Thursday, March 1, 2012

እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ወይስ….?

ከዴሞክራሲ ትሩፋቶች አንዱና ዋነኛው ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ነው፡፡ እገሌ ይቀየማል፣ እንቶኔ ይሰማዋል ሳይሉ የሆድን የመናገር እውነት፡፡ ዴሞክራሲ ባልዳበረበትና በሌለበት አገር ግን ሐሳብን በነፃነት መግለጽ የሚቻለው ሆድ ሲያባ ብቻ ነው፤ ብቅል ስለሚያወጣው፡፡ በአገራችንም ለበርካታ ዘመናት የእኛ ሰው ‹‹ዕብድና ዘመናይ የልቡን ይናገራል›› በማለት በሥርዓቱ ላይ ያለውን ቅሬታ የሚገልጸው አንድ ሁለት በመጎንጨት ሚስቱ ላይ ነው፡፡ ‹‹አህያውን ፈርቶ ዳውላውን›› እንዲሉ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በተለይ በጣም የተማረና የተመራመረ በሥርዓቱ ላይ ሆዱ ሲጎሽ አውቆ አበድ ይሆናል ወይም ‹‹ሙር›› ይሉታል በያኔው አጠራር፡፡ ከዚያም ያሻውን ቢናገር እሱ ሙር ስለሆነ ወዲያ ተውት ይባላል፡፡ ለአብነት የፍቅር እስከ መቃብሩ ጉዱ ካሣን ልብ ይሏል፡፡  
ባሳለፍናቸው የተለያዩ ሥርዓቶች ሐሳብን በግልጽ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት ባለመኖሩ ሕዝባችን ቅሬታውን ለመናገር ብቻ አንዳንዱን ሰካራም፣ ሌላኛውን ሳያብድ እብድ ሲያደርግ፣ የተወሰነውን ደግሞ ባለቅኔ አድርጓል፡፡ የአገዛዙ ቀንበር ሲጫነው የሰብዓዊ መብት ጥሰቱና ረገጣው አጥንቱ ድረስ ዘልቆ ሲያመው፡፡ በተለይ ይህ እውነት ጎልቶ የሚታየው ባጤዎቹ ዘመን ነበር፡፡ ሥርዓቱ ሳይወዱ በግዳቸው ሊቅ ያደረጋቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ እንደ አብነት አለቃ ገብረ ሐናን መውሰድ እንችላለን፡፡ አለቃ በአፄ ቴዎድሮስና በአፄ ምኒልክ ዘመን እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳ ሰውየው የነገሥታቱ ባለሟል (አማካሪ) ቢሆኑም ቅሉ፣ ሥርዓቱ ሆዳቸውን ሲያጎሸው እንደ አንዳንዶቹ መሣሪያ ዘርፈው ወደ ዱር አላስገባቸውም ይልቅዬ ቅኔ አዘርፏቸው አንቱታን አስቻራቸው እንጂ፡፡
እስቲ ለምሳሌ በጊዜው የነበረው ሕዝብ ሰውኛ ዘይቤን ተጠቅሞ ካላቸው ምሳሌያዊ ዘይቤዎች አንዷን እንይ፡፡ ‹‹ቁርበት ምን ያንጓጓሀል ቢሉት ባያድለኝ ነው እንጂ የነጋሪት ወንድም ነበርኩ፤›› አለ፡፡ የሚገርም አባባል አይደለም? ስለዚህ በአገራችን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመጻፍ ነፃነት አለመኖር ያተረፈልን ነገር ቢኖር ጥቂቶችን ተራች፣ አንዳንዶችን ቅኔ ዘራፊ ማድረግና ብዙዎችን ደግሞ ሰካራም ማድረግ ነበር ማለት ነው፡፡ ‹‹ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል›› ብለዋልና እነርሱ ራሳቸው፡፡ ታዲያ በእኔ ዘመን ‹‹ዕብድና ዘመናይ የልቡን ይናገራል›› የሚለው ተረት እንደማይሠራ ስረዳ ተረቱን እንዲህ ለመቀየር ተገደድኩ፤ ‹‹ዕብድና ሰካራም የልቡን ይናገራል፤›› ምክንያቱም አሁን አሁን ዘመናይ (ዘመናዊ) ሰው አፉን መሸበብ የሚመርጥበት ጊዜ በመሆኑና እብድና ሰካራም ብቻ የልቡን መናገር በመቻሉ ነው፡፡ አፉን ካልሸበበ ይጠብቀዋልና ‹‹ሸቤ›› እንዲሉ፡፡ (ዘብጥያ ማለት ነው በአራድኛ)፡፡ ሰካራም ግን ያሻውን ቢለፈልፍ ማን ከቁብ ይቆጥረዋል? ታዲያ እንዴት ነው ጎበዝ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ መለኪያ ሥር መደበቅ ያዋጣ ይሆን?
