የጉዞ ማስታወሻ

                           ባህርዳር ደርሶ መልስ

የትራፊክ ፖሊሶቹ ወግ ሲጨለፍ 

የመጀመርያ ጉዞዬ ነው ወደ ሰሜን።  በዝና ብቻ ወደ ማውቃት ባህር ዳር ከሁለት ጓደኞቼ ጋር ልጓዝ አቆብቁቤያለሁ። ወደ ክፍለ ሀገር ሲኬድ ወጉን አላውቅ ብለን ማለዳ ላይ በትራንስፖርት እጦት መንገላታችንን ያዩ ሳተናዎቹ የመርካቶ ደላሎች ወደ ጎጃም በረንዳ ወሰዱን። እዚያ በህገወጥ መንገድ የሚጭኑና እኔ ለጊዜው እንደ ጢያራ ያለ ፍጥነታቸውን አይቼ «የምድር ኦሮቢላ» ያልኳቸው መኪኖች አሉና።

የመጀመርያው ትራፊክ ፖሊስ

እንግዲህ በእሳቱ ደላላ አማካይነት ወደ ጎጃም በረንዳ ከደረስንና የምሱን ሰጥተነው ከሸነው በኋላ ወደ ሰሜን ለመሄድ ተኮልኩለው መኪና ይጠብቁ ከነበሩት ሰዎች ጋር ተደባለቅን።
አንድ «የምድር ኦሮቢላ»  ከርቀት ሲታይም ያ ሁሉ የሰው ኩልኩል በጎጃም በረንዳ ላይ ኮተቱን እያንኳተተ ጥንብ እንዳየ ጆፌ አሞራ ቁልቁል ቢራወጥ፣ እኛም አብረን እንዘጥ እንዘጥ አልን:: ይሁንና መኪናው በፈጣን ሯጮች ቀድሞ ሞላና ቁና ቁና መተንፈስ እጣችን ሆነ ። በዚያ ላይ እስከ ደብረ ማርቆስ ብቻ ነበር የመኪናው የመጨረሻ ምዕራፍ። ይሁን እንጂ ከየት አቅጣጫ እንደመጣ ያልተገመተ ትራፊክ ፖሊስ ድንገት ደርሶ የመኪናውን ታርጋ ፈቶ እብስ ቢል ውስጥ የነበሩት መንገደኞች በዝሆኖች ጸብ ፍዳውን እንደሚያይ ሳር ሆኑ።

ታዲያ አንደኛው ጓደኛችን ወደ መጣንበት አቅጣጫ «ተከተሉኝ» ብሎ ሽቅብ መሮጥ ሲጀምር ያ ሁሉ የሰው ግሪሳ ተከተለው። ለካ እዚያም ሌላ «ኦሮቢላ»  እንዲሁ ቆሟልና። አቤት መቼም ይሄ ጥቁር ቡና ልባችን ላይ ፈላ ሳይሆን ተንተከተከ ነው የሚባለው። (ምንም እንኳ ቤት ያፈራው ሆኖ በተቃራኒው ግን ዋጋው ኪሳችንን ቢያሸማቅቅም፤ እኛ ግን እስከ በረካ ድረስ ከማንቃረር አልቦዘንም።)
ወደ «የምድር ኦሮቢላ»ው ማራቶን እንደበላ ጀግና እያለከለክን ብንደርስ «ዕቃችሁን ብቻ ቦታ እያሲያዛችሁ እናንተ ካካባቢው ተሰወሩ።» ሆነ የአቡታንቲው («ወያላ» ከሚለው ቃል ይሻላል ብዬ ነው።) መልስ።

