ሰሞኑን አንድ ጽሁፍ እያነበብኩ ሳለ ለብዙ ጊዜ በመንፈሳዊ ሙዚቀኞቻችን ላይ አንዳች እል ዘንድ የሚጎተጉተኝ ሀሳብ ተቀሰቀሰና ብዕሬን ከሰገባው መዝዤ ከብራናዬ ወደርኩ፡፡
አንድ በትርፍ ጊዜው በሙዚቃ መሣሪያ ጨዋታ እግዚአብሔርን ‹‹ከሚያገልግል›› ወዳጄ ጋር ለዘወትር የማንስማማበት አንድ ነጥብ አለ፡፡ ሁልግዜ ብዙዎቹ የቤተክርስቲያን ሙዚቀኞች መንፈሳዊ ዕውቀት ይጎላቸዋል፣ ከእምነታቸው መመሪያ ከመጽሀፍ ቅዱስ ይልቅ ለኪቦርዳቸውና ጊታራቸው ያላቸው ግንዛቤ ያየለ ነው፡፡ በሚከረክሯቸው ክራሮች፣ በሚደረድሯቸው በገናዎች፣ በሚደልቋቸው ከበሮዎች፣ በሚገዘግዟቸው መሰንቆዎችና በሚነፏቸው ዋሽንቶች ባያሌው የተካኑ በመሆናቸው አድናቂዎቻቸውና አጨብጫቢዎቻቸው የትየለሌ ናቸው፡፡ ግና እንዳለመታደል ሆኖ ነፍሳቸው መንፈሳዊ የውሀ ጥም ያንገበገባት ፣ የጥበብ ምንጯ የደረቀባት፣ የማስተዋል ጅረቶቿም ከነጠፉባት ጥቂት የማይባሉ ክረምቶችና በጋዎች ያለፉባት ናት፡፡
አንድ ጊዜ በአንዲት ቤተክርስቲያን አዳራሽ ውስጥ መባ እየተሰበሰበ ሳለ ሙዚቀኞቹ ከመድረክ ላይ እንደተሰየሙ (ብዙ ‹‹ቸርቾች›› አሁን አሁን ካንድ ኪቦርድ ይልቅ ሙሉ ‹‹ባንድ›› እየተጠቀሙ ነውና) በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበረ አንድ ፈጠን ያለ ስልት ያለው ሙዚቃ እያሰሙ ነበር፡፡ በኋላም መባው እንዳለቀ በሙዚቀኞቹ የመሳሪያ ጨዋታ የተደመሙ ምዕመናን ባንድ ድምጽ ከጣራ ያለፈ ሆታ፣ ፉጨትና ጭብጨባ ያጎርፉላቸዋል፤ ሙዚቀኞቹም የተመልካቹ አድናቆትና ጭብጨባ ከደማቸው ዘልቆ ኖሮ ያለቅጥ ተነቃቅተው ፊታቸው ሁሉ ጥርስ በጥርስ ሆኖ ሳለ፣ መጋቢያቸው አንድ ነገር ብሎ በደስታቸው ላይ ውሃ ቸልሶበታል፡፡ ‹‹ምናለ ይሄ ጭብጨባ ለጌታ ቢሆን… ሙዚቀኞችኮ መንፈስ የላቸውም፡፡›› በዚህን ጊዜ ያ ሁሉ ጭብጨባ፣ ሆታና ፊሽካ ከምኔው ልሳኑ ተዘጋና የሙዚቀኞቹ ፊት አሸቦ ነዛበት፡፡ መጋቢው መቼም እንዲህ ያለው ሙዚቀኞቹን ቀርቦ ስለሚያውቃቸው ነው፡፡ የመድረክ ላይ ጀግኖች የጓዳ ቡከኖች መሆናቸውን ስለተረዳ ነው፡፡ ምናልባት ሁሉን ማጠቃለሉ ቢከብድም፡፡ ያንድ ሙዚቀኛ ዜማና፣ የበገና ድርደራ የእግዚአብሔርን ክብር የማንቀሳቀስና መንፈሱን የማውረድ ብቃት አለው፡፡ ዳዊት ገና በገናውን ሲደረድር ነበር የእግዚአብሔር መንፈስ የሚወርድበትና የሳዖል ክፉ መንፈስ የሚቀሰቀስበት፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔርም ሆነ ሰይጣን ሙዚቃንና ሞዛቂዎቹን በብርቱ ጉዳይ የሚሻ*ቸው፡፡ አንዲት አገር በጠላት ስትወረር በመሪዎቿና በጦር አበጋዞቿ እዝነ ህሊና ለቅስቀሳና ‹‹ፕሮፓጋንዳ›› ቀድመው የሚታወሷቸው ሞዛቂዎችና ከያኒዎች