ሰዎች ስለሕይወት ያላችሁ ትርጉም እንዴት ነው? ተብለን ስንጠየቅ
እንደየማንነታችን የምናስቀምጠው የሕይወት ፍልስፍና ይኖረናል። ምንም እንኳ የሁላችንም አመለካከት ለየቅል ቢሆንም
ቅሉ፣ ማጠቃለያችን አንድ ያደርገንና በኖህ መርከብ እንደነበሩት እንስሶች ያዛምደናል።
እኔም
በተለያዩ የህ/ሰብ ክፍሎች የሕይወት ትርጉም ስትቃኝ ምን እንደምትመስል ለማወቅ ፈልጌ በያጋጣሚው የማገኛቸውን በተለያየ ሙያ
ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ላናግር ሞክሬያለሁ፤ እስቲ አብረን እያንዳንዳቸው እንደየግብራቸው የሚሉትን እንስማ።
፩
በመጀመርያ
ያገኘኋቸው ቀዶሐኪም ናቸው። የሕይወት ትርጉም በርስዎ እይታ እንዴት ነው? ብዬ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ መልስ ከመስጠታቸው በፊት
ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል ይዘውኝ ሄዱ፤ እዚያም ስንደርስ የሙያ ባልደረቦቻቸው አንድ የቀዶ ጥገና ህክምና ሊያደርጉ በዝግጅት ላይ
እንዳሉ ተመለከትኩ። ሁሉም ጌሾ ቀለም ያለው የመለያ ልብሳቸውን ለብሰው አፋቸውንና አፍንጫቸውን ሸፍነውና ጓንታቸውን አጥልቀው
ቀጥሎ ሊያደርጉ ያሉትን ነገር ሊያደርጉ አንድ ነገር የሚጠብቁ ይመስላሉ።
እኔም
እንደ ሐኪሞቹ ከለበስሁ በኋላ የሚሆነውን ለማየት እችል ዘንድ ዕድል አገኘሁ። በቀዶ ጥገናው ጠረጴዛ ላይ ህመምተኛው ተኝቷል።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም በፍጹም ጸጥታ ስራው ተጀመረ። ህመምተኛው ማደንዘዣ ተወጋ፤ ከዚያም አንደኛው ሐኪም የመቅደጃ ቢላቸውን
ይዘው ወደህመምተኛው ራቁት ሰውነት ተጠጉ። ቢላዋቸውንም ልቡ አካባቢ ሲያሳርፉ አይኖቼን ጨፈንሁ። ጥቂት ቆይቼም ስገልጥ
አካባቢው በደም ጨቅይቶ ኖሮ ረዳት ሐኪሞቹ ደሙን እያደራረቁና አስፈላጊውን ነገር እያደረጉ ናቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላም
የህመምተኛው ልብ እንደ ኳስ እየነጠረች ታየችኝ። ከዚያም በኋላ ቀጥሎ ያለውን ነገር እመለከት ዘንድ አቅም ስላነሰኝ በድጋሚ
አይኖቼን ከደንሁ።
«ለእኛ
ቀዶሐኪሞች የሕይወት ትርጉም በቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ይጎላል። አየህ የሕይወትና የሞት ሽረት የሚታየው የሐኪሙ ቢላዋ
በህመምተኛው ሰውነት ውስጥ ዘልቆ ከገባበት ሰዓት አንስቶ ነው። የሰውዬውም ዕጣ ፈንታ ያኔ ይወሰናል። የሕይወቱ ገመድ ወይ