«ምነዋ?» ብንለው
«ትራፊክ ፖሊሱ እንዳያየን»
«እንዴ… ያየንስ እንደሆነ?»
«እዚህ አካባቢ መጫን አይፈቀድማ።»
«እንዴ ዕቃችንስ?»
«ቦታ ይይዝላችኋል።»
«መኪናው ጥሎን ቢሄድስ?»
«አይሄድም ባክህ ካላመንክ መተው ትችላለህ።»
እየፈራን እየቸርን ሻንጣችንን በምንቀመጥበት ወንበር ላይ አስቀመጥንና ፈንጠር ብለን በአይነ ቁራኛ እንጠባበቅ ጀመር።
ከዚያም ቅድም ላይ ከደብረ ማርቆሱ መኪና ላይ ታርጋ የፈታው፣ ለምድርና ለሰማይ የከበደው ሰውዬ ቢመጣ መኪናዋጋ ተከማችተው የነበሩት ሁሉ ድራሻቸው ጠፋ።
«የታለ ሹፌሩ?» አለ ትራፊክ ፖሊሱ
መልስ ሚሰጥ ጠፋ።
«የታለ የዚህ መኪና ሾፌር?»
ባካባቢው መርፌ ቢወድቅ እንኳ የሚሰማበት ታላቅ ጸጥታ ሆነ። ትራፊክ ፖሊሱ ምላሽ ሲያጣም ታርጋውን ሊፈታ ቢያጎነብስ፣ ረዳቱ ይሁን ደላላ ያልታወቀ ጎረምሳ ጸጉሩን እያከከ፣
«ሾፌሩ የለም ባሉካው ነው ያለው።» ይላል («ባሉካው» ባለቤቱ ለማለት ነው ባራድኛ።)
«ሾፌሩን ነው የጠየቁህ»
«ይመጣል ቁርስ ሊያረግ ሄዶ ነው!»
ትራፊክ ፖሊሱ አጎንብሶ ታርጋውን መፍታት ሲጀምርም ተሳፋሪ መስሎኝ የነበረ ሰው እየተቅለሰለሰ ጸጉሩን እያከከ ሁኔታውን ከሚከታተሉት ሰዎች መሀል መሰስ ብሎ እየወጣ
«ይቅርታ አድርግልኝ»
«አንተ ነህ ሾፌሩ?»
«አዎ… አይ… አዎ… ማለቴ ቁርስ ልበላ…»
«መንጃ ፈቃድ አምጣ!»
«እ…»
«መንጃ ፈቃድህን አሳየኝ!»
«እንትን…»
ትራፊክ ፖሊሱ ታርጋውን ፈቶ ጠፋ። እኛም የጉዟችን ነገር እዚያጋ እንዳከተመ እርግጥ ሆንን። ነገር ግን ሁልጊዜ የሚመላለሱት መንገደኞች
«ምሱን እስኪያሽረው ነው» አሉ
«የምን ምስ?»
«ባክህ እነርሱ ይተዋወቃሉ»
«መተዋወቅ ማለት?»
«አይገባህም እንዴ በቃ የሆነ ቦታ ይጠብቀዋል፤ ከዚያም የተወሰነ ‘ኮይን’ ይበጭቅለታል ከዚያም ይፋታሉ።»
እውነትም እንደ ተባለው ሾፌሩና አጋሮቹ ታርጋቸውን  ይዘው መጡና አስረውት ጉዞ ጀመርን።

 በሚኒ ባስ ውስጥ ከ18 ሰዎች ጋር ተሰይሜያለሁ። 
እንግዲህ በየቦታው በቆሙ ትራፊክ ፖሊሶች ብዙ ጊዜ መቆም ግድ ነው። እነዚህ ሰዎች ታዲያ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነገር ነው ሚያደርጉት።
በመጀመርያ መኪና ያስቆማሉ፣ ከዚያም መንጃ ፈቃድ ይጠይቃሉ፣ ቀጥሎ ሁሉም ባይሆኑም ትርፍ ሰው መጫን አለመጫኑን ያረጋግጣሉ፣ ከዚያም ፈንጠር ብለው መንጃ ፈቃዱን ተቀብለው ፊታቸውን ኮሶ ያሻራት ባልቴት አስመስለው ይሄዳሉ፣ በመጨረሻም ጫማቸው ላይ ሊደፋ ጋት ያህል ከሚቀረው ተለማማጭ ሾፌር ጋ ላፍታ እሰጥ አገባ የገቡ ይመስሉና… ለጊዜው በማናውቀው ምክንያት መንጃ ፈቃዱን ይመልሱለታል። ይሄንንም አንደኛው የጉዞ ባልደረባዬን እንዴት እንደሆነ ብጠይቀው መንጃ ፈቃዱ ውስጥ አንዳች ነገር ተከቶ አብሮ እንደ ሚሰጠው ነው የገለጸልኝ። የኛ ሾፌር ግን መንጃ ፈቃድ እንኳ በቅጡ ያልያዘ በመሆኑ ግርታዬን የበለጠ አብሶታል።