ናቸው፡፡ ፈላስፋዎቹም ‹‹ሙዚቃ የነፍስ ምግብ ናት፣ የዓለም ቋንቋ ናት፣ ወዘተ…›› እያሉ ሲፈላሰፉ ይስተዋላሉ፡፡ እርግጥ ነው ሙዚቃ ኃያል ናት፤ መልካም ተደርጎ የተሰራም ሙዚቃ ሐኪሞች ለበሽተኞቻቸው እንደ ኪኒና የሚያዙላቸው፣ እንደ መቅመቆ ይጋቱት ዘንድ ግድ የሚሏቸው ሙዚቃ አድምጥ/ አድምጪ እያሉ ነው፡፡በሙዚቃ ከጭንቀት፣ ከድብርት የሚያመልጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ምንያህል የክርስቶስ ተከታይ ሙዚቀኞች ይሄ ነገር እንደገባቸው አላውቅም፡፡
አንድ ታዋቂ ዘማሪን ለመጀመርያ ጊዜ ለማየት እሱ በተገኘበት የመዝሙር ኮንሰርት ላይ በታደምኩበት ሰዓት፤ ለማየት የጓጓሁለት ዘማሪ ትቼ፣ በከበሮ መቺው ጥልቅና እምቅ ችሎታ ተመስጬ ለደቂቃዎች ያህል የነበርኩበትን እስክረሳ ድረስ የሆንኩትን ነገር አልረሳውም፡፡ እስከዛሬ ከማውቃቸው ታምቡር ደላቂዎች ዋነኛው ነበር፤ ታዲያ ምን ዋጋ አለው መላ ቀልቤን ያስረሳኝ ያ የሙዚቃ መሣሪያ ሊቅ፣ ቀን ቀን ከመቅደሱ ማታ ማታ ከቤተ ዳንሱ ‹‹እንደሚያገለግል›› ስረዳ፤ ምናልባት ‹‹ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም፡፡›› የሚለው ብሂል ለርሱ አይሰራ ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡
ብታምኑም ባታምኑም ብዙ ወጣት የቤተክርስቲያን ሙዚቀኞችን ዓለም በገንዘቧና በብልጭልጭ ከንቱ ማንነቷ ከቤተክርስቲያን ጉያ እየነጠቀች ነው፡፡ አንዳንዶች ጨርቄን ቅሌን ሳይሉ ጠቅለው ከቤቷ ሲገቡ፣ አብዛኞቹ ደግሞ ምን ችግር አለው እያሉ ለሁለት ጌቶች እየተገዙ ናቸው፡፡ ለዚህም ዋቢ ይሆኑን ዘንድ ብዙ ስመ ገናና ሙዚቀኞችን በተለይም የምዕራቡ ዓለም ዝነኞችን መጥቀስ እንችላለኝ፡፡ ለምሳሌ እንደ ቢዮንሴ፣ … ከአገራችን ደግሞ እነ ኤልያስ መልካ፣ ናትናኤል ኃይሌ፣ ካሙዙ ካሣ፣ አማኑኤል በቀለ፣ ወዘተ…
እዚህ ላይ ከሁለት ሺ አመት በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ ለወጣቱ አገልጋይ ጢሞቴዎስ የጻፈለትን ማንሳት ብልህነት ነው፡፡
‹‹ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ ከኃይማኖት ተሳስተው በብዙ ስቃይ ራሳቸውን ወጉ፡፡ አንተ ግን የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከዚህ ሽሽ፣ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናናትንም የዋህነትንም ተከታተል፡፡ መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፣ የተጠራህለትንም በብዙ ምስክሮች ፊት በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሀለው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ነቀፋ ሆነህ ትዕዛዙን ጠብቅ፤…›› (ጢሞ. 6፡10-16)