የሰው ልጅ በተፈጥሮው፣ ሲበጅ ማለት ነው ሐሳቡ እንዲታፈን ተደርጎ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ገና ጡት ያልጣለ ጨቅላ መብቱን ሲነኩበት (ጡት ሲከለክሉት) ‹‹እሪ…›› ብሎ የሚያለቅሰው፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ምንም እንኳ ትውልዳችን ተረት መተረትና ቅኔ መቀኘት የተራራ ያህል ከብዶትና የሰማይ ያህል ርቆት ሐሳቡን በተረትና በቅኔ ባይገልጽም፣ በስድ ንባብና በግጥም እያደረገ በመረጃ መረብ ያሰራጨዋል፤ ከመቅጽበትም ዜናው ዓለምን ይሞላል፡፡ ምን ይደረግ ጊዜ ነዋ! ዘመነ መረጃ፣ ዘመነ ግሎባላይዜሽን፡፡
ዴሞክራሲ ‹‹አለ›› ተብሎ በሚነገርባቸው፣ ነገር ግን አተገባበሩ ላይ ‹‹አለ›› ተብሎ ስለማይወራላቸው መንግሥታት ሳስብ ሁሌ የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ በተለይም በፅኑ አገዛዛቸው የተነሣ በሥልጣን ኮርቻ ላይ ረጅም ዘመን ስላስቆጠሩት፡፡ ለመሆኑ እንዴት ነው ሕዝቡ ስለእነርሱ ያለውን ስሜት የሚረዱት? እንዴትስ ነው ሕዝቡ ምን እያለ እንደሆነ የሚሰሙት? ሕዝባቸው የሚተነፍስበት ምንም ዓይነት መንገድ ስለሌለ የሥልጣን ‹‹ጌጃቸው›› ምን ያህል እንደወረደ እንዴት ነው የሚያውቁት? ለዚህም ነው በብዙ አገሮች እንደምናየው ለዘመናት የታፈነ የሕዝብ ስሜት ድንገት እንደ እሳተ ጎመራ ፈንድቶ ለያዥ ለገናዥ አስቸጋሪ የሚሆነው፡፡ የመናገርና የመጻፍ መብቱ የተከበረለት ሕዝብ ያለው መንግሥት ግን በየጊዜው ራሱን ‹‹አፕዴት›› ያደርጋል፡፡ በየጊዜውም ራሱን ‹‹ስካን›› ያደርጋል፡፡ በአገዛዝ ‹‹ሲስተሙ›› ላይም አሪፍ ‹‹አንቲቫይረስ›› ጭኖ ለዕድገት ፀር የሆኑ ‹‹የሶፍትዌር ቫይረሶችን›› ጠራርጎ ያስወግዳል፡፡ ከዚያም ያላንዳች ‹‹ስታክ›› ማድረግ ‹‹ሲስተሙ›› መሥራት ይቀጥላል፡፡ ትንታኔውን በኮምፒዩተርኛ ማድረጌ ለርዕሴ ጥሩ ምሣሌ ስለሆነልኝ ነው፡፡
አንድ ጊዜ አንድ ሰው የቤት ሠራተኛ ሊቀጥር ወደ ደላላ ሄደ ይባላል፡፡ ለደላላውም ‹‹አሪፍ የቤት ሠራተኛ እፈልጋለሁ ታገኝልኛለህ?›› ይለዋል፡፡ ቀልጣፋው ደላላም፣ ‹‹ምን ዓይነት ሠራተኛ? ቀይ፣ ጥቁር፣ አጭር፣ ረጅም፣ ወፍራም፣ ቀጭን…›› እያለ እንደ ቱባ ክር አንደበቱን መተርተር ሲጀምር፣ ሰውየው፣ ‹‹እንደዚያ ማለቴ አይደለም፤ ባለሙያ፣ ታዛዥ፣ ጨዋ፣ የማትናገር፣ የማትጋገር፣ እኔ የምላትን ብቻ የምትሰማ ሠራተኛ ነው የምፈልገው፡፡ ስለ መልኳ እንኳ ብዙም ግዴለኝም፤›› ይለዋል፡፡