ይረዝማል አሊያም ያጥራል። ያኔ ነው እንግዲህ የህይወት ምንነት፣ የመኖር አስፈላጊነት፣ ምን ያህል እንደሆነ የምረዳው።»
በማለት ሐኪሙ ከቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ እንደወጣን መነጽራቸውን በማውለቅ አይናቸውን ያሻሹ ጀመር።
፪
«ሰማዩ
ከምድር ሲላቀቅ፣ የወፎች መንጫጫትን ተከትሎ ከአድማስ ባሻገር ማለዳ ጀምበር ፍንጥቅ ስትል ከመኝታዬ በመነሳት የአትክልት
መሣሪያዎቼን ይዤ ወደ አትክልቶቹ ስፍራ እሄዳለሁ። እዚያ ስደርስም…» አሉኝና አትክልተኛው እንደ ኤደን ገነት
የሚያምረውን የአትክልት ስፍራ ዙሪያ ገባውን ገረመሙት። ከዚያም ፈገግ እያሉ…«እዚያ ስደርስ ታዲያ ሕይወት ሕይወት ይለኛል
መኖር መኖር ይሸተኛል። አፈሩን እየኮተኮትሁ አረሙን ስነቅል፣ አበባ እየተከልሁ የተጠሙትን ሳጠጣ፣ የወደቁትን እየደገፍሁ
የተሰበሩትን ሳቀና የሕይወትን ጣፋጭ ትርጉም፣ የመኖሬን እውነት እወደዋለሁ። እነዚህ የምታያቸው የዛፍ ችግኞች የእኔ ህይወት
እየለመለመች ትሄድ ዘንድ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ለእኔ አንዲት ችግኝና የሰው ሕይወት ተመሳሳይ ናቸው።
ሕይወት ደግሞ ካለ እጽዋት ባዶ ናት።» በማለት ችርችም ብሎ ወደበቀለው ጥድ መቀሳቸውን እያንቀጫቀጩ ተለዩኝ።
፫
በሰፊው
ግቢ ውስጥ ቀያዮቹ የእሳት አደጋ መከላከያ መኪኖች ግምባራቸውን ወደ ግቢው መውጫ አፍጥጠው እንደ ኃያል ሠራዊት በተጠንቀቅ
ቆመዋል። ግቢውን እንደ ዘለቅሁም በመደዳ ከሚታዩት ቢሮዎች ውስጥ ወደ አንደኛው ጎራ አልኩ። ቢጫ የእሳት መከላከያ ቱታ
የለበሱና ቆብ የደፉ የድርጅቱ ዋነኛ ሠራተኞችም እየተሯሯጡ መኪኖቹ ላይ መሳፈር ጀመሩ። በወቅቱ ሁሉም በጥድፍያ ላይ ስለሆኑ
እኔን ከቁብ ቆጥሮኝ የሚያናግረኝ ሰው አልነበረምና ዝም ብዬ ምክንያቱን ለማወቅ ወደ አንደኛው መኪና ሳመራ አንደኛው ሠራተኛ
እየተጣደፈ «ፈጠን ብለህ ግባና እንሂድ» አለኝ። ሳላመነታም ገባሁ። ወዲያውኑ እኔ ከነበርኩበት ጋራ ሁለት መኪኖች በከፍተኛ
ፍጥነት የአደጋ ኡኡታቸውን እያሰሙ ከግቢው ተፈተለኩ።
ከአደጋው
ስፍራም ስንደርስ አካባቢው በጭስ ጉም ታፍኖ ነገር ሁሉ አይታይም ነበር። ወዲያውም መኪኖቹና ሠራተኞቹ ወደተግባራቸው ሲሰማሩ እኔ
ጥጌን ይዤ እየሆነ ያለውን እመለከት ገባሁ።
ብዙ
ጩኸትና ዋይታ ከአካባቢው ይጎርፋል። እንደ ጀማሪ ፍቅረኞች ተቃቅፈው የተሰሩ ቤቶች በእሳት እየጋዩ እንዳሉም አሁን ግልጽ
እየሆነልኝ መጣ። ከረጅም ሰዓት የማጥፋት ትግል በኋላም እሳቱ ጠፍቶ ሁሉም መረጋጋት ሲጀምር ወደ አንደኛው የእሳት አደጋ