ሁለተኛው ትራፊክ ፖሊስ

ጎረምሳው ሾፌር ያለቅጥ ይጋልባል።አንድ ሁለት ጊዜም አህዮች ገብተውብን ለመገልበለጥ ሩብ ጉዳይ ሆንን።
 ከሩቅ ሲታይ በጦም የደከመ ባህታዊ እንጂ ትራፊክ ፖሊስ ሚያስመስል አንዳችም ነገር የማይታይበትና አለባበሱ ወግ አልባ የሆነ የትራፊክ ፖሊስ አስቆመን። የጠየቀውን ነገር ስላላገኘም ታርጋውን ፈታና ለሾፌሩ የቅጣት ወረቀቱን ቢሰጠው እንደ አብዛኛዎቹ ባለመሆኑ ተገረምን። አለባበሱን ባያሳምርም ትክክለኛው የትራፊክ ፖሊስ ሥነ ምግባር በሚገባ የሰረጸበት ይመስላል። «የለበሰ የማንንም ጎረሰ።» እንዲሉ አለባበስ አሳምረው በሥርዓቱ ከማይሄዱ ጋጠወጦች ይሻላል ስንልም አንዳንድ ተሳፋሪዎች አጉረመረምን።
ሾፌሩም እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ መኪናዋን ሲያከንፋት አንዳንዴ ባየር ላይ ሁሉ የምንሳፈፍ ይመስለኝ ነበር። በነገራችን  ላይ ከመቶ አብዛኛው እጅ አደጋ የሚከሰተው እንዲህ ሀቀኛ ትራፊክ ፖሊስ ባበሳጯቸው ሾፌሮች ሳይሆን ይቀራል?... እንጃ እንዲያው ግምቴን እንጂ እነዚያኞቹስ ቢሆኑ ያልዘሩትን ሲያጭዱ ከማበሳጨት አልፎ ሳያሳብድ ይቀራል?... ምናልባት እንግዲህ ያደጋው ቅለትና ክብደት ይለያይ ይሆን ይሆናል እንጂ ሁለቱም አይነት ሰዎች ላደጋ መከሰት የራሳቸውን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ወጋችንን እንቀጥል፤