‹‹ታዲያ ምን ችግር አለ ሞልቷል›› በማለት ደላላው አንዲት ሠራተኛ ከመቅጽበት ይዞ ከተፍ ይልና፣ ‹‹እነሆ ጌታዬ የማትናገር የማትጋገር ጨዋ ሠራተኛ›› ብሎ ያቀርብለታል፡፡ ሰውየውም ለደላላው ኮሚሽኑን ከፍሎ ሠራተኛዋን ወደቤቱ ይዞ ሄደ፡፡ ሠራተኛዋም ሥራዋን ጀመረች፡፡ በመካከላቸው ከአለቃና ከሎሌ ወይም ከአዛዥና ከታዛዥ ውጪ አንዳችም ሌላ ግንኙነት የለም፡፡ ይኼን አድርጊ እሺ፣ ያን አታድርጊ እሺ፡፡ ይኼን ሥሪ፣ ያን አትሥሪ፣ እሺ፤ በዚህ ግቢ፣ በዚያ ውጪ እሺ፡፡ እንዲህ ነው ነገራቸው፡፡ ታዲያ ሰውዬው ብዙ ጊዜ ሥራ ሲሄድ ወይ ቁልፉን ረስቶ ይሄዳል፣ ወይ ኮቱን ገልብጦ ይለብሳል፣ ወይ አንድ እግር ካልሲ አድርጎ ይሄዳል፡፡ ቢሮ ሲደርስ ነው ልብ የሚለው፡፡
ሠራተኛዋ ብዙ ጊዜ ስህተቱን ልትነግረው እየፈለገች፡፡ ‹‹ጋ…ጋሼ የሸሚዝዎን አዝራር ባግባቡ አልቆለፉትም›› ገላምጧት ይወጣል፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ፣ ‹‹ጋሼ የኮትዎ ኮሌታ ተወላግዷል›› ፀጥ ብሏት ይወጣል፡፡ ‹‹ጋሼ ሁለት የግራ እግር ጫማ ተጫምተዋል›› እንዳልሰማት ሆኖ ያልፋል፡፡ ሰዓት ካልረፈደም ያስተካክለዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን አስተያየቷ አይመቸውም፡፡ አስተዳዳሪዋ ምግብ ከማብሰልና ልብስ ከማጠብ ውጪ ሌላ ቃላት ባትተነፍስ ደስ ይለዋል፡፡ ሠራተኛዋም ይኼ ነገር ስለገባት ‹‹ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባበትም›› ብላ በዝምታዋ ቀጠለች፡፡ በኋላ ግን ሰውየው ለብዙ ጊዜ ‹‹ፐርሰናሊቲ››ን ባለመጠበቅ፣ በዝርክርክነትና ግዴለሽነት በመሥሪያ ቤቱ ተገምግሞ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው፣ ችግሩን አስተዋለ፡፡ መስታወቱን እንዳልተጠቀመበትም ተረዳ፡፡ ለካንስ ተማረችም አልተማረችም፣ ሠለጠነችም አልሠለጠነችም፣ ሠራተኛው መስታወቱ ነበረች፡፡
ሕዝብ ጉድፉንና ስህተቱን ያይበት ዘንድ የተበጀ የመንግሥት መስታወት ነው፡፡ መንግሥት የአስተዳደር ሚዛኑ ከየትኛው በኩል እንዳጋደለ የሚያየው፣ በዙሪያው ምን እየተካሄደ እንዳለ የሚረዳው ሕዝብ በሚባለው መስታወት ነው፡፡ መንግሥት ያለ ሕዝብ፣ ሰው ያለ አየር እንደ ማለት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ መጠበቃቸውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሕዝብ ያለው መንግሥት ከውኃ ዳር እንደ በቀለ የወይራ ዛፍ ነው፡፡ ያላንዳች ችግር ሁሌ ይለመልማልና፡፡ ነገር ግን ሕዝብ ባንድም ሆነ በሌላ የመናገርና ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነቱ አደጋ ላይ ከወደቀ እንደተሰነጣጠቀ መስታወት ይሆንና መንግሥት ራሱን ማየት እስከማይችል ድረስ ይሆናል፡፡ ‹‹መካር የሌለው ንጉሥ ያለአንድ ዓመት አይነግሥ›› እንደሚባለው፣ የሕዝቡን ፍላጎት የማያውቅ መንግሥት የውኃ ላይ ኩበት ይሆናል፡፡ 
