Tuesday, March 13, 2012

ትርጉም፣ የፍልስፍና መጻሕፍትና ተግዳሮታቸው



ዓላማው ሰዎች መጻሕፍትን ያነቡ ዘንድ ማነሣሣት ነው፤ በየአስራ አምስት ቀናት አንድ ጊዜም በተጋበዙ እንግዶችና አባላቱ መካከል በልዩ ልዩ መጻሕፍትና ንባብ ነክ ርእሶች ዙርያ ውይይት የሚያደርገው ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመጽሐፍ ንባብና ውይይት ክበብ ነው፡፡ በዕለተ እሕድ የካቲት 25 ቀን፣ 2004 ዓ.ም. በአምስት ኪሎ ብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽም ከውጪ አገር በሚተረጎሙ የፍልስፍና መጻሕፍት ዙርያ ሰፋ ያለ ውይይት አድርጓል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬይሽንስ መምህር የሆኑት  አቶ ተሻገር ሽፈራው  በተነሣው ርእስ ላይ ትንታኔና ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ ቤቱም አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቶበታል፡፡ ዝግጅቱ ከመጀመሩ በፊትም በቅርቡ በሞት ያጣናቸውን አንጋፋና ስመጥር የጥበብ ሰዎች፣ ደራሲና ጋዜጠኞቹ ስብሐት ገ/እግዚአብሔርና ማሞ ውድነህ በሕሊና ጸሎት ታስበዋል፡፡

በየጊዜው ገበያውን በተቀላቀሉትና እንደ አሸን እየፈሉ በመጡት የውጪ አገር የፍልስፍና መጻሕፍት (በአብዛኛው ሰው አጠራር የሥነ ልቡና መጻሕፍት) የትርጉም ሥራዎች በአንባቢያኑ ዘንድ ስለሚያደርሱት አሉታዊ ተጽዕኖ ውይይት ከመደረጉ በፊት፣ አቶ ተሻገር ገለጻቸውን የጀመሩት መጽሐፍ ማንበብ ለምን ይጠቅማል? በሚል ጥያቄ ነበር ፡፡ ከርሳቸው ገለጻ በኋላም ውይይት ተካሂዷል፤ የነበረውም ድባብ  ደስ የሚል ነበር፡፡ አዳራሹ ካፍ እስከገደፉ ጢም ብሎ በመሙላቱም ምክንያት ብዙ ሰው ውይይቱን የተከታተለው ቆሞና በያገኘበት ተቀምጦ ነበር ፡፡

 አቶ ተሻገር ስለ መጽሐፍ ማንበብ ጥቅምና ስለ አንባቢ አይነቶች ሲናገሩ፡- “ጥሩ መጻሕፍት ማንበብ የአእምሮ ብስለትን ያመጣል፤ የመረዳት አቅምን ያጎለብታል፤ ጠያቂነትን፤ ኃላፊነትንና ምክንያታዊነትን ያጎናጽፋል፡፡ ጆን ስናይደር የተባለው ጸሐፊ አንባቢያንን በሦስት ምድብ ይመድባቸዋል፤ ያየውን ሁሉ ዓሳ ነው ብሎ የሚያጠምድ፣ ወይም ያገኘውን ሁሉ አግበስብሶ የሚያነብ ሰው ከመጀመርያው ምድብ ሲፈረጅ፤ ይህ ሰው በዋናነት መጻሕፍትን የሚያነበው ማንበብ ስላለበት ብቻ ነው፡፡ መራጭ አይደለም፡፡ ሁለተኛው አይነት አንባቢ ደግሞ ስለነገሮች መረጃን ለማግኘት የሚያነበው ሰው ነው፡፡ መራጭ ነው፣ ዓላማው መረጃ አግኝቶ ላቅ ወዳለ ደረጃ መጓዝ ነው፤ የራሱ መመዘኛዎች ስላሉት ምን ማንበብ እንዳለበት ያውቃል፤ ነገር ግን ዋነኛ ዕቅዱ መረጃ ነው፡፡ በሦስተኛው ምድብ ውስጥ የሚገኘው አንባቢ ግን ከሁለቱም ለየት ያለ ነው፡፡ የሥነጽሑፍ አዋቂ ነው፤ ስለተፈጥሮ፣ ስለሰው ልጅና ስለሕይወት በተለየ መልኩ ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ዓላማው ማወቅ ነውና፡፡ ምሉዕ ሰብዕና ያለው ሰው ለመሆንም ጽኑ ፍላጎት አለው፡፡”
ከውይይት ተሳታፊዎቹም አንደኛው፡- “አንድ ጸሐፊ መጻሕፍትንና ምግብን ያመሳስላቸዋል፤ ምግብ ሁሉ አንድ እንዳልሆነና የተለያየ ዓይነት ጣዕም እንዳለው ሁሉ መጽሐፍትም እንዲያ ናቸው፡፡ አንድ ጸሐፊ ደግሞ በበኩሉ ሦስት አይነት መጻሕፍት አሉ፤ የሚቀመሱ፣ የሚዋጡ እና የሚሰለቀጡ” ብሎ መጻሕፍትን ከምግብ ጋር አያይዟቸዋል፡፡  ማንበብ ከራስ ታሪክና ባህል ማወቅ ይጀምራል፡፡ የራስን ታሪክ አለማወቅ ትልቅ አደጋ ነውና በማለትም አቶ ተሻገር ከገጠማቸው ተነሥተው ያሉት ነጥብ አለ፡፡