ሶስተኛው ትራፊክፖሊስ

ሶስተኛው ትራፊክፖሊስ ግን ለየት አለብኝ። እንግዲህ ቀደም ብዬ እንዳልኩት በመኪናችን ውስጥ ሶስት ትርፍ ሰው አለ። ሰውየው አለ አይደል «ፈኒ» ቢጤ ነው። እንዲህ ነው ያደረገው። ያው ትራፊክ ፖሊስ የተባለ ሁሉ እንደሚያደርገው በመጀመርያ መኪናውን አስቆመ፣ ቀጠለናም በረዳቱ በኩል እየመጣና (በነገራችን ላይ መኪናችን ረዳት አልነበረውም። ይልቁንስ ትራፊክ ፖሊስ በመጣ ቁጥር እንደ ወያላ «የሚያክት» አንድ ነጠላጋቢ የለበሰ ባላገር ነበረ፤ የደሀ ቦርጭ በመሰለ ድቡሉቡል የቆዳ ወንበር ላይ የተቀመጠ። ይህ ሰው በጣም ነበር ያሳዘነኝ፤ ምክንያቱም ባህርዳር ድረስ ሁለት መቶ ሃያ ብሩን ሆጨጭ አርጎ ከፍሏል፤ ግና እንኳንስ በወጉ እንደ ሰው ወንበር ይዞ መቀመጫውን ሊያሳርፍ ይቅርና አንዴ ሲወርድ አንዴ ሲወጣ ፣ በር ሲከፍት ደግሞ ሲዘጋ፣ በጣፋጭ የሰሜን ለዛው «እህ ጌታው» ሲል ባህርዳር ዘልቋል።) ወደ ትራፊክ ፖሊሱ ልመለስ (የቱጋ ነበረ ያቆምኩት?) አዎ በረዳቱ በኩል እየመጣና  በር አስከፍቶ ሰው እየቆጠረ እንደቀደሙት ስለትርፍ ሰው አንዳችም ባይገደውም፣ ታርጋውን አየት እያደረገ
«በቃ ይሄ የታርጋ ነገር መደበኛ ሆነ አይደለ?» ሲል
ሾፌሩ ሁለተኛው ትራፊክ ፖሊስ የሰጠውን የቅጣት ወረቀት ጸጉሩን እያከከ ያሳየዋል።
«ምንድነው መውጫ አልያዝክም እንዴ?»
«አረ ጋለብክ ብሎኝ ነው»
«ራዳር ይዞ ነበር?»
«ሜዳ ላይ ነው ያለው ወላሂ የለበሰው ልብስ እንኳ ከውስጥ የለበስከው አይነት ነው እንዲያውም ገጭቼው ነበረ።»
«ገጭቸው ነበረ?... ገላግለሀው ነበራ»
ይሄኔ ተሳፋሪው በሳቅ አውካካ።
አብሮኝ ይጓዝ የነበረውም ወዳጄ
«ድሮ ድሮ መኪናን በየመንገዱ ሚያስቆሙ ሽፍቶች ነበሩ አሁን ግን ዘመን ተቀየረና ትራፊኮች ሆነዋል።» ቢል ወይ ግሩም ብዬ አፌን በጄ ጫንኩ።

የዓባይ በረሀ

ከብዙ ጉዞ በኋላ ልብን ቀጥ፣ ትንፋሽን ጸጥ ወደ ሚያደርገው ዓባይ በረሃ ደረስን።  እንዴት አይነት ተፈጥሮ ነው ጎበዝ? አቤት ሲያስፈራ!... ላፍታ ነፍሴ በሲዖል ያደረች መሰለኝ። እንዲህ ዓይነት ውበትና አስፈሪነት የተዋሀደበት ተፈጥሮ አይቼም ሆነ ሰምቼ አላውቅም። የጀግናው ቁርጭምጭሚት ቀጤማ የሚሆንበት፣ የኃያሉ ወገብ እንደ አራስ ሴት ደርሶ ውሃ ሚሆንበት፣ የብርቱው ክንድ ሚዝልበት፣ የፈሪው ሩህ  ጸሀይ እንደጎበኘው ቂቤ ሚቀልጥበት ቦታ ነው ዓባይ በረሀ ማለት።

እንግዲህ የበርካታ አገራት መመኪያና ተስፋ የሆነው የዓባይ ወንዝ ከአፋፍ ሆነው ቁልቁል ሲያዩት፣ በአንድ ትንሽ ካፊያ የተፈጠረ የቦይ ውሀ ነው እሚመስል። ወዲያውም የተወሰኑ ጥያቄዎች ራሴን ጠየቅሁ « ለመሆኑ አባይ ቢሞላ ቢሞላ አለው መላ መላ» የተባለው ዘፈን ምን ለማለት ይሆን? እውን አባይ ሞልቶ ያውቃልን? ከሞላስ እስኬት ነው የሚሞላው?... ያለም ውሃስ በሙሉ ቢጠራቀም ይሞላዋልን? (ይህቺኛዋ እንኳን የጅል ወይም የልጅ ጥያቄ ሳትሆን አትቀርም።)

