Saturday, March 3, 2012

ዜማ እስኪታደስ ጆሮ ዳባ ልበስ


እንደ ብዙ ውሆች ድምጽ ያለ፣ ጋራና ሸንተረሩን አቆራርጦ፣ ገመገሙንና ተረተሩን አሳብሮ፣
ወንዛ ወንዙንና ሰርጣ ሰርጡን ተሻግሮ፣ ሰማያትንና ደመናትን ሰነጣጥቆ፤ እንደ ዕጣንና ከርቤ
ጢስ የንጉሡን እልፍኝ የሚያውድ ነው፤ እኛ ላጤዎች ከየአቅጣጫው ሆነን፣ ከጓዳችን
ተደፍተን፣ ሁነኛ ውሀ’ጣጪያችንን፣ አይን ከዳኛችንን ለማግኘት ለአምላካቸን በእንባና ጸሎት
የምንጽፈው ግጥም ነው ‹‹የትዳር ጸሎት››።

በተለይ በተለይ፣ በመላ ሕይወታችን እግዚአብሔርን ጣልቃ ያስገባን፣ ከእርሱ ፈቃድ ውጪ
ጋት ያህል መራመድ የማይሆንልን፣ ከነፍሳችን ጋር የተቆራረጥን ‹‹ጨካኝ›› ክርስቲያኖችና፤
በሌላ በኩል ደግሞ እድሜያችን ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ የፈጠነብን እህቶችና ወንድሞች
የትዳር ጸሎት፣ የእግዚአብሔርን ፋይል ያጣበበ ነው፡፡ ‹‹ኔትዎርኩ››ም ከምድር ዙሪያ
በምናሰማውም የትዳር ጸሎት ዜማ ከመቸውም ይልቅ የተጨናቀ ይመስላል።

ይሁንና ጸሎታችን መልካም ሆኖ፣ ዓላማችንም የተቀደሰ ሆኖ ሳለ፣ እግዚአብሔር ግን በአንዳች
ነገር ያልተደሰተ ይመስለኛል፤ በጸሎታችን ዜማ ዓይነት።

እኛ ላጤዎች እድሜያችን ላቅመ ሄዋንና ዓዳም ከደረሰበት ዕለት አንስቶ፣ የትዳር ዜማችን
ለዘወትር ከአምላክ ጆሮዎች እንደተጋተ፣ እርሱም ሳይሰለች ‹‹እህ›› እንዳለ አለ፤ ምንም እንኳ
ዜማችንን ካጣጣመና ግጥማችንን ካነበበ በኋላ ጆሮ ዳባ ልበስ ቢልም ቅሉ።

ከዝምታው ጀርባ ግን ማናችንም ደፍረን ያልመረመርነውና ያላጤነው ዐቢይ ጉዳይ ታላቅ
ሚስጥር አለ። ይሁን እንጂ አያሌ ላጤዎች ከዝምታው ተራራ ጀርባ ያለውን አንዳች ቁምነገር
ከማጤን ይልቅ፣ ፈጥነን ነገር ማጠንጠንና ማውጠንጠን እንመርጣለን

የንጉሡ ዝምታ ግን የራሱ የሆነ ከባድ ሚስጥር አለው፤ ልብ ያለው ልብ የሚለው፣ አስተዋይ
እንደ ውሀ የሚቀዳው። እንደ እድል ሳይሆን ግን ብዙ ላጤዎች በዝምታው ተሰናክለን
ካላሰብነው የሕይወት ወጥመድ አዘቅት ውስጥ ስንገባ፣ ጥቂቶች ደግሞ ግጥምና ዜማቸውን
አስተካክለው በመጻፍና በማደስ እንደ ንጉሡ ፈቃድ የሆነ ጣፋጭ ሕይወት ይመራሉ

ለመሆኑ እግዚአብሔር እንዴት ዓይነት የትዳር ዜማዎችን ነው ጆሮ ዳባ ልበስ የሚለው?
እንግዲህ ላጤ ሴቶች ብዙ ጊዜ አጓጉል ዜማ የምንለቀው፣ ዕድሜያችን ገና ለጋ በሆነበትና
ውበታችን ደግሞ እንደ ቆላ አበባ ንቦችን ሁሉ በሚጠራበት ወቅት ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህን ጊዜ
ከሚለቀቁት ነጠላ ዜማዎች መካከል፡-