ነገር ግን ቤተክርስቲያን እንደ ጳውሎስ አይነት አባት በናፈቀችበት በዚህ ዘመን ‹‹ወጣት ሙዚቀኛ ልጆቼን የበላ ጅብ አልጮህ አለ›› እያለች ትገኛለች፡፡ ምንም እንኳ ልጆቿን ለጅብ የዳረገችውና የምትዳርገው እርሷ ብትሆንም ቅሉ፡፡ ስንቱ ሙዚቀኛ ‹‹እግዚአብሔርን አገልጋይ›› ተብዬ ቅዳሜ ማታ ማታ በደሊላ ጭን ውስጥ ገንዘብ እየሞቀ በረከሰ ማንነቱ ንስሀ እንኳ ሳይገባ ማለዳ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ጆሮ እንደ ሚያደነቁር ቤት ይቁጠረው፡፡
እዚህ ላይ የአንዲት ቤተክርስቲያን ሙዚቀኛ የገጠመውን ማንሳት ወደድሁ፤ ጥቂት ከቤተ ጭፈራ (Night Club) ክርስቲያን ሙዚቀኞችን ለመመልመል ቸርች የመጡ ሰዎች ቀልባቸው ከአንደኛው ሙዚቀኛ ላይ ያርፋል፡፡ ከአገልግሎት በኋላም ይተዋወቁትና አድናቂዎቹ እንደሆኑና በሙያው ምን ያህል እንደተካነበት ልብን በሚያቀልጥ የለዘበ ቃል ሲያማልሉት፤ የሙዚቀኛው ልብ ጠራራ ጸሐይ እንደጎበኘው ቂቤ ይቀልጥ ገባ፤ የኋላ ኋላም መልማዮቹ በሚዛን ላይ ያስቀመጡለት የብር መጠን ቤተክርስቲያኑ ለትራንስፖርት እያለች በየሳምንቱ ከምትሸጉጥለት ሀምሳና መቶ ብር ጋር ስለማይመጣጠን እንደምንም ብሎ ራሱን ያሳምንና አንድ እግሩን እዚያኛው ጫፍ ላይ ይሰቅላል፤ ቅዳሜ ማታ ማታ እጭፈራውና ዘፈኑ ቦታ፣ እሁድ ማለዳ ማለዳ ደግሞ በእግዚአብሔር ቤት፡፡
የማታ ማታ
የቅዳሜ ሌቱ - ሁካታ
የእሁድ ማለዳው - እርካታ
ቢያሳጣው እፎይታ፤
ሳይወድ በግድ ተመለሳታ፡፡
አዎ መዝሙሩና ዘፈኑ እየተደበላለቀበት፣ ህይወቱ በውሃ ላይ እንዳለ ኩበት ብትሆንበት፤ ሳይዘገይ ገንዘብንና ኢየሱስን ሚዛን ላይ መዘነ፤ ኢየሱስም ሚዛን ደፍቶ ተገኘ፤ ከዚያም ‹‹አይ በቃኝ፡፡ ከንግዲህ ወዲያስ አይለምደኝም፣ ለእስካሁኑም እግዚአብሔር ይቅር ይበለኝ…›› ብሎ እስከወዲያኛው ላይመለስ ወዳባቱ ቤት በሄደበት እግሩ ተመልሶ መጥቷል፡፡ ሙዚቀኞች ከሌላ ክርስቲያን ይልቅ አገልግሎታቸው በመድረክ ላይ በመሆኑና እሰው አይን ለመግባት ቀላል በመሆናቸው በጠላት ወጥመድ ለመጠመድ እጅጉን የቀረቡ ናቸው፡፡ ሙዚቃ ደግሞ ዲያብሎስ በእግዚአብሔር ላይ ባደረገው ‹‹ኩዴታ›› ምክንያት ከክብሩ ሳይሽቀነጠር አምላኩን ያገለግልበት የነበረ የሥራ ዘርፍ በመሆኑ ከማንም በላይ ሙዚቀኛ አገልጋዮችን ከቆፈረው የጉድጓድ ወጥመድ ሊያገባቸው ይሻል፡፡ ያ ቀደም የነገርኳችሁ ወዳጄ አገልግሎ ከመድረክ ሲወርድ፣ አያሌ እንስቶች አድናቆታቸውን ሊገልጹለት ‹‹ተሰልፈው›› እንደሚጠብቁት ሁሉ ሳይገልጽልኝ አላለፈም፡፡ እኔም ታዲያ ጠላት ምንያህል በሰዎች ሆኖ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር እየዘረፈ እንዳለ አስተውያለሁ፡፡