ከላይ እንዳልኩት በዚያ መስመር ገና የመጀመሪያ ጉዞዬ ነውና፣ አቡነ ዘበሰማያትን በሆዴ ስንት ጊዜ እንዳነበነብኩ መናገሩ ዋጋ የለውም። ብቻ እንዲቹ ልቤ እንደተንጠለጠለችና ነፍስና ስጋዬ እንደተወራጩ ያን ግርማው የሚያርድ፣ ሞገሱ የሚያሸብር ቦታ ከ አንድ ሰዓት ምናምን ጉዞ በኋላ ጨርሰን ወደ ሜዳማው መልክዓ ምድር ገባን።

የጎጃም ጤፍ

ክረምት ሳይል በጋ
ቆላ ሳይል ደጋ
ለዘመናት ያገሬን ጉሮሮ የዘጋ
ባለውለታችን የጎጃሙ ማኛ
አሁን ድረስ አለ ዘብ ቆሞልን ለኛ።
በሰፊው ሁዳድ ላይ ከሩቅ ሲታይ እንደ ጠጠር የፈሰሰው ነገር ሌላ ሳይሆን የጤፍ ክምር ነው። እንዲህ ለዕይታ የሚያታክት የጤፍ ክምር ከተፈጠርኩ አይቼ አላውቅም። ዙሪያ ገባውን ቢያማትሩ አይንን ሰንጎ የሚይዘው ሌላ ሳይሆን የጤፍ ክምር ነው። እንዴት ነው ጎበዝ «ምንም ቢያርሱ እንደ ጎመን አይጎርሱ» የተባለው ተረት ምናልባት እዚህ አገር «ምንም ቢያርሱ እንደ ጤፍ  አይጎርሱ» ይሆን እንዴ?... ግን ግን ፡- «ለምን ታዲያ የጤፍ ዋጋ ሰማይ ነካ?»…«ለምን ስ እንደ ውሻ ምላስ የሳሳ እንጀራ ሶስት ብር ተሸጠ?»… ይሄ የማየው ጉድ፣ አይደለም ኢትዮጵያን ድፍን ዓለምን መመገብ አይችልምን? (እዚህጋስ ሳላጋንን አልቀርም፤ እንዲያው ያየሁትን ነገር በደንብ ለመግለጽ ፈልጌ ነው።)

የትራፊክ መንገድ አጠቃቀም

ድፍን አገሬውና የትራፊክ መንገድ አጠቃቀም እጅና ጓንት ናቸው። ቀኛቸውን ከያዙ ቀኛቸውን ነው። ምናልባት በተቃራኒው እየመጣ ያለ ሰው ካለ ጠጉረ ልውጥ ለመሆኑ ዋቢ ምስክር ነው። ግና አብዛኛዎቹ ሰዎች ቀኝና ግራቸውን ሳያዩ ድንገት ዘለው «ባቡር መንገድ» የሚያቋርጡት ሰዎች ነገር ግራ አጋብቶኛል።