አምላኬ ሆይ
እኔ ምፈልገው ባል፣
‘አቤት ጉድ!’ ‘ሚያስብል፣
በሐብቱ ወደር አልባ፣
ዝናው ከዳር ዳር ‘ሚያስተጋባ፣
ቁመናው ዛላ፣ ዝግባ፡፡
ሰሀ ማይወጣለት የታደለ ባህሪ፣
አይደለም ከሰው ካውሬ አዳሪ፡፡
አብሮኝ ሲሆን ‘ማያሳፍር፣
በሳር ቅጠሉ ‘ሚያስከብር፡፡
ከራሱ አብልጦ የሚወደኝ፣
ሁን ያልኩትን ሚሆንልኝ፡፡
ሲያመኝ ፈጥኖ ደራሽ ሐኪሜ፣
ስከፋ-ደስታዬ፣ ስጨነቅ፣ሰላሜ፡፡
አንዳች ነገር ስፈልግ ውስጤን የሚረዳ፣
ደርሶ ሚከፍልልኝ የኑሮዬን ዕዳ።

(እግዚሀር እንዲህ ዓይነቱን የጸሎት ዜማ ሲያደምጥ በአግራሞት ጭንቅላቱን ከግራ ቀኝ
እየወዘወዘ «አይ ጸሎት! እንዲም አርጎ ጸሎት የለ!» የሚል ይመስለኛል። ፈገግም እያለ፡-
«ለማንኛውም ዜማው እስኪቀየር መልሳችን ዝምታ ነው።» እያለ በሌላ ጊዜ ቀጠሮ ፋይሉን
ወደ መዝገብ ቤት የሚመልስ፡፡)

ታዲያ ይህ ጊዜ ከአያሌ ትዳር ፈላጊዎች አይን ውስጥ የምትገባው ይህቺ ሴት የመጣውን ሁሉ
አቃቂር እያወጣች፣ ፊት እየነሳችና «ልብ እንቅርት ይመኛል» እያለች፣ አሸማቃ ቀንዷ
እንደተመታ ላም የምትመልስበት ጊዜ ነው። በርግጥ በፈቃዷ ማንም ጣልቃ ባይገባም ለትዳር
ያወጣችውን መስፈርት ግን ባያሌው የሚያሟላ ስለማይገኝ የፈላጊዎቿን ጥላ ገፋና ቀንድ
ሰብራ ማባረር የለባትም።

ወንዶችም ብንሆን ቁመናና ደረታችን፣ ግርማና ሞገሳችን፣ የብዙ እንስት አይኖችን
ሲያንከራትት፣ እየተኮፈስን የምናሰማው ዜማ ይሄን ይመስላል


አምላኬ ሆይ
እኔ ምፈልጋት ሚስት፣
እንደሞናሊዛ
የተጎናጸፈች የውበትን ለዛ፣
እንደ ክሊዎፓትራ
ጠቢብ ልብን የታደለች፣
የስንቱን ናፖሊዮን ጦር’ቃ ያስፈታች፣
ገና ከማለዳው ዕውቀት ከሐብትጋ፣
አሟልታ የሰነቀች ዕምቡጥ ጮርቃ ለጋ።

(አሁንም ለእንዲህ አይነቱ ዜማ እግዚአብሔር ዝምታውን ነው የሚቸር የሚመስለኝ።
ምክንያቱም ከእንስቷ ዜማ በምንም ያላነሰ ነውና።)
በዚህም ጊዜ ልክ እንደ እንስቷ ሁሉ፣ ወደ እኛም አያሌ እንስቶች በትዳር ጥያቄያችን ወራት
ይመጣሉ። ግና የመጡቱ ሁሉ እንደ ተራራ የተቆለለ መስፈርታችንን ስለማያሟሉልን
በመጡበት እግራቸው እንመልሳቸዋለን።
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ዜማችን ወደ ጭቅጭቅና ንዝነዛ የሚቀየረውና ሲብስ ደግሞ ወደ
ማስፈራሪያ ሁሉ ሊለወጥ የሚችለው።

‹‹ አምላኬ ሆይ
ካልሰጠኸኝ የልቤን መሻት
ምወደውን ልጅ
አምላኬ ሆይ
ካልሰጠኸኝ የልቤን መሻት
ምወዳትን ልጅ
ያባቴን ፋንታ
የናቴን ፋንታ
በራሴ ጊዜ
ጉዞ ጀምራለሁ ፍለጋ
ቆላ ሳልል ደጋ
ምናለፋኝ አንተጋ፡፡

