 24፡67)
አሪፍኮ ነው ምናልባት በደላላው አማካይነት ሚስቴን በልኬ ላገኝ እችል
ይሆናል፣ እሷም መሻቷን ታገኝ ይሆናል፡፡ ባወጣነው መስፈርት መሰረት ዘሯ ከዘሬ፣ ሐብቷ ከሐብቴ፣ ዕውቀቷ ከዕውቀቴ ተጋብተዋል።
ነገር ግን ትልቁና ዋነኛው ነገር፣ ያም ነፍሴ ከነፍሷ እንዴት ነው ሚጋቡት? ትዳርንኮ ልዩ የሚያደርገው ነገር በዘልማድ
እንደምናውቀው የአካል ከአካል መዋሀድ ሳይሆን የነፍስ ከነፍስ መጣመር ነው።
እዚህ ጋ አንድ ያጋጠመኝን ማንሳት ግድ አለኝ፣
የሆነ ጊዜ ሰዎች ሁሉ ጎጆ ሲቀልሱ፣ የሞቀ፣ የደረጀና የደመቀ ኑሮም ሲኖሩ
አየሁና እኔስ «ሁ ማይነስ ሁ?» በማለት፣ ከቅን ልቦና በመነጨ ስሜት፣ ገና የትዳርን ሀሁ ሳላጠና፣ እንደ ብልጦቹ ሀብትና
ንብረት ሳላደራጅ፣ ...የማገኛቸውን ሰዎች ሁሉ ሚስት ይፈልጉልኝ ዘንድ ተማጸንኩ። በኋላም ከታላቅ ወንድሞቼ
አንደኛው:-
«የእውነት ሚስት ማግባት ትፈልጋለህ?» ይለኛል
«እንዴታ ምን ጥያቄ አለው?» (ፍርጥም ብዬ)
«እንግዲያውስ አንዲት እህት አለች፣ ትዳር ትፈልጋለች፣ ስልኳን ልስጥህና
ደውልላት።»
«ስራ አላት?»
«አዎ አላት።»
«ደሞዟ ምን ያህል ነው?»
«አንድ ሁለት ሺ ምናምን… ለዚያውም ‹‹ኤን ጂ ኦ›› ውስጥ ነው
የምትሰራው።»
«እውነትህን ነው?... በል እንዲያ ከሆነ ፈጥነህ ስልኳን ወዲህ በል።»
ስልኳን ሰጠኝ።
አፍታም ሳልቆይ ደወልኩላት። ከዚያኛውም ጫፍ
«ሀሎ» የሚል ውብ የእንስት ድምጽ በጆሮዬ አንቃጨለ፡፡
«ሄሎ ሣራ ነሽ?» (ለባለታሪኳ ስም ጥንቃቄ ለጊዜው ስሟን ቀይሬዋለሁ።
ምናልባት ሣራ መጣጥፌን እያነበብሽ ከሆነ ‹‹አሰላም አለይኩም›› ብያለሁ በአረብኛ ቋንቋ፡፡ ሰላም ላንቺ ይሁን እንደማለት
ነው፡፡)
«አዎ ማን ልበል?»
ስሜን ነገርኳት። ስልኳንም ከወንድሜ ሳይሆን ከሌላ ሰው እንዳገኘሁ አረዳኋት።
(ወንድሜ ስልኳን ከእሱ እንዳገኘሁ እንዳልነግራት አስጠንቅቆኝ ነበርና፡፡) ለደቂቃዎች ያህልም በቀጥታ ለምን እንደምፈልጋት
አወራኋት። የበለጠ ተገናኝተን እንድናወራም ወፍራም ቀጠሮ ያዝን።
በቀጠሮውም ቀን የክት ልብሴን በተለይም አንዲት በፍጹም የማልረሳት «ስትወርድ
ስትዋረድ» የመጣች ታሪካዊ ኮቴን ሽክ ብዬ ወደ ቀጠሮው ስፍራ አመራሁ። «ፎር ዩር ሰርፕራይዝ» ቤታቸው ነበር የቀጠረችኝ።
ከግቢያቸውም ዘልቄ የዋናውን በር ሳንኳኳም «ግባ» የሚል ድምጽ ሰማሁ፣ ገባሁ።
ግባ ያለችኝ ሴት ከተንጋለለችበት ረጅም ሶፋ ላይ ቀና እያለችና እየጨበጠችኝ፡
«ሀይ ሰላም ነህ? ቁጭ በል ቁጭ በል፣ ትንሽ እግሬን ወለም አለኝና ስራ
ሳልሄድ ቀረሁ።» አለች።
«አም ሶሪ ተጎዳሽ በጣም?» እያልኩ ቁጭ ብዬ በውስጤ የሳልኳት ሳራ
እስክትመጣ ጣራ ጣራውን ሳይም፣
«አንተ ነህ አይደል ዳዊት?» ትለኛለች
«አዎ እኔ ነኝ፣ ሳራስ የት አለች ነው ወይስ አንቺ ነሽ?»