ባህር ዳር

አመሻሽ ላይ ከውቧ ባህርዳር ገባን።  ታዳጊ ደላሎች አፋፍሰው አልጋ ወዳለበት አንድ ሆቴል እኔና ሦሥቱን ጓደኞቼን ይዘውን ሄዱ። ቡና ቤቱ አንድ መጸዳጃ ቤት ብቻ ስለነበረውም ተንፈስ ለማለት ወረፋ መያዝ ነበረብን። በዚያ ላይ የአልጋ ክፍሎቹ በራሳቸው ጽዳት የሌላቸውና በየአጎበሮቹ ላይ ቁና ሙሉ ቢንቢ የሰፈረባቸው ናቸው። «በቡሀ ላይ ቆረቆር» እንዲሉም ከቡና ቤቱ የተለቀቀውና የጆሮን ታምቡር የሚጠልዘው አገርኛ ሙዚቃ፣ በስካር ለዛ አብረው ከሚያንጎራጉሩ ጠጪዎችጋ ተዳምሮ ባየሩ ላይ ሲናኝ ፣ከዚያ ድካምጋ ሌቱ እንዴት እንደሚነጋ ሲታሰበኝ ግራ ገባኝ። ይሁን እንጂ ሀምሳ ሀምሳ ብራችንን ቀድመን የከፈልን ቢሆንም ቅሉ፣ ለእራት ፍለጋ ስንወጣ ሌላ የተሻለ አልጋ በአምስት ብር ልዩነት ብቻ አግኝተን አዳራችንን እዚያ አደረግን።
ታዲያ ለክፋቱ፣ ኩነኔ እንደገባ ሰው ሌቱ አይንጋልህ ቢለኝ፣ እኔ ያረፍኩበት ክፍል ከጎኑ ጽዳት የናፈቀው መጸዳጃ ቤት ነበርና ፤ አዳሬ እስከዛሬ ከገጠሙኝ መጥፎ አዳሮች መካከል አንደኛው ሆኖ ተመዘገበ። እንዲቹ ሌቱን ሙሉ የተበከለ አየር ስምግ አደርኩ።
በዚያች ጥቂት ቀናትም ባህርዳርን በምሽት ላያት ሞክሬያለሁ፣ በዕድሜዬ ካየሁዋቸው ውብ መንገዶቿ ላይም «ወክ» በልቻለሁ።
ባህርዳር ደረጃውን በጠበቀ «ፕላን» የተቆረቆረች ውብ ከተማ ናት። መሀልና ዳር ላይ ተተክለው ያለከልካይ ከሚዘናፈሉት ዘንባባዎችዋና ልዩ ልዩ ዛፎችዋ ባሻገር ለጥ ባሉትና ሰፋፊ ስፓልት መንገዶቿ ላይ ተሳፋሪ አንግበው ሽቅብ ቁልቁል የሚሉት  ባጃጆቿ ልዩ ውበቷ ናቸው።
በባህር ዳር አንድም የገበጣ መጫወቺያ ቆሬ የመሰለ መንገድ አላጋጠመኝም። ይልቁንስ በየመንደሩ ከጫፍ ጫፍ የተዘረጋውና በብልሀተኛ ባለሙያዎች የታነጸው የ«ኮብል ስቶን» መንገድ በውበት ላይ ውበት ጨምርሏታል እንጂ።
ዩና አፍንጫን ሰንጎ የሚይዝ ጠረን፣ ደግሞም አይንን «የሚያቅለሸልሽ» ቆሻሻ ፈጽሞ አላየሁም።  ይልቁንስ በየመንደሩ የተንጠለጠሉት የቆሻሻ ቅርጫቶች ህዝቡ ለጤናና ውበት ቅድሚያ ሰጥቶ ምን ያህል እየሰራ እንደሆነ  ይናገራሉ እንጂ።
ህንጻዎቿ ውበት ብቻ ሳይሆን ከእድሜ ጫፍ መድረስ እንደሚችሉ አሰራራቸውና የተሰሩበት ቁስ ያሳብቃል።
ነገር ግን «ውስጡን ለማንትስ» እንዲሉ ወደ ማጀቷ ስንዘልቅ እንደብዙዎቹ አሉን የምንላቸው ከተሞች ውቧ ባህርዳርንም  የሚያሳጡ፣ ከዘመናዮቹ እኩል የማይራመዱ፣ አንካሳና  በእድሜ ጫና የጎበጡ  ሰቀላ ቤቶች ድካም ተጫጭኖናል ማረፍ እንሻለን የሚሉ ይመስላሉ።
በየታዛውና ደጀሰላሙ ጥቂት የማይባሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለማየት ብችልም፣ በዘልማድ «የኔ ቢጤ» የሚባሉትንና በሰው እጅ የሚተዳደሩ ወገኖች በቁጥር ሁለት ወይም ሦሥት ነው ያጋጠሙኝ እነርሱም የአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን።
ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ግን አንድ ታዳጊ የአካል ጉዳተኛ በጣም አስደምሞኛል። ይህ ሁለት እግሮቹ በልጅነት ልምሻ የተጠቁት ልጅን ከሩቅ ሳየው መንገድ ዳር ተቀምጦ የሚለምን ነበረ የመሰለኝ፣ ነገር ግን ጠጋ ብዬ ሳየው እየለመነ ሳይሆን መፋቂያ እየሸጠ ነበር። ጓደኛዬ በጣም ተደስቶና ተገርሞም የአስር ሳንቲሙን መፋቂያ በአስር ብር ገዝቶታል።