ብዙ ከቤተክርስቲያን የሚፈልሱ ሙዚቀኞቻችን ዓለም ላይ ተጽእኖ ማሳደር ከሚችል ትልቅ አቅማቸው ጋር ሲኮበልሉ ቤተክርስቲያን ጉዳዩን ከመጤፍ የቆጠረችው አትመስልም፡፡ እንጂማ እንዲያ እያማለለና እያባበለ የሚጎትታቸውን የነዋይ ፍቅር ዕነሆ ጥማታችሁ ብላ ከወዲሁ ባቀረበችላቸውም አልነበር?… ነገር ግን እንዳለመታደል ሆነና በብዙዎቻችን ዘንድ ‹‹የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፡፡›› የሚለው ጥቅስ ለወንጌላዊያን፣ ለመጋቢያንና ለቄሶች ብቻ ነው የሚመስለን፡፡ እንጂማ ካንድ የተሳካለት ነገር በስተጀርባ እኛ የማናውቀው አካል እንዳለ ሁሉ ለወንጌላችን በእግሩ መሮጥ የሙዚቀኞቻችን አስተዋጽኦ ታላቅ እንደሆነ መገመት አስቸጋሪ ባልነበር፡፡
ዮሐንስ መጥምቁን እሚያህል የአምላክ መልዕክተኛ አንገቱ እንዴት ተቀላ?… ብለን ብንጠይቅ ይኸው ከአንዲት ትንሽ ልጅ ጉሮሮ የተንቆረቆረና ንጉሥ ሄሮድስን ከዙፋኑ ያነቃነቀ ሙዚቃ ነው፡፡ ጳውሎስና ሲላስ በወህኒ ታስረው ሳሉ በመንፈቀ ሌሊት ሲዘምሩ ነበር በታላላቅ ጋኖች ተከርችሞ፣ በክንደ ብርቱ ጠባቆች ይጠበቅ የነበረው አይበገሬው የወህኒ በር ወለል ብሎ የተከፈተላቸው፡፡()
በትንፋሹ፣ በእጆቹና በእግሮቹ እግዚአብሔርን ሲያገለገልና ህዝቡን ሲባርክ የነበረን ሰው ዓለምና ሰይጣን ሲያገኙት ካዳሚያቸው ነው የሚያደርጉት፡፡ በርሱም ስራ ኃጢያት ይነግሳል፣ ክፋት ይሞገሳል፣ ርኩሰት ይወደሳል፡፡ ለዚያም ሰው ኃጢያት ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል፣ የድንጋይም ወፍጮ ባንገቱ ታስሮ ወደባህር ቢጣል ይቀለዋል፤ ብዙዎች በርሱ የተነሳ ተሰናክለዋልና፡፡
ሙዚቀኞቻችን ከፈንጂ ወረዳ እንዳለ ወታደር ናቸው፡፡ እያንዳንዷ እርምጃቸው ከየትኛውም ሰው ይልቅ በአደጋ የታጀበች ናት፤ ለምን ቢሉ ‹‹ሙዚቃ ስለሆነ የሚሰሩት፡፡›› ነው መልሱ፡፡ ደግሞም ሙዚቃን ይመለኩበትና ይወደሱበት ዘንድ እግዚአብሔርም ሰይጣንም ይፈልጓታልና፡፡ እንዴት ቢሉ ሙዚቃ የሰው አንገት ያስቆርጣል፣ የወህኒውን በር ያስከፍታል፣ ለህመምተኛው ፈውስ ይሆናልና፡፡
አንድ ዘወትር ጌታን አምኖ ይድን ዘንድ አጥብቄ የምጨቀጭቀው ወንድሜ ለምን በኢየሱስ ማመን እንዳቃተው ሲነግረኝ፡- ‹‹ጌታን ብቀበል በወደድኩ፤ ነገር ግን ጌታ የማይወዳቸውን ነገሮች ትቼ ትቼ አንድ ነገር ያቅተኛል፤ ያም ዘፈን ነው፡፡ የዘፈን ነገር አይሆንልኝም፡፡›› ነበር ያለኝ፡፡