አንዲት በዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምሕርት የምትከታተል የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ለመመረቂያዋ  ይረዳት ዘንድ አስባ፣ ስለሕይወቱ  ቃለ መጠይቅ ልታደርግለት ጋዜጠኛ ዘነበ ወላን ትቀጥረዋለች፡፡ በቀጠሯቸውም መሠረት ስትጠይቀው ሲመልስ፣ ስትጠይቀው ሲመልስ፤ ከባሕር ኃይል ተሰናብቶ እንዴት ወደ ጋዜጠኝነቱ ዓለም እንደገባ ትጠይቀዋለች፤ ዘነበም በ1983 ዓ.ም.  በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ምክንያት እንደሆነ ይመልስላታል፡፡ ጀማሪ ጋዜጠኛዋም “በወቅቱ ምን ዓይነት የፖለቲካ ትኩሳት ነበረ?” ብላ አስገርማዋለች፡፡ የቅርቡን ብቻ ሳይሆን የቆየውንም ታሪክ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በንባብ የሚመጣ ነው፣ ጊዜን ከመጻሕፍትጋ በማሳለፍ የሚገኝ ቁምነገር ነው፡፡”

 ነገር ግን ትውልዳችን ምን ያህል ከመጻሕፍትጋ ያሳልፋል? በየቀበሌውና መንደሩስ ምን ያህል ቤተ መጻሕፍት አሉ? በገዛ ራሳችን ሰዎች የተጻፉስ አገር በቀል መጻሕፍት ምን ያህል በቂ ናቸው? ብለን ብንጠይቅ ለመመለስ አዳጋች አይሆንም፡፡ ህጻን ልጅ ሳለሁ ብዙ ወጣቶች ዳጎስ ያለ መጽሐፍ በጉያቸው ሸጉጠው ሲሄዱ እመለከት ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን የማየው ነገር ሌላ ነው፣ ጫት አለፍ ሲልም ሴት፡፡ ወዴት እየተኬደ ነው? ባንድ ወቅት የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት የነበሩ ስፍራዎች ዛሬ ዛሬ ሌላ ነገር የሚካሄድባቸው እየሆኑ ነው፤ ይህ ነገርስ ዕድገታችንን ሊያመላክት ይችላልን? ብዙ ጊዜ ከውጪ አገር በቀጥታ ቃል በቃል ተተርጉመው የሚቀርቡልን የፍልስፍና መጽሐፍት በአብዛኛው ከባህላችን፣ ወጋችንና ሥርዓታችን ጋር የሚጣረሱ በመሆናቸው ለተርጓሚዎቹም ሆነ ለተደራሲው አስቸጋሪ ናቸው፡፡ የአንዱን አገር ማኅበረሰብ ዕውቀት፣ ባህል፣ ወግና ሥርዓት ላንደኛው ማህበረሰብ አቀብሎ ተለማመደውና ኑርበት ማለት የማይቻል ጉዳይ ነውና፡፡ እዚያ እንደ መልካም ነገር የሚታየው እኛጋ ነውር ሊሆን ይችላል፡፡

