በአንድ ማለዳ ወዳጄ ከቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወደ ፒያሳ በሚወስደው መንገድ ላይ ፒያሳ የሚሄድ ታክሲ ከሌሎች ተሳፋሪዎች ጋር ችሎት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በርከት ብለው ይጠብቃሉ፡፡ ሰዓቱ እየረፈደ ነው፡፡ ሁሉም ተሳፋሪ ቶሎ ታክሲ አግኝቶ ወደ ሥራ ይሄድ ዘንድ ጓጉቷል፡፡ ነገር ግን ታክሲዎች በሙሉ ከመነሻው ማለትም ከቀጨኔ መድኃኔዓለም እየሞሉ ስለሚመጡ ችግራቸው የከፋ ሆነ፡፡ በዚህን ጊዜ አንድ ከፒያሳ የመጣ ታክሲ በአጋጣሚ ከመጨረሻው ሳይደርስ መንገድ ላይ ተሳፋሪዎቹን በሙሉ አውርዶ ባዶ ስለነበረ፣ ችሎት አደባባዩ ላይ ያዞርና ወደፒያሳ ለመሄድ ተኮልኩለው የነበሩትን መንገደኞች ማሳፈር ይጀምራል፡፡ በአካባቢው የነበሩ ሁለት የፀጥታ አስከባሪዎች ግን ታክሲው እንዳይጭን ያዙታል፡፡ ‹‹እንዴ ምን ችግር አለው?›› አለ ረዳት፤ ‹‹አደባባይ ላይ ተሳፋሪዎች ወርደው ታክሲው ባዶ ከሆነ እዚህ ብንጭን ምን ችግር አለው?›› አለ ሾፌር፤ ‹‹ምንድነው ችግሩ?›› አሉ ተሳፋሪዎች፤ ‹‹አይቻልም! አዙረህ ሄደህ ከመነሻው ጫን!›› አሉ የፀጥታ አስከባሪዎቹ፡፡
በዚህ መሀል እሰጥ አገባው እየከረረ፣ እየከረረ መጣ፡፡ ‹‹ባዶ አይደለሁ እንዴ? እዚህ ብጭን ችግሩ ምን እንደሆነ ልትነግሩኝ ትችላላችሁ?›› ይጠይቃል ረዳት፡፡ ፖሊሶቹም እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው፣ ‹‹ጭራሽ ችግሩን አስረዱኝ ይላል እንዴ?›› ይሉና አንጠልጥለው ወደ አንድ የግለሰብ ግቢ ያስገቡታል፡፡ አስገብተውም እንደ በርበሬ ደልዘው፣ እንደ ኑግ ወቅጠውና እንደ ተልባ አድቅቀው ባፍና ባፍንጫው ደም ቡልቅ ቡልቅ እያለ ቢልኩት ተሳፋሪዎች በሙሉ በጣም ተገርመውና ደንግጠው፣ ደግሞም ነግ በኔን ፈርተው በሹክሹክታ ‹‹ምን ዓይነት ጉድ ነው መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር ለምን እንዲህ ዓይነት ድርጊት ይፈጸማል? ዴሞክራሲ አለ በሚባልበት አገር እንዴት እንደዚህ ይደረጋል? ታዲያ የቱ ጋ ነው ነፃነት ያለው?›› እያሉ ሲያጉረመርሙ፣ ‹‹የፀጥታ አስከባሪዎቹ›› ሁሉንም ሰዎች አስወርደው ታክሲው ከመነሻው እንዲጭን ፈርደውበታል፡፡ እንግዲህ ሾፌርና ወያላ እንዲሁም ተሳፋሪዎች ለምን? ብለው ስለጠየቁ ነው ይህ ሁሉ ድርጊት የተፈጸመው፡፡
እኔ የምለው?
1. የፀጥታ አስከባሪዎች ሥራቸው ፀጥታ ማስከበር ወይስ ሰላም ማደፍረስ?
2. የፀጥታ አስከባሪዎች ሥራ ችግር መፍታት ወይስ በቆመጥ ሰው መነረት?
3. በሰው ግቢስ ያለፈቃድ ሰውን አስገብቶ መደብደብ ይቻላል?
4. አንድ ሰውስ ጥፋት እንኳ ቢኖርበት በ48 ሰዓታት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት መወሰድ ይገባዋል እንጂ እንዲያ ይደረጋል? ነውር አይደለም?
5. ለሕግ ያልተገዛው እነርሱ ሕግ አዋቂዎቹ ወይስ ሕግ አላወቀም የተባለው ረዳት?
እዚህ ላይ መንግሥት የፖሊስ ሠራዊቱን ሲያሠለጥን በአብሮነት ሕገ መንግሥቱን፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉንና ሌሎች ሕጎችን በሥልጠና ወቅት በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እንደሚያስተምር አልጠራጠርም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመናገር ነፃነት አለመኖር ፈርጀ ብዙ ችግሮች አሉት፡፡ ለምሳሌ እንደ ሰደድ እሳት ለተስፋፋው ሙስና ይህ ዓይነቱ ችግር ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ ሕዝቡ የሙስና ወንጀል እንዳለ ያውቃል፡፡ በዚያ ሰንሰለት ውስጥም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያሉትን አብጠርጥሮ ያውቃል፡፡ ግን በሰዎቹና በሥራቸው ላይ አንዳች ለማለት አቅም የለውም፡፡ ምክንያት ቢሉ ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱ የተገደበ ነውና፡፡ ለደኅንነቱም ይሰጋልና፡፡ ለዚህ ነው ሥርዓታችን እንደ ፍልፈል ውስጥ ለውስጥ የሚሄድን እንጂ ግልጽ የሆነ ማንነትን በሕዝባችን ውስጥ ያላዳበረው፡፡ መንግሥትና ሕዝብ እጅና ጓንት መሆን የሚችሉት መንግሥት አንዳችም ገደብ የሌለበት ሐሳብን በነፃነት የመናገርና የመጻፍ ነፃነት ሲያጎናጽፍ ነው፡፡ አለዚያ ግን በክፍተቱ ንፋስ ይገባና ለጥፋት ኃይሎች መሣሪያ ይሆናል፡፡ ፖሊሲዎቿንና መመርያዎቿን ‹‹ኮማ›› ሳይቀር የምንኮርጅላት አሜሪካ ዴሞክራሲዋን፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመጻፍ ሕጓንም ልንኮርጅላት ይገባናል፡፡
No comments:
Post a Comment
ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