ሳይንቲስቶች እንኳ በቅርቡ ‹‹መልካም ተደርጎ የተሰራ ጥዑም ዜማ እጽዋት ሰምተው መልስ ይሰጡበታል፤ ይነቃቁበታልም፡፡›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
መንፈሳዊ ሙዚቃ አቀናባሪው ጌታያውቃል ግርማይ ባንድ ወቅት ስለዜማ ሀይለኛነት ሲናገር ‹‹አንድ ጊዜ አንድ የማላውቀው ዜማን በፉጨት አንጎራጉር ነበር፤ በኋላ ያ በፉጨት ቀኑን ሙሉ ሳንጎራጉር የነበረውና፣ ከማቀናብራቸው የዝማሬ ዜማዎች አንዱ የመሰለኝ ዜማ፤ ለካ ሳላውቅ ታክሲ ውስጥ በጆሮዬ የተጋተው ዘፈን ነበርና፡፡››
እንግዲህ ዘፈንም ሆነ መዝሙር ለሚሰራቸው፣ ለሚሰማቸውና ለሚጠቀማቸው ደግሞም ለሚዘፍንላቸውና ለሚዘምርላቸው አካሎች አንዳች ነገርን ያከናውኑ ዘንድ ከፍተኛ ብቃት አላቸው፡፡ ታዲያ ዘማሪዎቻችንም ሆኑ ሙዚቀኞቻችን በሚገባ ሊጠነቀቁ የሚያሻቸው አይመስላችሁምን?
ለሙዚቀኞች ከምንም በላይ የሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ዕውቀትና ህይወት ነው፡፡ እግዚአብሔርም ከምንም በላይ ከእነርሱ የሚፈልገው የሙዚቃ ዕቃቸውን ጩኸትና ድምጽ ሳይሆን የእነርሱን ምሥክር ያለው ህይወት ነው፡፡ ምክንያቱም ካልተሰራ ማንነት የሚወጣ ቃልም ሆነ ዜማ ያልተሰራውን ሰው ሊሰራ ምንም ሀይል አይኖረውምና፡፡ ሙዚቀኞች ሊጸልዩ ይገባል፡፡ ነገር ግን ለብዙ ሙዚቀኞች ጸሎት ማለት ተበላሽቶ የቆመን መኪና ገፍቶ የማስነሳት ያህል ነው፡፡ እንጸልይ አሊያም ጸልዩ ሲባሉ እሺ ይላሉ ነገር ግን ሲጸልዩም ሆነ ሲያጸልዩ ብዙ ጊዜ አይስተዋሉም፡፡ የጸሎት ህይወታቸው በሌሎች አገልጋዮች ላይ የተደገፈ ነው፡፡ የሙዚቃ መሣሪያቸውን በሚጫወቱባቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ላይ የሚደረገው ጸሎት ብቻውን ለነርሱ በቂ ነው የሚመስላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን ጸሎት ከክርስትና ህይወታችን አንዱና ዋነኛው ክፍል እንደሆነ በብዙ ስፍራዎች ላይ አጽንቶ ይናገራል፡፡ (ማር 14፡38)
እንግዲህ የማይጸልይ ሙዚቀኛ ጠላት ጣቶቹን አሊያም ትንፋሹን ተጠቅሞ ዘፈን አያሰራውም ወይ?… ሌላ ነገር ነው፣ ግን የማይጸልይ ሙዚቀኛ፣ መግቢያቸው ዘፈን የሚመስሉ ወይም ሙሉ በሙሉ ኮፒ ፔስት የተደረጉ ስራዎችን ላለመስራቱ ምንም ማረጋገጫ አይኖረንም፡፡ ደግነቱ ብዙ ሙዚቀኞቻችን ጊዜያቸውን እስቱዲዮ ውስጥ መሽገው አሊያም ኪቦርዳቸው ላይ ብቻ አቀርቅረው ስለሚውሉ ለብዙ የሐሰት ትምሕርት የተጋለጡ አይደሉም እንጂ፤ እንደ አሸን የፈሉት የዘመኑ የሐሰት ትምህርት አራማጆች ባገኟቸውና ከመረባቸው በጣሏቸው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ወጣቶቹ በቂና ማንኛውንም በእግዚአብሔር አሳብ ላይ ተነስቶ ሊያስክድ የሚቋምጥን ትምሕርት የሚመቱበትና የሚመልሱበት የቃል ዕውቀት የላቸውምና ነው፡፡