በዕለቱ በዋነኛነት የተነሣውም ይኸው ጉዳይ ነው፡፡ እንደ አቶ ተሻገርና የውይይቱ ተሳታፊያን ከሆነም፣ ብዙ የፍልስፍና ትርጉም ስራዎች ትውልዱን እያሳደጉት ሳይሆን ማንነቱን እያሳጡት ነው፡፡ የነኦሾና ዶክተር ራምፓ አይነት መጻሕፍት ምናልባት በተጻፉባቸው ኅብረተረሰብ ባህልና ወግ እሰየው አበጃችሁ ሊባሉ ይችሉ ይሆናል፤ እንደኛ ዓይነት ከብዙ ብሔርና ብሔረሰብ ለተውጣጣና በሃይማኖት ተኮትኩቶ ላደገ ማኅበረሰብ ግን ፋይዳቸው ያን ያህል አይሆንም፡፡” ነበር ያሉት፡፡

አቶ ተሻገር እንደ ምሳሌ ከተጠቀሙዋቸው ግብዓቶችም ሁለቱን ላካፍላችሁ፡፡ ባንድ የአገራችን ብሔረሰብ ሁለት የወንድ ባልንጀሮች ፍቅራቸው ወሰን ልክ አጥቶ ጥግ ሲደርስ፣  ፍቅረኞቻቸውን በጋራ ይተኟቸዋል ይባላል፡፡ እንግዲህ እዚያ ማሕበረሰብ ላይ ተራ የለት ተለት የሆነው ጉዳይ ወደሌላኛው ቢወሰድ ሌላ የባህል ወረራ አሊያም መጥፎ መስተጋብር ሊያስከትል ይችላል ማለት ነው፡፡
አንድ ጊዜ ደግሞ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በአንድ ክልል ላይ ጥሬ ሥጋ መብላት እንዴት ለበሽታ እንደሚያጋልጥ በፊልም የተደገፈ ትምህርት ይሰጥ ነበር አሉ፡፡  ፊልሙ ካለቀም በኋላ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባል ስለፊልሙ ጭብጥ ምንነት ሲጠየቁ የሰጡት ምላሽ “በሁዳዴ ምድር ሥጋ መብላት ለበሽታ ይዳርጋል፤”ነበር፡፡ ወቅቱ የሁዳዴ ጦም ነበርና፡፡