«ሳራ እኔ ነኝ፤»
«እኔም እኔ ነኝ፡፡»
ተሳሳቅን። ዕድሜ፣ ስራችንን፣ የወር ገቢያችንን፣ የምንጠላውን፣
የምንወደውን፣ ወዘተ… ቋቅ እስኪለን ድረስ አወራን። የእውነት ግን ለመናገር በስልክ ውስጥ የሳልኳት ሴት አይነት አልነበረችም።
እሷም እኔን እንደዚያ። እናም ጨዋታችን ሁሉ ለዛ እያጣ ሲመጣ፣
«ባሌ እንዲሆን የምፈልገው ሰው አድርግልኝ ያልኩትን ሁሉ የሚያደርግልኝ፣
ሁንልኝ ያልኩትን ሁሉ የሚሆንልኝ ሰው ነው። »
«አንቺስ እሱ ያለሽን ሁሉ ልትሆኚ ዝግጁ ነሽ?»
«እኔን አይመለከትም፡፡» (ፍርጥም ብላ)
«እንዴት ምን ማለት ነው?»
«በ…ቃሀ። እኔ ብቻ፤ ለምሳሌ ማታ ቴሌቪዥን እያየ ከሆነ ቲቪውን ጥፍት
አድርጌበት ወደ መኝታ ክፍሌ እየጎተትኩት ስሄድ ጸጥ የሚለኝ፣ ደግሞ ጋዜጣ እያነበበ ከሆነ ጋዜጣውን ንጥቅ አርጌው እንዲያወራኝ
ስፈልግ ደስ ብሎት ሚታዘዘኝ፣ እ…ህ… ደግሞ አንዳንዴ አለ አይደል… ደስ ሲለኝ በጥፊ ሳጮለው ስቆ ዝም የሚለኝ ወዘተ…»
«እንግዲያውስ አንቺ ሰው ሳይሆን «ሮቦት» ነዋ የምትፈልጊው?» ተናድጄ
ነበር። ሳቀች።
‹‹አይ አንተ ሮቦት አልክ››
‹‹አንቺ የምትመኝው ወንድ በምድር ላይ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡››
«ሞልቷል፡፡ ምራቁን የዋጠ ስንት አለ መሰለህ፡፡ በዚያ ላይ አንተ በእድሜ
አትበልጠኝም፣»
ቀድሞ ይሄን አውቄ ኖሮ ይሄን አውቄ አስቀድሜ "ከሌላ ሰው አንድ
አምስት አመት ተበድሬ" ሰላሳ አመቴ ነው ብያት ነበር።
«እሱስ እውነትሽን ነው። ግን ለትዳር የግድ ወንዱ መብለጥ አለበት እንዴ?»
«አዎ። ምክንያቱም እኩያሞች ከሆንን እንናናቃለን። ለምሳሌ አንተ ብትመታኝ
ዝም አልልህም፣ መልሼ ነው የምደረግምብህ።»
«አስቀድሞ ነገር በባልና ሚስት መካከል ጠብ ያለሽ በዳቦን ምን አመጣው?»
«አንዳንዴማኮ ይኖራል፣ አለ አይደል እንደ የፍቅር ዱላ አይነት ነገር
ያስፈልጋል።»
ብዙ አወራን፣ ብዙም ተፈላሰፍን፤ ይሁን እንጂ የሁለታችንም አሳብ
እንደ ሰሜንና ደቡብ ዋልታ ሳይገናኝ ቀረ። በመጨረሻም፡-
«እንግዲህ እኔና አንቺ አልተመቻቸንም መሰል፤»
«መሰለኝ፡፡»
«ታዲያ ሌላ ሰው፣ አንቺ የምትፈልጊው አይነት ሰው ባመጣልሽ ፈቃደኛ ነሽ?»