እኔ አንድም ሙዚቀኛ ወደቤተክርስቲያን ሲሄድ መጽሐፍ ቅዱስ በጁ ይዞ ሲሄድ አይቼ አላውቅም፡፡ (በርግጥ ይህ ነገር ፋሽን ሆኖ ዛሬ ዛሬ ብዙ መጽሐፍ ቅዱስን የያዘ ክርስቲያን ማየት እየቀረ ቢሆንም፡፡) በርግጥ ወደ ቸርች ሲሄዱና ሲመጡ መጽሐፍ ቅዱስ መያዝ ለእግዚአብሄር ቃል እውቀት መመዘኛ ባይሆንም፤ ነገር ግን ማንኛውም ክርስቲያን ወደ ቸርች ሲሄድ መጽሀፉን ይዞ ቢሄድ ሰባኪው የሚለውን ሰሚ ብቻ ሳይሆን አንባቢም ጭምር ነው ይሆናል፡፡ እንግዲህ ችግሩን ነቅሰን አውጥተን አየን፤ መፍትሔውስ ምንድነው?… ሙዚቀኞቻችን ምን ቢመቻችላቸው ነው ፍልሰታቸውን የሚያቆሙት?… እንደኔ እንደኔ ቤተክርስቲያን ፈዛለች፡፡ ጫጩቶቿን ከአውሬና ከጭልፊት በክንፎቿ እንደምትሸሽግ እናት ዶሮ መሆን አቅቷታል፡፡ ቸልተኝነት፣ ንፍገትና ስንፍና ተጠናውቷታል፡፡ ገንዘብ አይተው በተጣመመው መንገድ የሚሄዱትን ልጆቿን የሚፈልጉትን ሰጥታ መመለስ ትችል ነበርና፡፡ አዚምና ድንዛዜ ተጫጭኗታል፡፡ በጸና የእግዚአብሔር ቃል ትምሕርት ማስታጠቅና ለገንዘብ ፈተና እንዳይጋለጡ ማድረግ ትችል ነበርና፡፡ ለትራንስፖርት እየተባለ የሚመደብላቸው ሀምሳና መቶ ብር ከዚያኛው ቤት መስኮት ወደውስጥ ከመቃኘት አያስመልጣቸውም፡፡ ይሄን ስል ታዲያ ምንም እንኳ ከግብጽ የሚቀርብላቸው ሽንኩርትና ዱባ የትየለሌ ቢሆንም እነርሱ ግን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በምደረበዳ መራብን የመረጡ አያሌ ሙዚቀኞች እንዳሉን ሳልክድ ነው፡፡ ደግሞ ጥቂት ቤተክርስቲያኖች ለሙዚቀኞቻቸው እንደ መጋቢያኑና ወንጌላዊያኑ ድርጎ ሠፍረዋልና እግዚአብሔር ይባርካቸው፣ ዘግይተውም ቢሆን ባነዋልና፡፡
በመጨረሻም እናንተ ሙዚቀኞች ሆይ፣ አበው
‹‹በሬ ሆይ በሬ ሆይ
አይተህ ሳሩን
ሳታይ ገደሉን›› እንዲሉ ምንም እንኳ የምትሄዱበት ስፍራ ለምለም፣ ስታዩት ለመብላት የሚያሥጎመዥ ቢሆንም በውስጡ ግን ሞት አለበት፤ ባንዴ የማይገድል፡፡ ስለዚህ በህይወት እስካለን ድረስ ያለንን የምሕረት እድል በመጠቀም ልንወጣ ያሰብን በይቅርታ፤ የወጣንም በንስኃ ልንመለስና የጽዮኑን ጉዞ ልንቀጥል ይገባናል፡፡
ዘምሮ አዘምሮ
ደልቆ ከበሮ
ክራርን ከርክሮ
በገናን ደርድሮ
ግጥምን ቀምሮ
ዜማን አቀናብሮ
መሰረዝ አለና
ከየሱስ ቀጠሮ፡፡
--//--
ሚያዝያ 20፣2001
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment
ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