(ውይ ማን ተጎዳ!… ባቄላ አለቀ ቢሉ… አሉ። ሂጂ ያሻሽን አርጊ!፤ ሂድ ያሻህን
አርግ!…የሚል ይመስለኛል ፈጣሪ፡፡ በርግጥ የርሱን ልብ ማን አውቆት፣ እንደኛ አይደል
ቸኩሎ ሚወስን፣ ኋላ ሚጸጸትበትን፡)

እንግዲህ እግዚአብሔር በባህሪው ርህሩህና መልካም፣ ሰዎችን የማያስጨንቅ፣ በፈቃዳቸው
ጣልቃ ገብቶ የማያሳዝን ስለሆነ «የልቤን መሻት ካልሰጠኸኝ ሞቼ እገኛለሁ!» ለምንል እርሱጋ
ምን ችግር አለ? ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ ነው፤ የፈለግነውን ይሰጠናል፣ ምንም እንኳ የዝምታው
ሚስጥር መሻታችን በነፍሳችን ላይ ክሳት እንደሚያመጣ ማወቁ፣ ምኞታችን ይዞን እንዳይጠፋ
ቀድሞ መገንዘቡ ቢሆንም፣
በጣም ከነዘነዝነውና ላይኖቹ ዕረፍ ልንሰጣቸው ካልወደድን፣ ለፈቃዳችን አሳልፎ ይሰጠናል።
ታዲያ ለፈቃዳችን አልፈን በተሰጠንና የፈለግነውን ሰው ባገኘን ማግስት አፍታም ሳንቆይ ሌላ
አዲስ ዜማ እንለቃለን፡፡ ለምሳሌ እንስቷ እንዲህ ልትል ትችላለች                

ጌታ ሆይ ያገባሁት ባል
የእሳት ታናሽ ወንድም ነበልባል
አንድዶ ለቀቀኝ
አቃጥሎ ገደለኝ
ባክህ ፍቀድልኝና
እንድፈታው ልብ ስጠኝ ጭንቀቴን እይና፡፡
(እግዚአብሔር ይሄን ዜማ ሲያደምጥ፡- ቀድሞ ነበረ እንጂ መጥኖ መደቆስ፣ አሁን ምን
ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ…ይል ይሆን…እንጃ፣ እሱ ያውቃል፡፡)
ወንዱም በበኩሉ
ፈጣሪዬ ሆይ
የሰጠኸኝ ሚስት
ሚጥሚጣ ናት እሳት
ባክህ ፍቀድልኝ እንድፈታት፡፡
ይላል።

(ወይ ፍርጃ፡፡ ሰውን በመፍጠሬ ተጸጸትኩ ቢል ምን ያስገርማል ታዲያ ?…)
ታዲያ እግዚአብሔር በዚህን ጊዜ ከማዘን አልፎ አይቆጣም ትላላችሁ?
ቢሆንም የፍቅር አምላክ እንደመሆኑ አሁንም የጸሎታችንን ዜማ በትግስት ማዳመጡን
አያቆምም።
እኛ ባለብዙ መሥፈርቶቹ፣ እስከ መጨረሻው ስእላችንን ካላገኘን ወይ ፍንክች ያባ ቢላዎ ልጅ፣
የምንለው የውስጣችን ምኞት ስዕል ብቻ ሆኖ ሲቀርና እኛም ባንድ ወቅት የነበረን፣
የምንመካበት ውበት፣ ሐብትና ዝና መና ሆኖ ሲቀር፤ ዜማችን ወደልቅሶና ጥርስ ማፋጨት
ይቀየርና እንዲህ ማለት ደግሞ ይመጣል፡-

ጌታ ሆይ
ዘመኔ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ሲፈጥንብኝ
ለምን ጨክነህ ዝም አልከኝ?
ይኸው ሳላጋባ
ክረምት አልፎ በጋው ገባ
ሁሌ እየታጠብኩ በእንባ
የልጅ ፍቅር ባይኔ እየዋለ
ጡቴ በናፍቆት እየዋለለ።

(ምጽ!… ከንፈሩን ይመጥ ይሆን እግዚያር?... በጣም ልብን የሚነካ ዜማ ነው፤ የሐዘን
እንጉርጉሮ ቢባል አይሻልም ይሆን?…)