(አንድ እሷ እንደምትፈልገው አይነት በእድሜ ገዘፍ ያለ፣ ከወደግንባሩ ገባ ያለ ወዳጄ ታውሶኝ፡፡)
«ደስ ይለኛል ስልኬን ስጠው፡፡»
ሰጠሁት።
የለም የለም እሷ ራሷ ይዘከው ና ባለችኝ መሠረት ይዤው ቤቷ ድረስ ከተፍ
አልኩ እንጂ። ወዲያውም ተግባብተው፣ እኔንም ረስተው ለብዙ ሰዓታት አወሩ። ልጅቱ ከድሮው ቃሏ አንዳችም ፍንክች አላለችም።
ትዳር የሞረሞረው ወዳጄም የምትይው ሁሉ ልክ ነው እያለ፣ እሷም ደስ እያላት ከቆይታ በኋላ ተመቻቹ። ግንኙነታቸውም በፍጥነት
ተጀመረ። ዕነሆም የፍቅርን ሀሁ አሀዱ ማለት ጀመሩ፡፡ ከጊዜያት በኋላም ያን ሰው አገኘሁትና፡-
«የትዳሩ ጉዳይ እንዴት እየሄደልህ ነው?»
«ጥሩ ነው፣ እስካሁን ደህና ነን፣ ግን ምን እንደምትል ታውቃለህ?»
«አላውቅም።»
«ጠንቀቅ በል፣ ትለኛለች።»
«ምን ማለት ነው?»
«ፍቅር እንዳይዝህ ተጠንቀቅ፤»
«እንዴት?»
«እንጃ፡፡»
«እንዲህ ስትልህ ታዲያ አንተ ምን ትላታለህ?»
«ምን እላታለሁ አንቺ ራስሽ ተጠንቀቂ እላታለሁ እንጂ»
«እውነትህን ነው?»
«አዎ ግን ለራሴ ነው በሆዴ። ለሷ ባፌ እሺ እጠነቀቃለሁ እላታለሁ፤ እኔ ግን
በሆዴ ባክሽ ራስሽ ተጠንቀቂ እላታለሁ።»
«የማያጠግብ እንጀራ፡፡» አልኩ ለራሴ። በቃ የትም ድረስ መጓዝ እንደ ማይችሉ
አንዳች ነገር ሹክ አለኝ። በሌላ ጊዜ ቆይቶ ተገናኘን ከዚሁ ወዳጄ ጋር።
«ዘንድሮስ እንዴት ናችሁ?»
«አንተ ደግሞ የሞተ ዘመድ የለህም እንዴ?... የመቸውን?»
«እንዴት … ተለያያችሁ እንዴ?»
«አዎ ሳንጋባ ተፋታን።»
ከዚያን ጊዜም በኋላ ትዳር በደላላ እንደማይሆን ተረዳሁ።
ብዙ ጊዜ በደላላ የሚሆን ነገር ስለ ሚደልሉለት ቁስ አሊያም ሰው ያለ ባህሪው
ነገሩ ሁሉ እንደ ደላላው ስሜትና ሐሳብ የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው። ሊደልሉለት ያሰቡትን ዕቃ አሊያም ሰው ከአሪፍነቱና
ከመልካምነቱ አጋነው ከመለፈፍ ውጪ በጎ ያልሆነ ጎኑን ሲናገሩ ፈጽሞ አይታወቁም፡፡
በሌላ አነጋገር ከአንድ የትዳር አገናኝ ቢሮ ወይም ደላላ ሚስት
አሊያም ባል እንዲያዘጋጅላችሁ ስትዋዋሉ፣ የሴትዮዋን ወይም የሰውዬውን ‹‹እንከን የለሽ›› ማንነት በተባ አንደበቱ እያጎላ
ድካማቸውን እያሳነሰ አንዳንዴም ፍጹም መልአክ እያደረገ ነው፡፡ (በርግጥ ተመዝጋቢዎቹም ቢሆኑ ደካማ ጎናቸውን
ባይናገሩም)፡፡ ይህ ደግሞ በመሥፈርት /Criteria / ላይ ብቻ የተመሠረተ ትዳር ፍቅር አልባ ስለሚሆን ሰኞ ተጋብተው
ማክሰኞ መለያታቸው አይቀሬ ነው፡፡ በመስፈርትና ማንነት፣ በብርና ዘር፣ በዕውቀትና ዝና የተመሠረተ ፍቅር- ከእለታት
አንድ ቀን ነፋስ እንደጎበኘው እብቅ ይሆናልና መጠንቀቅ ነው፡፡
ስለዚህ ምን ይሁን?… ሰው ቆሞ ቀረ፣ ሴቶች ባል አጡ፣ ወንዶች ሚስት አጡ፣
ወቅቶች ተላለፉ፣ ማግባት ያለባው ሰዎች ጊዜያቸው እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ፈጠነና ንቦችና፣ ቢራቢሮዎች እንደተውት የደረቀ አበባ
ሆኑ...
