ውድ ዳዊት እንደምንአለህ?
ይህቺን መልእክት የምጽፍልህ ከተለመደው ስፍራ ሆኜ እንዳይመስልህ። ማለቴ ምድር ላይ ከሚኖሩት መካከል አይደለሁም። በእርግጥ ባንድ ወቅት እንደ አንተና እንደ መሰሎችህ በምድር ላይ ነበርኩ። አሁን ግን ፈጽሞ አይደለሁም። እኔ በሰማዩ ስፍራ የምኖርና ዜግነቴም ሰማያዊ የሆንኩኝ ነኝ። ምድር ላይ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ አስራሁለቱ ደቀመዝሙሮች አንደኛው ነበርኩ። ኢየሱስንም በጣም እወደው ነበር። እሱም ወደ አምላኩና ወደ አምላካችን ካረገ በኋላ ከሐዋርያት ጋር ሕይወት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በብርቱ ሰርተናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በጻፍኳቸውና ለምድር ነዋሪዎች ባበረከትኳው ሶስት መጽሐፎች ማለትም የዮሐንስ ወንጌል፣ የዮሐንስ መልዕክትና፣ የዮሐንስ ራዕይ እታወቃለሁ። ሐዋርያውና ወንጌላዊው ዮሐንስ ነኝ።
ስለ ሕይወት የተለያየ ሙያ ያላቸው ሰዎች የሰጡትን ትርጉም አየሁና ቢገርመኝ ነው ይህን የጻፍኩልህ። ወዳጄ ባጭር አነጋገር ሰዎቹ የሚሉትና ትክክለኛው ሕይወት ትርጓሜ ለየቅል ነው። አንተ ጋዜጠኛው ራስህ ስለህይወት ያለህ ትርጉም ይኼ መሆኑ አሳዝኖኛል።
ዳዊት ለመሆኑ የህይወት ትርጉሙ እውን እናንተ እንዳላችሁት ነው እንዴ?... ፈጽሞ አይደለም። ትክክለኛው የህይወት ትርጉምን ለማወቅ ትፈልጋለህ?... እንግዲያውስ ከመደርደሪያህ ላይ አቧራ የጠጣውን መጽሐፍ ቅዱስህን አንሳና አቧራውን አራግፈህ አንብብ። እዚያ ላይ የህይወት ትርጉም እንደ ማለዳ ጮራ ፍንትው ብሎ ይታይሀል።
በል ታዲያ ትክክለኛውን የህይወት ትርጉም እንዳገኘህ ለተሳሳቱት ሁሉ የህይወት ትርጉሙ ይኼ ነው ብለህ ከስህተት ጎዳና መልሳቸው።
ወደ እኛ ለመምጣት ትጋ። በጽድቅ ጎዳና ተመላለስ። የምስራቹን ወንጌል በጊዜውም ሆነ አለጊዜው ስበክ። እግዚአብሔር ይረዳሀል። ጊዜህ ደርሶም ወደ እኛ እስክትመጣና ሰማያዊ ህይወትህን መምራት እስክትጀምር ድረስ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር፣ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና የመንፈስ ቅዱስ እውነት ያግኝህ።
ሐዋርያና ወንጌላዊ ዮሐንስ
ከአዲስቷ ጽዮን
አስገራሚውን ደብዳቤ አንብቤ እንደ ጨረስኩ ለዘመናት የመጽሐፍት መደርደሪያዬን ከማጣበብ ውጪ አንዳችም ጥቅም ሰጥቶኝ ወደማያውቀውና አቧራ ወደጠገበው መጽሐፍ ቅዱስ እጄን ሰድጄ መዝዤ በማውጣት የእውነት ማንበብ ጀመርኩ።
እንደ መጀመርያም ለምን የዚህን ሐዋርያ ሶስት መጽሐፎች አላነብለትም አልኩና ከዮሐንስ ወንጌል ጀመርኩ። በመጽሐፉ የመጀመርያ ምዕራፍም እንዲህ የሚል ቃል ሰፍሯል።
«በመጀመርያው ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመርያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ
አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፣ ጨለማም አላሸነፈውም።»
(ዮሐ. ፩፡፩-፭)
በጣም ተገረምኩ። በእርሱ ሕይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሀን ነበረች ነው የሚለው። ምን ለማለት ነው? ብዬም ራሴን ስጠይቅ ከጽሁፉ ያገኘሁት መልስ፡-
፩. ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ መኖሯን
፪. ያም ሕይወት ኢየሱስ መሆኑንና
፫. ሕይወትም ወይም ኢየሱስ የሰው ብርሀን መሆኗን ነው።
(ንባቤን ቀጥያለሁ። ያነሳሁት ነጥብ ስለ ሕይወት ትርጉም ነውና፣ ሕይወትን የተመለከተ ነገር ሳገኝ በማስታወሻ ደብተሬ ላይ አሰፍራለሁ። ደግሞም እንዲህ የሚል ቃል አገኘሁ።)
«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።»
(ዮሐ.፫፡፲፮)
(በጣም የሚገርም ቃል ነው። የዘላለም ሕይወት ነውኮ ሚለው። እንዴት ያለ ነገር ነው?... በማን ያመነ ነው የዘላለም ሕይወት የሚያገኘው?.... ንባቤን ልቀጥል፣)
«በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።»
(ዮሐ. ፫፡፴፮)
(ምን አለ?... በልጁ የሚያምን?... በማ ልጅ?... እንዴ ሐዋርያ ዮሐንስ ምን እያለ ነው?... ለማንኛውም ንባቤን ልቀጥል…)
«… ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፣ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ፣ የህይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር…»
(ዮሐ. ፬፡፲)
(ምናለ?... የሕይወት ውኃ?... ሐዋርያ ዮሐንስ ምን ለማለት እየፈለገ ነው?... እውን እኛ ከምናውቀው የምድር ውኃ ውጪ ሌላ የሕይወት ውኃ የሚባል ነገር አለ?... ይገርማል… እሺ ሐዋርያው በጣም ኃይለኛ «ኢሹ» ነው ያነሳኸው… ·ረ ቀጥልልኝ ትካርህ ጥሞኛል። )
«… እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፣ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ።»
(ዮሐ. ፬፡፲፬)
(ሐዋርያው ግራ እያጋባኸኝ ነው። ኢየሱስ እንዲህ አለ እያልክ ነው ያለኸው። ታዲያ ይህ የምትለው ነገር እንዴት ሰዎች ሳይረዱት ቀሩ?... ለምንስ በምድር ላይ ብዙ ሐይማኖት ተፈጠረ?... በክርስትና ስር ራሱ እጅግ በርካታ ሐይማኖቶች አሉ፤ ይህ ለምን ሆነ?... ደግሞም የኢየሱስ ዘር የሆኑት አይሁዶች ራሳቸውኮ አልተቀበሉትም፣ … ለማንኛውም እስቲ ማንበቤን ልቀጥል። )
«እናንተም በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።»
(ዮሐ. ፭።፴፱)
(ከዚህ በላይ ግራ መጋባት ምን አለ?... በጃቸው ያለው መጽሀፍ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩና የሚመሰክሩ ከሆኑ፣ ሌላ ኢየሱስ መጠበቅ ስለምን አስፈለጋቸው?... አሁንስ ቢሆን እየሆነ ያለው እንዲህ አይደለም እንዴ?... ኢየሱስ ብቻ ነው የሕይወት ቁልፉ ተብሎ ሳለ ብዙ ሰዎች ግን ቁልፉን አጥተውታል። ቁልፉ በጃቸው ሆኖ ሳለ አላስተዋሉትም፣ ወይ ንቀውታልና ሌላ የሕይወት በር ቁልፍ እየፈለጉ ናቸው። ሲገርም… ለማንኛውም ወደ ንባቤ ልመለስ…)
(ዮሐ. ፮፡፴፭)
(እውነታው ግን ብዙዎች ይህንን ቃል አላነበቡትም ወይም አልበራላቸውም ስለዚህም ኢየሱስ የሕይወት እንጀራን ቸል ብለውታል፤ ዳሩ ሰው ካልታዘዘ፣ ካላነበበና ካልሰማ እንዴት ቃሉ ይበራለታል?... እኔን ጨምሮ የብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ አቧራ ከመጠጣት አልፎ ሸረሪት አድርቶበታል።)
«ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።»
(ዮሐ. ፮፡፵
(ወይ ግሩም አያችሁልኝ ሌላ ጉድ?... አያችሁ የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ምን እንደሆነ?... የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የአብ ፈቃድ ነው። ያም በልጁ ስናምን ብቻ ነው። ደግሞኮ ሞተን አንቀርም ምክንያቱም በመጨረሻው ቀን እኔ አስነሳዋለሁ ይላልና ኢየሱስ። አሁን ሕይወትና የሕይወት ትርጉም እየገባኝ ነው። ንባቤን ቀጥያለሁ።)
«እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።… ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ስጋዬ ነው።… እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ።»
(ዮሐ. ፮፡ ፶፩-፶፬)
«ሥጋ ምንም አይጠቅምም እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።…»
«… ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም። ኢየሱስም ደግሞ ለ አስራሁለቱ እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ። ስምዖን ጴጥሮስ፡- ጌታ ሆይ ወደማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ እኛስ አንተ ክርሰቶስ የህያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት።»
(ዮሐ.፮፡፷፰)
(ታዲያ እስከዛሬ የሄድኩበት መንገድ ትክክል አይደለም ማለት ነው? … እስከዛሬ ድረስ የዘላለም ሕይወት እንዴት ማግኘት እንዳለብኝ ማንም የነገረኝ አልነበረም። «ኢቭን» ከናትና አባቴ የወረስኩት ሐይማኖት በራሱ ሰንበትንና በዓላትን ከማክበር ውጪ አንዳችም ቁም ነገር አላስተማረኝም። የናትና አባቴ ሐይማኖትማ ትልቅ ቦታ ሚሰጠው ለአዳኙ እናት እንጂ ለልጇ እንዳልሆነ ጸሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። … እውነት ለመናገር ይኸው እስካሁን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ከጀመርኩበት ሰከንድ አንስቶ አንድም ቦታ ላይ ስለ እናቲቱ አማላጅነት የሚናገር ስፍራ አላገኘሁም። ይልቁንስ የወንጌሉ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ የሚያትተው ስለ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ ምንድነው ምጠብቀው?... እውን የዘላለም ሕይወት ማግኘት አልፈልግምን?... በጣም እፈልጋለሁ። እንግዲያውስ በኢየሱስ ክርስቶስ ልመና?)
1996 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment
ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