ሠራተኛ ቀርቤ የተለመደ ጥያቄየኝ ሰነዘርኩለት።
እጅግ
ተዳክሞ ስለነበረ ብዙ ሊለኝ አልቻለም። ብቻ «አሁን ካየኸው ሌላ የምልህ የለኝም። ሕይወት ከመቼውም የበለጠ በንደዚህ አይነት
ሰዓት ትርጉሟ ፍንትው ብሎ ይታይሀል። በተለይማ ከእሳት ላንቃ ውስጥ አንዲትን ነፍስ መንጭቀህ ስታወጣ፣ ጣፋጭነቷ ምን ያህል
እንደሆነ ትገነዘባለህ።» ብሎኝ እዚያው እንደተገተርኩ ወደ መኪኖቹ አመራ።
፬
የመወዳደሪያው
ስፍራ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ሰዎች ተጨናንቋል። ታዋቂና ስመጥር ሯጮች፣ ስፖርቱን የሚወዱ ሯጮች፣ ለመሮጥ ብለው የሚሮጡ ሯጮች፣
የድሉን አክሊል ለመሸለም የሚሮጡ ሯጮች፣ ለተሳትፎ የሚሮጡ ሯጮች፣ ከታዋቂ አትሌቶች ጎን እየሮጡ ካሜራ አይን ውስጥ ለመግባት
የሚሮጡ ሰዎች… ብቻ ሁሉም አሉ።
የውድድሩ
ፊሽካ ተነፋ፤ ህዝበ ዓዳም እየተግተለተለ ይሮጥ ገባ፤ ማራቶኑ ተጀመረ። ግማሽ ኪሎ ሜትሩም ሳይጠናቀቅ ከአራቱ ሁለት እጅ ያህሉ
ወደየት እንደገቡ ታጡ። ገና አርባ አንድ ኪ.ሜ. ያህል ይቀራል። አሁንም ጥቂት እንደተሮጠ ቀርቶ ከነበረው ሲሶው ያህል ረገፈና
በጣት የሚቆጠሩ ሯጮች ብቻ ቀሩ።
በመጨረሻው
ዙርም አንድ ሰው እጆቹን እንደ ክንፍ ዘርግቶ ክሩን ሲበጥስ ተስተዋለ። ይህን ሰው ቀርቤም ሳስተውለው አርባ ሁለት ኪሎ ሜትሯን
ጥጥት አርጎ ገና ምንም ያልሮጠ መስሎ ይታያል። ደግሞም «ለእኔ የሕይወት ትርጉሟ የሚፈታልኝ በንዲህ አይነት ወቅት ነው።»
የሚል ይመስላል።
፭
ነገር
ዓለሙ ጸጥ ረጭ ባለበት ትልቅ የመቃብር ስፍራ ውስጥ ነኝ። ጸጥታው የሚባላ አፍ ያለው ይመስላል። ግቢውን ካጣበቡት
መቃብሮች ጋራ ተዳምሮ ዝምታው ነፍሴን አራዳት።
አንዳንድ
ጊዜ በሐውልቶች ላይ የሚጻፉ የህይወት ታሪኮችን ማንበብ ያስደስተኛልና፣ እያነበብሁ በሁለት ልብ ሆኜ ስራመድም፣ ከቅርብ ርቀት
ድም… ድም… ድም…. የሚል ድምጽ ይሰማኝ ጀመር። ስፈራ ስቸር አይኖቼን ድምጹ ከሚመጣበት አቅጣጫ ስወረውር አንድ አካሉ
የፈረጠመ ሰው መቃብር እየቆፈረ ነው። በቀስታም ወዳለበት ሳመራ ዱክን ሰምቶ ኖሮ ቀና ብሎ ተመለከተኝ። በፊቱ ላይ
የተንቸረፈፈው ላቡ ትናንሽ ቦዮች እየሰራ በመጨረሻም አንድ ትልቅ ቦይ በመስራት ይቀላቀልና በአገጩ ጫፍ እየተንጠባጠበ ከመቃብር
ጉድጓድ ውስጠ ወጥቶ በተቆለለው አፈር ይመጠጣል።
«የሕይወት
ትርጉሟ ከአስክሬንና የመቃብር ጉድጓድ ጋር የተያያዘ ነው።» አለኝና ጨወታውን ጀመረልኝ።«የሕይወቴ ድውር የተጠነጠነው
ከሙታኖች መንደር ነው። እነዚህ ሁሉ መቃብሮችም የእኔ እንጀራ የተጋገረባቸው ናቸው። ህይወቴ የምትረካውና መኖሬን የምወደውም