አንድ ወዳጄ ለሥራ ሲሰማራ የገጠመውን ላንሳና ወጌን ልቀጥል፤ በአንድ ማለዳ ወዳጄ ከቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወደ ፒያሳ በሚወስደው መንገድ ላይ ፒያሳ የሚሄድ ታክሲ ከሌሎች ተሳፋሪዎች ጋር ችሎት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በርከት ብለው ይጠብቃሉ፡፡ ሰዓቱ እየረፈደ ነው፡፡ ሁሉም ተሳፋሪ ቶሎ ታክሲ አግኝቶ ወደ ሥራ ይሄድ ዘንድ ጓጉቷል፡፡ ነገር ግን ታክሲዎች በሙሉ ከመነሻው ማለትም ከቀጨኔ መድኃኔዓለም እየሞሉ ስለሚመጡ ችግራቸው የከፋ ሆነ፡፡ በዚህን  ጊዜ አንድ ከፒያሳ የመጣ ታክሲ በአጋጣሚ ከመጨረሻው ሳይደርስ መንገድ ላይ ተሳፋሪዎቹን በሙሉ አውርዶ ባዶ ስለነበረ፣ ችሎት አደባባዩ ላይ ያዞርና ወደፒያሳ ለመሄድ ተኮልኩለው የነበሩትን መንገደኞች ማሳፈር ይጀምራል፡፡ በአካባቢው የነበሩ ሁለት የፀጥታ አስከባሪዎች ግን ታክሲው እንዳይጭን ያዙታል፡፡ ‹‹እንዴ ምን ችግር አለው?›› አለ ረዳት፤ ‹‹አደባባይ ላይ ተሳፋሪዎች ወርደው ታክሲው ባዶ ከሆነ እዚህ ብንጭን ምን ችግር አለው?›› አለ ሾፌር፤ ‹‹ምንድነው ችግሩ?›› አሉ ተሳፋሪዎች፤ ‹‹አይቻልም! አዙረህ ሄደህ ከመነሻው ጫን!›› አሉ የፀጥታ አስከባሪዎቹ፡፡
በዚህ መሀል እሰጥ አገባው እየከረረ፣ እየከረረ መጣ፡፡ ‹‹ባዶ አይደለሁ እንዴ? እዚህ ብጭን ችግሩ ምን እንደሆነ ልትነግሩኝ ትችላላችሁ?›› ይጠይቃል ረዳት፡፡ ፖሊሶቹም እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው፣ ‹‹ጭራሽ ችግሩን አስረዱኝ ይላል እንዴ?›› ይሉና አንጠልጥለው ወደ አንድ የግለሰብ ግቢ ያስገቡታል፡፡ አስገብተውም እንደ በርበሬ ደልዘው፣ እንደ ኑግ ወቅጠውና እንደ ተልባ አድቅቀው ባፍና ባፍንጫው ደም ቡልቅ ቡልቅ እያለ ቢልኩት ተሳፋሪዎች በሙሉ በጣም ተገርመውና ደንግጠው፣ ደግሞም ነግ በኔን ፈርተው በሹክሹክታ ‹‹ምን ዓይነት ጉድ ነው መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር ለምን እንዲህ ዓይነት ድርጊት ይፈጸማል? ዴሞክራሲ አለ በሚባልበት አገር እንዴት እንደዚህ ይደረጋል? ታዲያ የቱ ጋ ነው ነፃነት ያለው?›› እያሉ ሲያጉረመርሙ፣ ‹‹የፀጥታ አስከባሪዎቹ›› ሁሉንም ሰዎች አስወርደው ታክሲው ከመነሻው እንዲጭን ፈርደውበታል፡፡ እንግዲህ ሾፌርና ወያላ እንዲሁም ተሳፋሪዎች ለምን? ብለው ስለጠየቁ ነው ይህ ሁሉ ድርጊት የተፈጸመው፡፡
እኔ የምለው?