ከውይይት ተሳታፊዎቹም አንዳንዶቹ “ዩኒቨርሲቲዎቻችን በራሳቸው ከተማሪዎቻቸው አቅም በላይ የሆነ የፍልስፍና ትምህርት በመስጠታቸው ብዙ ተማሪዎች አቅላቸውን ይስታሉ፡፡” ብለዋል፡፡  በዘልማድ “ጀዝባ” እየተባሉ የሚጠሩ ብዙ ተማሪዎችም የዚህ ውጤት ናቸው ሲሉ አክለዋል፡፡  አንድ “ጀዝባ” ተማሪ የዩኒቨርሲቲ ትምሕርቱን ለመጨረስ ከሰባት እስከ አስር አመት ሊወስድበትም ይችላል፡፡ ተሳታፊዎቹም ከገጠማቸው ሲናገሩ፡- ካምፓስ እያለን አንድ ጓደኛችን የዶ/ር ራምፓን መጽሐፍ ያነብ ነበር፤ መጽሐፉ ብዙ ማድረግ የማይቻሉ ነገሮችን ሰዎች ይሞክሯቸው ዘንድ የልብ ልብ የሚሰጥ ነው ይባልለታል፡፡ ለምሳሌ፡- “አንተኮ ብረት ነህ፣ እሳት ያግልህ ይሆን ይሆናል እንጂ አያቃጥልህም፡፡” ይላል፤ ታዲያ አንዱ ተማሪ እሳቱን በራሱ ላይ ሞክሮ ያካል ጉዳተኛ ሆኗል፡፡ አንደኛውንም ተማሪ ቀጣይ ኑሮውን በኮርኒስ ውስጥ እንዲያደርግ ገፋፍቶት ላንድ ቀን የዶርሙ ኮርኒስ ውስጥ ካደረ በኋላ በስንት መከራ በእኛ ዕርዳታ ሊወርድ ችሏል ነበር ያሉት፡፡ የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው አክለውም መጻሕፍት የሰውን ሰብዕና የመቀየር ኃይል አላቸው፡፡ ተርጓሚዎች ለመተርጎም ሲነሱ ግባቸው ገንዘብ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ብዙ ጊዜ ታዲያ አንዳንድ ትርጉም የፍልስፍና መጻሕፍትን ስናይ ገበያ ተኮር ተደርገው ከመዘጋጀታቸው የተነሳ ርእሳቸው ይጮሃል፤ ውስጣቸው ግን ባዶ ነው፡፡ በትውልዱ ላይም ይህ ነው የማይባል የማንነት ቀውስ እያሳደሩና የባህል ወረራ እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ግራ የሚያጋቡ የሌላ አገር ባህልና ተሞክሮ ናቸውና በሕይወትና ሰብዕና ላይ የሚያመጡት ተግዳሮት በቀላሉ አይታይም፡፡

 እነዚህ መጻሕፍት እንዴት ባጭር ጊዜ ሀብታም መሆን እንደሚቻል፣ ደግሞም ከስኬት ማማ ላይ እንደሚደረስ ይጠቁማሉ፡፡ ያብዛኛዎቹ ዓላማ ጥረህ ግረህ ብላን ሳይሆን ባቋራጭ ክበር አይነት ነገር ነው ፡፡ ስለሃይማኖትና ባህል፣ ልማድና ወግ፣ ብሎም ፍቅርና ወሲብ አስመልክቶም ከባህላችንና ወጋችን ያፈነገጠ ዕይታ ነው ያላቸው፡፡

ውይይቱ ቀጥሏል፤ አቶ ተሻገርም ለመሆኑ ፍልስፍና ምን ማለት ነው? ሲሉ ለብዙዎቻችን ሩቅና ጠሊቅ የሚመስለውን ጽንሰ ሐሳብ ባጭሩ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፤ ፍልስፍና ከሕይወታችን ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ፍልስፍና በማኅበረሰባችን ውስጥ ያለውን ችግር ወደ ውስጥ ዘልቆ በማየት መፍትሔ ማምጣት ነው፡፡  ለምሳሌ ሕይወት ምንድናት ተብሎ ይጠየቅና ሕይወት እንዲህና እንዲያ ናት እያሉ ትንታኔና ድምዳሜ መስጠት ሊሆን ይችላል፡፡ ከውይይት ተካፋዮቹ መካከል አንደኛው “ፍልስፍና የማንነት ጥያቄ ነው፤ መፈላሰፍ ሲጀመርም እኔ ማነኝ ካለ በኋላ መላ ዕድምተኛውን ፈገግ ያሰኘች ታሪካዊ ገጠመኝ አካፍሏል፤ እንዲህ ነው ገጠመኙ፡፡

 በደርግ ጊዜ ነው አሉ አንድ የወሎ ገበሬ መፈክር አሰማ ተብሎ
“አሜሪካ ትውደም!” ሲል ሠልፈኛው “ትውደም!” ይላል፤
“እንግሊዝ ትውደም!”  ሲል ሠልፈኛው “ትውደም!” ይላል፤
“ሩሲያ ትውደም!” ሲል ግን ሠልፈኛው አጉረመረመ፡፡
“ሩሲያ ትውደም!” ይባስ ብሎ ሠልፈኛው ፀጥ አለ፡፡
“ምንሁናችኋል ጎበዝ ሩሲያ ትውደም! ነውኮ ያልኩት!” ቢል አንድ አዛውንት ድምጻቸውን እየሞረዱ፡-
“ምን ነካህ አያ ሩሲያኮ ዘመዳችን ናት እንዴት ትውደም እንላታለን?” ብለው ቢሉ አስፈካሪው (መፈክር አሰሚው?)፡-
“በምን ሒሳብ ነው ሩሲያ ምትዛመደን ቆቦ ነው ወይስ አላማጣ የተወለደችው?” አለ ይባላል፡፡