ጥሩና ያማረ የሬሳ ጉድጓድ የቆፈርኩ ዕለት ነው።
፮
ምንም
ፊደል ያልተጻፈበት ጠመኔ ይዤ ወደ ማስተምርበት ክፍል ስገባ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ አስተውላለሁ። አዲስን ነገር
ሊቀበል በተዘጋጀ ዓዕምሮ ውስጥ አንዳች ነገር ማስቀመጥ፣ መጻፍ ወይም ማተም። እንዲያ የሚሆነው ታዲያ ጠመኔዋን ከጥቁር ሠሌዳ
ጋር በማገናኘት ለማስተማር አሀዱ ስል ነው። ጠመኔዋ አንድ ፊደል፣ ሁለት ፊደል እያለች ቃል ከቃል፣ ሐረግ ከሐረግ፣ ከዚያ
ዓረፍተ ነገር በመጨረሻም ምንባብን ስትጽፍ፣ እየተፈረፈረች እየቦነነች እያለቀች ትመጣለች። ታዲያ ጠመኔዋ ስታልቅ ለተማሪዎቼ
እንግዳ ነገር አስገንዝባ አንዳች ነገር አስጨብጣ መስዋዕት ሆና ነው።
ሕይወትም
እንደ ጥቁር ሰሌዳ በምመስላት ዓለም ላይ የራሷን ፊደል ከትባ፣ የራሷን ቃላትና ምንባብ መስርታ ትከስማለች። በሰሌዳው ላይ ያለ
ጽሁፍ ግቡን ከመታ በኋላ በማጥፊያ ለሌላኛው ትምህርት ይጻፍበት ዘንድ እንደሚጠፋ ሁሉ ሕይወትም አንዴ የምድር ላይ ቆይታዋን
ካሳካች በኋላ በሞት ትጠፋለች። ሌላ አዲስ ሕይወት መጻፍ /መፈጠር/ አሊያም መተካት አለበትና፤ ታዲያ ሕይወትን ስመለከታት
በሁለት ነገር እመስላታለሁ የመጀመርያው ሊጻፍበት እንደተዘጋጀ፣ ወይም እየተጻፈባት እንዳለ፣ አሊያም እንዳለቀ ጠመኔ ሲሆን
ሁለተኛው ደግሞ በጥቁር ሰሌዳ ላይ እንደተጻፈ ምንባብ። ትርጉሟም የሚገባኝ በጠመኔዬ የዘራሁት ዘር በቅሎ ሲያፈራና የቀለም
ልጆቼ ግማሹ ሐኪም፣ ግማሹ መሐንዲስ፣ ከፊሉ ያገር መሪ ወዘተ ሲሆን ነው።
፰
ከጠራው ሰማይ ስር የጠራ ውሀ አለ።
በውሀው ዳር ካለው አሸዋ ላይ ወንዶችና ሴቶች ፣ ህጻናትና አዋቂዎች በየፈርጁ ጸሐይ እየሞቁ ሲታዩ ከፊሎቹ ደግሞ እየዋኙ ነው።
ከነርሱ እንደ አንዱ ለመሆን ፈለግሁና ወደነበሩበት አመራሁ። በዚህን ጊዜም በባህሩ ውስጥ እየዋኙ ከነበሩት ሰዎች አካባቢ
ግርግርና ሁካታ ተፈጠረ። ሁናቴውንም ለማወቅ እየሮጥኩ ሄድኩ።
«አሁንኮ አጠገቤ በሰላም እየዋኘ
ነበረ፤ ሳያውቀው ወደ ጥልቁ ወርዶ ነው የሰመጠው።» ይላል አንድ ሰው የልቅሶ ቃና ባለው ድምጽ። በርግጥ የሚያለቅሰው ሰውዬ
ፊቱ በእምባ ይታጠብ አይታጠብ አያስታውቅም እየዋኘ ስለነበረ።
ከጥቂት ጊዜም በኋላ አንድ ሰው
የሰመጠውን ሰው ተሸክሞ እየዋኘ ወደ ዳር ሲመጣ ታየ። ከውሀ እንደ ወጣም ሰጥሞ የነበረውን ሰው በጀርባው እንዲንጋለል ካደረገው
በኋላ የጠጣውን ውሀ ያስተፋው ጀመር። ሰውየውም ቀስ በቀስ ነፍስ እየዘራ መጣና በመጨረሻ ሊድን ቻለ። እኔም የኋላ ኋላ ነፍስ