ታዲያ እግዚአብሔር በዚህ ጉዳይ የረሳንና ስለእኛ የማይገደው ከመሰለን አቋራጭ
መፍትሔ እንጠቀምን?… በእጅ ስራ ወይም በ ‹‹አዶቤ ፎቶሾፕ›› ያበደ ፎቷችንን አሜሪካና አውሮፓ አገራት በ ‹‹ፌስቡክ›› ና
ለዚሁ ዓላማ በተሰሩ ድረ ገጾች እንበትንን… ወይስ…?
እንደኔ እንደኔ እንዲህ አይሁን ይልቁንስ እኔ የእግዚአብሔር ነኝና፣
እግዚአብሔርም የእኔ ነውና፣ ደግሞም ከወንድም ይልቅ አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ ነውና፣ ችግሬን ለርሱ ልንገረው፡፡ ከእኔ መሻት
በላይ ሊያደርግ የታመነ አምላክ ነውና፡፡
ዛሬ ዛሬ የብዙዎችን የፍቅር ጎጆ፣ የአያሌዎችን የትዳር በር መለያየት
የሚያንኳኳው፣ ጥላቻ የሚገነጥለው፣ ጥርጣሬ የሚበረብረው፣ አለመተማመን የሚያወላግደው ለምንድነው?… ባንድም በሌላም፣ አስቀድሞ
የእግዚአብሔር ክቡር አሳብ ስለሌለበት ነው፡፡ የእግዚአብሔት ፈቃድ በሌለበት ግንኙነት ውስጥ ስላለፍን ነው፡፡ እግዚአብሔር
ያለበት በሚመስል፣ ነገር ግን ጨርሶ እርሱ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ስለምናልፍ ነው፡፡
ውበት አይተን፣ ቁሳቁስ አይተን፣ ገንዘብ አይተን፣ የአውሮፓና የአሜሪካ ውሀ
ተጠምተን ዘው ብለን ስለምንገባበት ነው፡፡ ከመጋረጃው በስተጀርባ ያለው ኃቅ ይሄ ነው፡፡
አንዴ አንዱ እግዚአብሔር እንዴት በትዳር እንደባረከው እየነገረኝ ነበር
እናም፡-
‹‹እግዚአብሔር እኮ ትዳር ሰጠኝ››
‹‹ውይ በጣም ደስ ይላል፣ ለመሆኑ ማናት?››
‹‹ይህቺውልህ›› (ፎቶዋን እያሳየኝ)
‹‹በጌታ ናት በራሷ?››
‹‹በጌታ ናት፡፡››
‹‹የየትኛው ቸርች አባል ናት?››
‹‹እሱን እንኳ አላውቀውም፡፡››
‹‹እንዴት?››
‹‹ውጪ አገር ስለምትኖር፡፡››
‹‹ጥሩ እንዴት አገኘሃት ታዲያ?››
‹‹በዘመድ፡፡››
‹‹አብራህ የቆየችውን እጮኛህንስ ምን ታደርጋታለህ?››
‹‹ትቀራለቻ፡፡›› (ቆጣ ብሎ)
‹‹እንዴ እስካሁን አብራችሁ ተጉዛችሁ፣ አታዝንብህም?››
‹‹ምን ችግር አለው?... አላገባኋት?››
‹‹እግዚሀርስ አያዝንብህም?››
‹‹ለምን ያዝናል እጮኛዬ እንጂ ሚስቴ አይደለች፡፡››
‹‹የክፉ ቀን ደራሽህኮ ናት፡፡››
‹‹በክፉ ቀን የታዘዘ ሁሉ ይደርስልሀል፣ አሁን አሁን ሳስበው አልወዳትም
ነበረ፡፡››
‹‹ታዲያ ለምን በጊዜ አልነገርካትም?››
‹‹እውነተኛዋ ሚስቴ እስክትመጣ ታስፈልገኝ ነበራ፡፡››
‹‹አ…ሀ… ባጣ ቆይኝ ነበረች ማለት ነዋ፡፡››
‹‹ተወኝ ባክህ፡፡ ደግሞም ‹ሚስት ማለት በረከት ናት ይላል› መጽሐፉ፡፡››
‹‹እጮኛህንስ ካገባሀት የት ይቀራል?… በረከት ለመሆን የግድ አውሮፓና
አሜሪካ መሄድ አለባት እንዴ?››
ከወዳጄ ጋር አልተግባባንም፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላም በስውር አግብቶ በስውር
ካገር ወጣ፡፡ ያሳዝናል… ያቺ ምስኪን እጮኛው ግን ምን ብላ ይሆን?... ዳግም ወንድን ታምን ይሆን?... እሱስ እንዳለመው
በረከት አግኝቶ ይሆን?... እንጃ፡፡