ጣና

­
አጣፍቶ የወግ ኩታ ደርቦ የወኔ ባና፣
ደረቱን ገልብጦ እያየ ደመና፣
የጎጃሜው ኩራት ያውላችሁ ጣና።
ምንም እንኳ ዕለቱ እሁድ፣ የሄድኩበትም ሰዓት ረፋዱ ላይ የነበረ ቢሆንም በተንጣለለው የጣና ሀይቅ ላይ ሁለት ታንኳዎች ብቻ ነው ያየሁት።  አብዛኛዎቹ ታንኳዎች ሀይቁ ዳር ታስረው በንፋሱና በውሃው በሚፈጠረው ትንሽዬ ማዕበል ዥዋዥዌ ይጫወታሉ። …ጎብኚውን ምን ዋጠው?
የጣና ሀይቅ ዙሪያ ገባ ለጎብኚዎች እንዲመች ተደርጎ ነው የተሰራው። ሀይቁን «ወክ» እያረጉ ይጎበኙት ዘንድ ቢሄዱበት ቢሄዱበት የማያልቅ ደገጃውን የጠበቀ የእግረኛ መንገድ አለ። ወደፊት ደግሞ ጥሩ ተስፋ ሊፈነጥቁ የሚችሉ ሪዞርቶች እየታነጹ ነው።

የመልስ ጎዞ ወደ አዲስ አበባ

ስካይባሱና ዓባይ በረሀ


መኪናው በዓባይ በረሃ አደጋ እንደ ደረሰበት የሰማሁት ወደ አዲስ አበባ እየተመለስኩ መንገድ ላይ ሆኜ ነበር። ደብረ ማርቆስ ለምሳ ወርደን። ታላቅ እህቴ ናት ደውላ
«አንተ የት ነው ያለኸው?» (ድምጿ ውስጥ ፍርሃት ነግሷል።)
«ከባህር ዳር እየተመለስኩ ነው ምነው?»
«አይ ተወው በቃ ግን ሰላም ነህ አይደል?»
«አዎ ሰላም ነኝ፤ ምነው ምንሆነሻል?»
«‘አባይ በረሃ ላይ የመኪና አደጋ ደርሷል’ እየተባለ ነው ለማንኛውም ተጠንቀቁ፣ ደግሞም ጸልይ።»
ጥቂት ቆይቶም በመኪናዋ የነበርነው በሞላ ዜናውን ሰማን። ደርሰን ባይናችን እስክናረጋግጥም ቸኮልን። አይደርሱ የለምና እንደደረስን፣ አያሌ ፖሊሶች ስፍራውን ተቆጣጥረውት አገኘን። ወርደን አስክሬን በማውጣትም እንድንተባበራቸው ግድ አሉን።
 መኪናው በግምት 200 በሚደርስ ገደል ውስጥ ነበር ተምዘግዝጎ የገባውና ሙሉ በሙሉ የነደደው። በጣም የገረመኝ ነገር ያ ሁሉ ከአርባ ሰው በላይ አስከሬን የት ገባ?... እውን እሳት አጥንት እንኳ አያስተርፍምን? የሰው ልጅ ከንቱ ነው፣ የእውነት ጠዋት ታይቶ ከሰዓት በኋላ እንደሌለ የማለዳ ጤዛ ነው። የአሁን እንጂ የነገ አይደለም። መውጣቱን እንጂ መግባቱን እንኳ በቅጡ የማያውቅ ምስኪን ፍጡር ነው።

ለመሆኑ አደጋው ግን እንዴት ሊደርስ ቻለ?