ሰውዬው ነፍስ አድን አሊያም life Saver መሆኑን ተረዳሁ።
የሕይወት ትርጉም ለእርሱ በውቅያኖስ
ላይ እንደምትጓዝ መርከብ ናት። መርከቧ ረጅም ርቀት ስትጓዝ የምታርፍበት ወደብ ለመድረስ በማዕበል፣ በአውሎ ነፋስና፣ በግዙፍ
አሳ ነባሪዎች እንደምትፈተን ሁሉ፣ ሕይወትም በጎዳናዋ ላይ አያሌ ፈታኝ ነገሮች ይገጥሟታል። ቢሆንም ግን በውሀ ውስጥ
የሰመጠችን ሕይወት ደርሶ ከሞት እንደ ማስመለጥ ያለ አስደሳች ነገር የለም።
፰
ጥሬው ብረት ገና መደበኛ ቅርጹን
ሳይዝ ወደ እሳቱ ይገባል። አንጥረኛውም ከሰል በማቀጣጠያው ውስጥ ከጨመረ በኋላ ወናፉን ያናፋዋል፤ ወናፉ ከሰሉን ያፍመዋል፤
ከሰሉም ብረቱን ያግመዋል፤ ያኔም አንጥረኛው የጋመውን ብረት በሜንጦ ይይዝና ያወጣዋል፤ አውጥቶም ከጠፍጣው መቀጥቀጫ ብረት ላይ
ያስቀምጠዋል። ክንደ ብርቱው አንጥረኛም በከባድ መዶሻ እየቀጠቀጠ የሚፈልገውን መሳሪያ ቅርጽ ይይዝ ዘንድ ግድ ይለዋል። የኋላ
ኋላም ያ ጉማጅና ቅርጸ ቢስ የነበረ ጥሬ ብረት ከብዙ መቀጥቀጥ በኋላ ማለፊያ ማረሻ፣ ወይም ዶማ፣ ካልሆነም ቢላዋ ወይም ደግሞ
አስገራሚ ፋስ ይሆናል።
አየህ ጥሬው ብረት የሚፈለግበትን
ዓይነትና ቅርጽ ይይዝ ዘንድ በእሳት ውስጥ ማለፍ የግድ እንደሚሆንበት ሁሉ፣ ህይወትም በመከራ እሳት ትፈተናለች። በችግር
መዶሻም እየተቀጠቀጠች ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ትጓዛለች። እናም ለኔ አንድ ተራ ብረትን በእሳት ፈትኖ ቢላዋን አሊያም ድግር
ማውጣትን ያህል የመሰለ ታላቅ እርካታ የለም። የህይወቴ ህይወት እኩል ይሆናል እሳት ሲደመር የጋመ ብረት አበቃሁ።
፱
በምድራችን ላይ በየዕለቱ
መልካቸውንና ዘዴያቸውን እየቀያየሩ ብዙ ወንጀሎች ይሰራሉ። አንዳንዶቹ የወንጀል ዓይነቶች ቀላልና ብዙም የማያለፉ ይሆኑና
ፋናቸውን ለማግኘት ጊዜ የማይወስድ ይሆናል። ሌሎቹ ደግሞ እጅግ ውስብስብ ከመሆናቸው የተነሳ ቀንድና ጭራቸውን ለመያዝ አንድ
የተወታተበ ልቃቂትን የማስተካከል ያህል ይሆናል።
በተለያዩ የወንጀል ምርምር ዑደቶች
ውስጥ የአንድን ውትብትብ ወንጀል ጭራ ለመያዝ አያሌ ቀንና ሌሊቶች፣ ብሎም ብርቱ ጥረትና ትዕግስት ይጠይቃል። ነገር ግን
እውነት ምናልባት ታማ ባልጋዋ ላይ ትውል ይሆናል እንጂ ፈጽሞ ስለማትሞት ፈለግዋን አሽትቶ ለማግኘት ብርቱ ወንጀል መርማሪ
መሆን ያስፈልጋል። ለወንጀል መርማሪዎች እንደተጎለጎለ ማግ የሆነን ውል አልባ ወንጀል እንደ መፍታት የሚያረካቸው ነገር የለም።
፲
በመጨረሻም እኔ ራሴን ጠየቅሁ።
ለእኔስ ለጸሀፊው፣ ለጋዜጠኛው ህይወት እንደ ምንድናት?