አቶ ተሻገር ስለ ፍልስፍና ያንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ አይነት ነገር ሲናገሩም፡- “ፍልስፍና በ Capital ‘‘P’’ (Philosophy) እና በ Small ‘‘p’’ (philosophy) ሲጻፍ የተለያየ ትርጉም አለው፡፡ በ Capital ‘‘P’’ ሲጻፍ እንደ አንድ የዕውቀር ዘርፍ ሲሆን በ Small ‘‘p’’ ሲጻፍ ግን የለት ተለት ሕይወት ይሆናል፡፡ የፍልስፍና አስተሳሰብ ከሕይወትና ኑሮ ጋር የተያያዘ ነው ብለናል፡፡ ደግሞም የ Small ‘‘p’’ ዋን ፍልስፍና (philosophy) ስንጠቀም የለት ተለት ሕይወታችን ይሆናል ስንል አክለናል፤ ለዚህም ለአብነት ያህል ይሆነን ዘንድ ሻላና ዝዋይ አካባቢ የሚኖሩ ያገር ሽማግሌዎችን ፍልስፍና  እንጠቅሳለን” በማለት የሚከተለውን ምሳሌ አጫውተውናል፡፡

አንደኛው አዛውንት ሌላኛውን አዛውንት፡-
“የመሬት መሐሉ የቱጋ ነው?” ብለው ይጠይቃሉ፣
መላሹም “እዚህ እኔ የቆምኩበትጋ ነው ከፈለግህ ከግራና ቀኝ ለክተህ ማረጋገጥ ትችላለህ፡፡” ይላሉ፡፡ እንዴት አይነት አስገራሚ ነገር ነው?. . . የመሬት መሐል እኔ የቆምኩበትጋ ነው፣ ከፈለግህ ዙሪያ ገባዬን ለክተህ አረጋግጥ፡፡ ድንቅ አይደለም? . . . ጠያቂው አዛውንት ይቀጥላሉ፤ “የፈረስህ ፀጉር ብዛት ምን ያህል ነው?” መላሹም፡- “የአንድ ጆንያ ጤፍን ያህል ነው፡፡ ከፈለግህ ለክተህ አረጋግጥ፡፡” ይላሉ፡፡ እንዲህ አይነቱ ፍልስፍና የማረጋገጥን ዕዳ ወደሌላው የማስተላለፍ ሒደት ነው ይባልለታል፡፡ አለቃ ገብረሐና ፈላስፋ ነበሩ፤ ነገር ግን የተሸነፉት ባንዲት ልጃገረድ ፍልስፍና ነው፡፡ እንዲህ ነው የሆነው፤  አለቃ በእንግድነት የዚያች ልጃገረድ ቤተሰብ ዘንድ አርፈው ኖሯል፤ በኋላም ልጃገረዲቱ ለመኝታቸው አጎዛ አንጥፋ “አለቃ ይተኙ!” ብትላቸው አለቃ የአጎዛዋን አናሳነት ተመልክተው፡-“አዬ ልጄ ይበቃኛል ብለሽ ነው?” ብለው ቢጠይቋት ልጃገረዲቱ “ሲጨርሱ ይጨመርልዎታል!” ብላ ቆሌያቸውን ገፋዋለች ይባላል፡፡ እንዲያውም አፈታሪክ እንደሚለው አለቃ ገብረሐና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው መፈላሰፋቸውንና መቀለዳቸውን ያቆሙት፡፡
© ይህ ጽሁፍ በመጠኑ ተሻሽሎ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በእሁድ እትም መጋቢት 2፣ 2004 ዓ.ም. የወጣ ነው፡፡


No comments:

Post a Comment

ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