እንግዲህ ተጨባጭ የሆነ መረጃ ባይሆንም ካደጋው ከተረፉት ሰዎች አንደበት ተሰማ እንደሚባለው መኪናውን ለአደጋ የዳረገው አላግባብ ፍጥነት ነው። ሲጀመር መኪናው ገና ከማለዳው ያለ ተራው ነው ጉዞ የጀመረው። በትክክል ወደ ጎንደር ይመጣ የነበረው መኪና ብልሽት ደርሶበት በዚህኛው ተቀይሯል። እንግዲህ በቅይይሩ ጊዜ በራሱ ሊባክን የሚችል ጊዜ ይኖራልና አሽከርካሪው በሰዓቱ ጎንደር መድረስ አለበት። ስለዚህም ያለወትሮው ሊፈጥን ይችላል።  «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሉም መንደደኛ ከነበሩት ሴቶች አንዷ እመኪናው ውስጥ እንዳለች ከብረትጋ በመጋጨቷ እሷንም ለማሳከም ጊዜ ወስደዋል። እንግዲህ ያንን ጊዜ ለማካካስ ነው ፍጥነቱና ለአደጋው መዳረጉ።

በተዓምር የተረፈው መንገደኛ

ከተሳፋሪዎቹ አንደኛው መኪናው ሴትዮዋን ለማሳከም ይሁን ለሌላ ምክንያት ሲቆም ለሽንት ይወርድና ማንም ሳያስታውሰው መኪናው ጥሎት ይሄዳል። አቤት ሰውዬው በጊዜው ምንኛ ተናዶና አማሮ ይሆን?... ደግሞስ ይሄንን አስደንጋጭና አሳዛኝ ዜና ከሰማ በኋላ ህይወቱ በተዓምር በመትረፏ ምንኛ ሐሴት አድርጎና አምላኩን አመስግኖ ይሆን?...
የሆነው ሆኖ በዕለቱ በተከሰትው ክስተት የሟቾች ወገኖች ተጎዱ፤ የሞቱትማ አንዴ እስከ ወዲያኛው ህቅ ብለዋል ምን ተዳቸው።
እዚያ ቦታ ላይ ጥቂት የማያባል ቆይታ ካደረግን በኋላም በተሳፈርንበት «ኦሮቢላ» መኪና ውስጥ ስንገባ ተመሳሳይ እጣ እንዳይደርስብን ሁላችንም ሰግተን ነበርና ሾፌሩ ትንሽ ፈጠን ያለ ሲመስለን
«· እባክህ መኖር እንፈልጋለን»
«ቀስ በል እንጂ»
«በራሳችን ላይ እስኪደርስ ብቻ ለምን እንጠብቃለን? ለምን በሌሎች ስህተት አንማርም እንዴት ያለ ፍርጃ ነው ጎበዝ?»
እያልን ልባችንን እንደተንጠለጠለ አይገባ የለም አዲስ አባባ ገባን።

እንደ ጥቆማ


ምናልባት መንግስት ካሰበው በላይ ባላውቅም ነገር ግን ቦታ አደገኛ የአደጋ ቀጠና ነውና ከአንጸባራቂ ምልክቶች ባሻገር፣ በብዙ ኤምባሲዎችና የመንግሥት ድርጅቶች ደጃፍ ላይ እንደሚወመጠው በጠጠርና አሸዋ የተሞላ ኮንክሪት ቢቀመጥ፣ ደግሞም በቅርበት በቶሎ ለተጎጂዎች ለመድረስ ይቻል ዘንድ የእሳት አደጋ ብርጌድና የመጀመርያ ዕርዳታ ክሊኒክ ቢቋቋም ምንኛ ሕይወትን መታደግ በተቻለ ነበር።
ለማንኛውም ቸር አውሎ ቸር ያግባን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

No comments:

Post a Comment

ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