ጋዜጠኛ ሆነህ ስትሰራ ዘወትር
ሚዛናዊ የሆነ ዜና ለመስራት የሐቅን ምርኩዝ መደገፍ መቻል አለብህ።
ለምን ቢባል ክምር እውነት የመሰሉ
እውነቶች እጀርባህ ላይ የመርግ ያህል ይጫኑህና መጻጉዕ ሊያስመስሉህ ይችላሉና። ያኔ ታዲያ የሐቅን በትር ጨብጠህ ያልያዝክ
እንደሁ ጉድ ፈላ… በአጭር ቃል አለቀልህ ብልህስ?... ምን እንደሚፈጠር ገመትክ?... እንደ ፍርስራሽ የተጫነህ ወይም ቃሉን
ላሳምርልህና የተቆለለብህ ባዶ እውነት ጨፍልቆና ትንፋሽ አሳጥቶ ይገልሀልና ነው።
ሕይወትም እንዲያ ናት። በኖርካት
ቁጥር አያሌ ቁልሎች፣ ብዙም ክምሮች አሉ። ያጎበጡህና ያስጎበደዱህ። ካጎበጠህ ነገር ቀና ለማለት ደግሞ እውነትን ፈልፍለህ
ስታገኝ ብቻ ነው።
ሚዛኑን የጠበቀ ጋዜጣዊ ስራና ጣፋጭ
ህይወት ይመሳሰላሉ። ሲያጣጥሟቸው ሀቅ ሀቅ እየሸተቱ ነገን መኖር ያስመኛሉና።
ስለህይወት ትርጉም የተለያዩ
የማህበረሰብ ክፍሎች ያሉትን ጽሁፍ ያነበበ ሰውም የሚከተለውን አስገራሚ ደብዳቤ ጻፈልኝ።
ውድ ዳዊት እንደምንአለህ?
ይህቺን መልእክት
የምጽፍልህ ከተለመደው ስፍራ ሆኜ እንዳይመስልህ። ማለቴ ምድር ላይ ከሚኖሩት መካከል አይደለሁም። በእርግጥ ባንድ ወቅት እንደ
አንተና እንደ መሰሎችህ በምድር ላይ ነበርኩ። አሁን ግን ፈጽሞ አይደለሁም። እኔ በሰማዩ ስፍራ የምኖርና ዜግነቴም ሰማያዊ
የሆንኩኝ ነኝ። ምድር ላይ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ አስራሁለቱ ደቀመዝሙሮች አንደኛው ነበርኩ። ኢየሱስንም በጣም እወደው
ነበር። እሱም ወደ አምላኩና ወደ አምላካችን ካረገ በኋላ ከሐዋርያት ጋር ሕይወት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በብርቱ ሰርተናል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በጻፍኳቸውና ለምድር ነዋሪዎች ባበረከትኳው ሶስት መጽሐፎች ማለትም የዮሐንስ ወንጌል፣ የዮሐንስ
መልዕክትና፣ የዮሐንስ ራዕይ እታወቃለሁ። ሐዋርያውና ወንጌላዊው ዮሐንስ ነኝ።
ስለ ሕይወት የተለያየ ሙያ ያላቸው
ሰዎች የሰጡትን ትርጉም አየሁና ቢገርመኝ ነው ይህን የጻፍኩልህ። ወዳጄ ባጭር አነጋገር ሰዎቹ የሚሉትና ትክክለኛው ሕይወት
ትርጓሜ ለየቅል ነው። አንተ ጋዜጠኛው ራስህ ስለህይወት ያለህ ትርጉም ይኼ መሆኑ አሳዝኖኛል።
ዳዊት ለመሆኑ የህይወት ትርጉሙ
እውን እናንተ እንዳላችሁት ነው እንዴ?... ፈጽሞ አይደለም። ትክክለኛው የህይወት ትርጉምን ለማወቅ ትፈልጋለህ?...