1.       የፀጥታ አስከባሪዎች ሥራቸው ፀጥታ ማስከበር ወይስ ሰላም ማደፍረስ?
2.      የፀጥታ አስከባሪዎች ሥራ ችግር መፍታት ወይስ በቆመጥ ሰው መነረት?
3.      በሰው ግቢስ ያለፈቃድ ሰውን አስገብቶ መደብደብ ይቻላል?
4.      አንድ ሰውስ ጥፋት እንኳ ቢኖርበት በ48 ሰዓታት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት መወሰድ ይገባዋል እንጂ እንዲያ ይደረጋል? ነውር አይደለም?
5.      ለሕግ ያልተገዛው እነርሱ ሕግ አዋቂዎቹ ወይስ ሕግ አላወቀም የተባለው ረዳት?
እዚህ ላይ መንግሥት የፖሊስ ሠራዊቱን ሲያሠለጥን በአብሮነት ሕገ መንግሥቱን፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉንና ሌሎች ሕጎችን በሥልጠና ወቅት በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እንደሚያስተምር አልጠራጠርም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመናገር ነፃነት አለመኖር ፈርጀ ብዙ ችግሮች አሉት፡፡ ለምሳሌ እንደ ሰደድ እሳት ለተስፋፋው ሙስና ይህ ዓይነቱ ችግር ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ ሕዝቡ የሙስና ወንጀል እንዳለ ያውቃል፡፡ በዚያ ሰንሰለት ውስጥም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያሉትን አብጠርጥሮ ያውቃል፡፡ ግን በሰዎቹና በሥራቸው ላይ አንዳች ለማለት አቅም የለውም፡፡ ምክንያት ቢሉ ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱ የተገደበ ነውና፡፡ ለደኅንነቱም ይሰጋልና፡፡ ለዚህ ነው ሥርዓታችን እንደ ፍልፈል ውስጥ ለውስጥ የሚሄድን እንጂ ግልጽ የሆነ ማንነትን በሕዝባችን ውስጥ ያላዳበረው፡፡ መንግሥትና ሕዝብ እጅና ጓንት መሆን የሚችሉት መንግሥት አንዳችም ገደብ የሌለበት ሐሳብን በነፃነት የመናገርና የመጻፍ ነፃነት ሲያጎናጽፍ ነው፡፡ አለዚያ ግን በክፍተቱ ንፋስ ይገባና ለጥፋት ኃይሎች መሣሪያ ይሆናል፡፡ ፖሊሲዎቿንና መመርያዎቿን ‹‹ኮማ›› ሳይቀር የምንኮርጅላት አሜሪካ ዴሞክራሲዋን፣  ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመጻፍ ሕጓንም ልንኮርጅላት ይገባናል፡፡
አንድ ተረት ጣል አድርጌ ወደ ወጌ መደምደሚያ ልግባ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ተረት ተረት የሚሆነው የእውነት ተረት ሆኖ ነው እንዴ? ብዬ ብጠይቃችሁስ? እንደኔ እንደኔ መረጃ ባይኖረኝም ደግሞም አብዛኛው ሰው እንደሚስማማበት ተረት የአንድ ወቅት እውነት ነው መልሴ፡፡ ማን ያውቃል የእኛም ትውልድ ጊዜ ሲያልፍ ሌላ ትውልድ ይመጣና በጥንት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ይኖሩ ነበር ተብሎ ገድላችን ይተረትልን ይሆናል፡፡ ስለዚህም አንድ እውነት ተረት የሚሆነው ሦስት ደረጃዎችን አልፎ ነው ማለት ነው፡፡ የመጀመርያው የአሁንኛውን ክስተት ሲያልፍ ‹‹ገጠመኝ›› ተብሎ፣ ቀጥሎ  ባንድ ወቅት እንዲህ ተከሰተ ተብሎ ባለ ገድሎቹና ገድሉ ሲወሩ፣ ‹‹ታሪክ›› ተብሎና ሦስተኛው ደረጃ ላይ ሲደርስ ግን በጣም በመቆየቱ ደብዝዞ ተረት ተረት የላምበረት ይባልና በምድጃ ዳር ይወራለታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ተረት ሁሉ ውሸት አይደለም፤ ውሸት ሁሉ ደግሞ ተረት አይደለም፡፡