እግዚአብሔር ትክክለኛ የትዳር አጋራችንን ለማግኘት ባልተኬደበት መንገድ ላይ
እንድንሄድ አይደለም ዓላማው፡፡ ችግሩ ያለው ለኛ ያለውን የከበረ ዓላማ ምን እንደሆነ መረዳትና አለመረዳቱ ላይ ነው፡፡ ያን
ለመረዳት ደግሞ ብዙ መጓዝ አይጠበቅብንም፤ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ብቻ መግለጥ በቂ ከበቂም በላይ ነው፡፡ እግዚአብሔር በዘመናት
መካከል ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ እዚያ ላይ ሰፍሯልና፡፡
ለመሆኑ ክርስቶስ ኢየሱስ ቤተክርስቲያንን /እኛን/ ሲወድ በምን መስፈርት
ነው?... መስፈርትስ ነበረን ወይ?... ዕውቀት ወይስ ውበት፣ ዝና ወይስ ሐብት… ጽድቅ ወይስ ቅድስና?… አንዳችም ወደርሱ
የሚያቀርብ ነገር አልነበረንም፡፡
የክርስቶስ ልብ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ ሰውን ሁሉ ለመውደድ አንዳችም ቀመር
ያላስፈለገበት ልብ፡፡
ውበት መስፈርታችን ለሆነ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውበት ከንቱ እንደሆነ
ይናገራል፡፡ ‹‹ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው፣ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርሷ ትመሰገናለች፡፡››
(ምሳሌ ተግሳጽ 31(7)፡30)
በመልኳ ስለምትመጻደቅ፣ ነገር ግን ከወደ ጥበቡ ወገቤን ለምትል ሴትም እንዲህ
ይላል፤ ‹‹የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደሆነ፣ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት፡፡›› (ምሳሌ 11፡22)
ደግሞም በሌላ ስፍራ ላይ፡ ‹‹ልባምን ሴት ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቁ እጅግ ይበልጣል፡፡››
(ምሳሌ ተግሳጽ 31(6)፡10)
ዛሬ ዛሬ ሰዎች ትዳራቸው ጠዋት ታይቶ ከሰዓት እንቶ ፈንቶ የሚሆንበት ዐቢይ
ምክንያት ዕውቀት እያገቡ፣ ሐብት እያፈቀሩ፣ ቁስ እያገቡ፣ ውበት እያፈቀሩ ነው፤ እንጂማ የሰው ልጅ ለአምላኩ ሕግ ተገዢነቱ
ቢታይለት በቤተክርስቲያን ውስጥ ቆመው የቀሩ ወገኖቻችን ሁሉ እማና አባወራ በሆኑም አልነበር?
ምናልባት የጽሁፌ ታዳሚዎች ለትዳር መፍረስኮ አንተ የጠከስከው ብቻ አይደለም
ምክንያቱ ሌላ ጉድ አለ ሊሉ ይችላሉ፣ እውነት ነው፤ አውቃለሁ፤ ያንን ያልጠከስኩት ከጽሁፌ ዓላማ ጋ ስላልሄደልኝ ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም እንዲሉ ነገሬን ሳጠቃልለው
በአጭር ቃል ትዳር በደላላ በህልም ዓለም ቂቤ እንደመጠጣት ከንቱ ምኞት ዓይነት ነው፡፡ ይልቁንስ አስተዋይ ከእግዚሀር ደጅ ዝም
ብሎ ይጠናል፡፡ በጊዜውም አለጊዜውም፡፡
No comments:
Post a Comment
ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