ታዲያ እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነት ዜማ ሲደርስው፡ በርግጥ ሆዱ ይባባል፣ ያዝናል፣
(እንዴት አወቅህ እንዲህ እንደሚሰማው? ካላችሁኝ፣ ከራሴ ስሜት ተነስቼ ነው፤ ያም ማለት
ሲፈጥረኝ የመለኮቱ ባህሪ ተካፋይ አድርጎ አይደል?… ስለዚህ እሱጋ የሌለውን ባህሪ ከየትም
አላመጣውም፡፡ ሌላው ሌላውስ መጥፎ መጥፎ ባህሪ ከየት አመጣነው? ካላችሁኝ፤ እሱ
የስጋችን ፍሬ ነው ነው መልሴ፡፡ ለበለጠ ማስረጃ ገላትያ ምዕራፍ 5 ሙሉውን አንብቡት
ከፈለጋችሁ፡፡)

ግና አሁንም ከዝምታ እልፍኙ እንዳለ ነው፡፡ የግድ ዜማችን መቀየር አሊያም መታደስ
አለበት፤ ግጥሙም ተስተካክሎ መጻፍ አለበትና፡፡
የኛም ተባዕቶቹ ተስፋ ስንቆርጥ ዜማችን ብዙም ከእንስቶቹ የተለየ አይደለም፡፡

ጌታ ሆይ
ሚስት ሳላገባ
ጸጉሬ ኋላ ኪሴ ገባ
ጆሮዎቼ ናፈቁ መስማት ሲለኝ ልጄ ‹‹አባ››
የሰው ልጅ ሳይ ሆዴ እየባባ፡፡
እልፍ ቆንጆ ብትመጣም ተሰብስባ
ምንም አልቻለችም ከ‹‹ታርጌቴ›› ልትገባ
·ረ አጥንቴን ፍለጋ እምን ጉድጓድ ልግባ?

እንግዲህ እንዲህ እንዲህ እያልን ላጤዎች መከራችንን ስንበላ እንቆይና የማታ ማታ ‹‹ለመሆኑ
ከእግዚአብሔር የዝምታ ተራራ ጀርባ ምን አለ?›› ብለን ፋታ ወስደን፣ ለእግዚአብሔር ጊዜ
መስጠት ስንጀምር እንዲያ ‹‹አርባ ዓመት›› ሙሉ ያስጓዘንን የትዳር ሚስጥር፣ ለካ አርባ ቀናት
ብቻ የሚፈጅ እንደነበረ ሚስጥሩን እንደርስበታለን፡፡
ከዚያም የበገናችንን አውታር፣ የመሰንቆና ክራራችንን ቅኝት እናስተካክልና፣ ዳግም ጉሮሯችንን
ስለን ባዲስ ዜማና ስልት፣ ደግሞም ባልተሰማ ግጥም እንዲህ ስንል ወደላይ እናሳርጋለን፡፡

*1. ‹‹ያሳቤ የልቤ ባይሞላም፣
ያልኩት ሁሉ ደግሞ ባይሳካም፣
ላመስግን ልተው ማማረሬን፣
ያልከው ይሁን ያ መልካም ነው ለኔ፡፡
ካንተ ጋር መስማማት ይሻላል፣
ማማረር ማኩረፍ ምን ያዋጣል፣
ሀሳብህ ይሁን ማለት መልካም፣
በጊዜው ነገር ውብ ይሆናል፡፡››



ፈቃድህ እሷ እስክትመጣልኝ፣
ፈቃድህ እሱ እስኪሰጠኝ፣
ደጃፍህ ላይ ሆኜ እጠብቃለሁኝ፡፡
ተረድቻለሁኝ የሰው ማንነቱ፣
ተገንዝቤያለሁኝ የሰው ሰውነቱ፣
እንዳልሆነ ሐብቱ፣
ዝናና ዕውቀቱ፣
ቁመና አካላቱ፣
ረጋፊ ውበቱ፣
ይልቅስ እውነቱ፣
አንተን የመፍራቱ፡፡

*2. <<ውበት ሐሰት ነው ደምግባት ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርሷ
ትመሰገናለች፡፡>>
ዳዊት ወርቁ
2001 ዓ.ም
አዲስ አበባ

የግርጌ ማስታወሻ
*1. ስምንቱ መስመር ስንኝ - ከዘማሪ ዳንኤል አምደሚካኤል፣ ቁጥር አንድ የመዝሙር አልበም
የተወሰደ
*2. መጽሐፈ ምሳሌ 31፣(7)

No comments:

Post a Comment

ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