እናም በድሮ ጊዜ አንድ ባለሟል (በአሁኑ ዘመን አጠራር የፕሬዚዳንት አሊያም የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ እንደማለት) ነበር ይባላል፡፡ ሥራው ንጉሡን ማማከር ነውና ስለንጉሡ የማያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ውስጣቸውን ሳይቀር አብጠርጥሮ ያውቃል፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ከእንቅልፉ በማለዳ ነቅቶ፣ በሰላም ያሳደርከኝ በሰላም አውለኝ ብሎ በማለዳ ወደ ሥራው ሲሄድ፣ ባየው ያልተለመደ ነገር ጠላታችሁ ይደንግጥ ክው ብሎ ይቀራል፡፡ ንጉሡ ቀንድ አብቅለው ነበር፡፡ “Pause” የሆነ ያህልም ላፍታ ዓይኑን በንጉሡ ላይ ተክሎ ከቆየ በኋላ ወደ አዕምሮው ሲመለስ ንጉሡ ‹‹አሁን የተመለከትከውን ነገር በፍፁም ለማንም ትንፍሽ ማለት የለብህም!›› ብለው ማስጠንቀቂያ አዘል ትዕዛዝ ይሰጡታል፡፡ እሺ ብሎ ከንጉሡ እልፍኝ ቢወጣም እንግዳው ጉዳይ ግን ውስጡ ታምቆ ካልወጣሁ እያለ አስቸገረው፡፡ በመጀመርያ ለሚስቱ ሊነግራት አሰበና የንጉሡን ትዕዛዝ ፈራ፡፡ ታዲያ ግራ ቢገባውና እንግዳው ነገርም ገንፍሎ ሊወጣ መሆኑን ሲረዳ መሬት ቆፈረና አፉን ቀብሮ ‹‹ንጉሥ ቀንድ አበቀሉ›› ብሎ ለመሬት ተናገረ ይባላል፡፡ ሰው ሐሳቡን በነፃነት ይገልጽና ይናገር ዘንድ ካፈኑት ለግዑዝ አካል እንኳ መናገሩ የማይቀር እውነት ነው፡፡ በባል የምትጨቆን ሚስት አንተ ሰማይ ፍረደኝ፤ አንቺ ምድር ፍረጂኝ እንድትል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት ሰዎች በተፈጥሮ ከታደሉዋቸው መብቶች መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል፡፡ እውነት ለመሆኑም ድርሳናትን በማገላበጥ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ጊዜ የማይሽረው እውነታ በመፃረር በተቃራኒው ሲሠራ መታፈን ይመጣል፡፡ የታፈነ ደግሞ መፈንዳቱ አይቀርም፡፡ ያለአግባብ የሚፈነዳ ነገር ጥፋቱ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም እውነቱን እየተናገረ የመሸበት ያድር ዘንድ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ይከበር፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!
(ይህ ጽሁፍ በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ እትም የካቲት 21 ቀን 2004 ዓ.ም የወጣ ነው፡፡)

No comments:

Post a Comment

ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