እንግዲያውስ ከመደርደሪያህ ላይ አቧራ የጠጣውን መጽሐፍ ቅዱስህን አንሳና አቧራውን አራግፈህ አንብብ። እዚያ ላይ የህይወት
ትርጉም እንደ ማለዳ ጮራ ፍንትው ብሎ ይታይሀል።
በል ታዲያ ትክክለኛውን የህይወት
ትርጉም እንዳገኘህ ለተሳሳቱት ሁሉ የህይወት ትርጉሙ ይኼ ነው ብለህ ከስህተት ጎዳና መልሳቸው።
ወደ እኛ ለመምጣት ትጋ። በጽድቅ
ጎዳና ተመላለስ። የምስራቹን ወንጌል በጊዜውም ሆነ አለጊዜው ስበክ። እግዚአብሔር ይረዳሀል። ጊዜህ ደርሶም ወደ እኛ
እስክትመጣና ሰማያዊ ህይወትህን መምራት እስክትጀምር ድረስ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር፣ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና
የመንፈስ ቅዱስ እውነት ያግኝህ።
ሐዋርያና
ወንጌላዊ ዮሐንስ
ከአዲስቷ
ጽዮን
አስገራሚውን ደብዳቤ
አንብቤ እንደ ጨረስኩ ለዘመናት የመጽሐፍት መደርደሪያዬን ከማጣበብ ውጪ አንዳችም ጥቅም ሰጥቶኝ ወደማያውቀውና አቧራ ወደጠገበው
መጽሐፍ ቅዱስ እጄን ሰድጄ መዝዤ በማውጣት እውነት ማንበብ ጀመርኩ።
እንደ መጀመርያም ለምን የዚህን
ሐዋርያ ሶስት መጽሐፎች አላነብለትም አልኩና ከዮሐንስ ወንጌል ጀመርኩ። በመጽሐፉ የመጀመርያ ምዕራፍም እንዲህ የሚል ቃል
ሰፍሯል።
«በመጀመርያው ቃል ነበረ፣ ቃልም
በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመርያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፣
ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ
አልሆነም። በእርሱ
ሕይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም
በጨለማ ይበራል፣ ጨለማም አላሸነፈውም።»
(ዮሐ. ፩፡፩-፭)
በጣም ተገረምኩ። በእርሱ ሕይወት
ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሀን ነበረች ነው የሚለው። ምን ለማለት ነው? ብዬም ራሴን ስጠይቅ ከጽሁፉ ያገኘሁት መልስ፡-
፩. ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ
መኖሯን
፪. ያም ሕይወት ኢየሱስ መሆኑንና
፫. ሕይወትም ወይም ኢየሱስ የሰው
ብርሀን መሆኗን ነው።
(ንባቤን ቀጥያለሁ። ያነሳሁት ነጥብ
ስለ ሕይወት ትርጉም ነውና፣ ሕይወትን የተመለከተ ነገር ሳገኝ በማስታወሻ ደብተሬ ላይ አሰፍራለሁ። ደግሞም እንዲህ የሚል ቃል
አገኘሁ።)
«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም
ሕይወት እንዲኖረው እንጂ
እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።»
(ዮሐ.፫፡፲፮)
(በጣም የሚገርም ቃል ነው።
የዘላለም ሕይወት ነውኮ ሚለው። እንዴት ያለ ነገር ነው?... በማን ያመነ ነው የዘላለም ሕይወት የሚያገኘው?.... ንባቤን
ልቀጥል፣)
«በልጁ የሚያምን የዘላለም
ሕይወት አለው።
በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።»
(ዮሐ. ፫፡፴፮)
(ምን አለ?... በልጁ
የሚያምን?... በማ ልጅ?... እንዴ ሐዋርያ ዮሐንስ ምን እያለ ነው?... ለማንኛውም ንባቤን ልቀጥል…)
«… ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን
መሆኑንስ ብታውቂ፣ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ፣ የህይወትም
ውኃ ይሰጥሽ
ነበር…»
(ዮሐ. ፬፡፲)
(ምናለ?... የሕይወት ውኃ?...
ሐዋርያ ዮሐንስ ምን ለማለት እየፈለገ ነው?... እውን እኛ ከምናውቀው የምድር ውኃ ውጪ ሌላ የሕይወት ውኃ የሚባል ነገር
አለ?... ይገርማል… እሺ ሐዋርያው በጣም ኃይለኛ «ኢሹ» ነው ያነሳኸው… ·ረ ቀጥልልኝ ትካርህ ጥሞኛል። )
«… እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ
ግን ለዘላለም
አይጠማም፣ እኔ
የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም
ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል
እንጂ።»
(ዮሐ. ፬፡፲፬)
(ሐዋርያው ግራ እያጋባኸኝ ነው።
ኢየሱስ እንዲህ አለ እያልክ ነው ያለኸው። ታዲያ ይህ የምትለው ነገር እንዴት ሰዎች ሳይረዱት ቀሩ?... ለምንስ በምድር ላይ
ብዙ ሐይማኖት ተፈጠረ?... በክርስትና ስር ራሱ እጅግ በርካታ ሐይማኖቶች አሉ፤ ይህ ለምን ሆነ?... ደግሞም የኢየሱስ ዘር
የሆኑት አይሁዶች ራሳቸውኮ አልተቀበሉትም፣ … ለማንኛውም እስቲ ማንበቤን ልቀጥል። )
«እናንተም በመጻሕፍት የዘላለም
ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ እነርሱም
ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው ነገር
ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።»
(ዮሐ. ፭።፴፱)
(ከዚህ በላይ ግራ መጋባት ምን
አለ?... በጃቸው ያለው መጽሀፍ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩና የሚመሰክሩ ከሆኑ፣ ሌላ ኢየሱስ መጠበቅ ስለምን አስፈለጋቸው?...
አሁንስ ቢሆን እየሆነ ያለው እንዲህ አይደለም እንዴ?... ኢየሱስ ብቻ ነው የሕይወት ቁልፉ ተብሎ ሳለ ብዙ ሰዎች ግን ቁልፉን
አጥተውታል። ቁልፉ በጃቸው ሆኖ ሳለ አላስተዋሉትም፣ ወይ ንቀውታልና ሌላ የሕይወት በር ቁልፍ እየፈለጉ ናቸው። ሲገርም…
ለማንኛውም ወደ ንባቤ ልመለስ…)
«ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፡- የሕይወት
እንጀራ እኔ ነኝ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም
በእኔ የሚያምን ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።»
(ዮሐ. ፮፡፴፭)
(እውነታው ግን ብዙዎች ይህንን ቃል
አላነበቡትም ወይም አልበራላቸውም ስለዚህም ኢየሱስ የሕይወት እንጀራን ቸል ብለውታል፤ ዳሩ ሰው ካልታዘዘ፣ ካላነበበና ካልሰማ
እንዴት ቃሉ ይበራለታል?... እኔን ጨምሮ የብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ አቧራ ከመጠጣት አልፎ ሸረሪት አድርቶበታል።)
«ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን
ሁሉ የዘላለም
ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፣ እኔም
በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።»
(ዮሐ. ፮፡፵
(ወይ ግሩም አያችሁልኝ ሌላ
ጉድ?... አያችሁ የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ምን እንደሆነ?... የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የአብ ፈቃድ ነው። ያም በልጁ
ስናምን ብቻ ነው። ደግሞኮ ሞተን አንቀርም ምክንያቱም በመጨረሻው ቀን እኔ አስነሳዋለሁ ይላልና ኢየሱስ። አሁን ሕይወትና
የሕይወት ትርጉም እየገባኝ ነው። ንባቤን ቀጥያለሁ።)
«እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ
የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። የሕይወት
እንጀራ እኔ ነኝ።… ከሰማይ
የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም
ይኖራል እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ስጋዬ ነው።… እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ
ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን
የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም
በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ።»
(ዮሐ. ፮፡ ፶፩-፶፬)
«ሥጋ ምንም አይጠቅምም እኔ
የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።…»
«… ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ
ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም። ኢየሱስም ደግሞ ለ አስራሁለቱ እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?
አለ። ስምዖን ጴጥሮስ፡- ጌታ ሆይ ወደማን እንሄዳለን? አንተ
የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ እኛስ አንተ ክርሰቶስ የህያው
የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት።»
(ዮሐ.፮፡፷፰)
(ታዲያ እስከዛሬ የሄድኩበት መንገድ
ትክክል አይደለም ማለት ነው? … እስከዛሬ ድረስ የዘላለም ሕይወት እንዴት ማግኘት እንዳለብኝ ማንም የነገረኝ አልነበረም።
«ኢቭን» ከናትና አባቴ የወረስኩት ሐይማኖት በራሱ ሰንበትንና በዓላትን ከማክበር ውጪ አንዳችም ቁም ነገር አላስተማረኝም።
የናትና አባቴ ሐይማኖትማ ትልቅ ቦታ ሚሰጠው ለአዳኙ እናት እንጂ ለልጇ እንዳልሆነ ጸሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። … እውነት
ለመናገር ይኸው እስካሁን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ከጀመርኩበት ሰከንድ አንስቶ አንድም ቦታ ላይ ስለ እናቲቱ አማላጅነት የሚናገር
ስፍራ አላገኘሁም። ይልቁንስ የወንጌሉ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ የሚያትተው ስለ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ ምንድነው
ምጠብቀው?... እውን የዘላለም ሕይወት ማግኘት አልፈልግምን?... በጣም እፈልጋለሁ። እንግዲያውስ በኢየሱስ ክርስቶስ ልመና?)
ዳዊት
ወርቁ
1996
ዓ.ም.
አዲስ
አበባ
oh dave God bless u more betam telek neger new geta eyesus zemenehen yebarek banete lay yejemerewen sayecheres ayakomemem blss u!
ReplyDeleteThank you so much. God bless you too.
Delete