የሆነ ጊዜ ሰዎች ሁሉ ጎጆ ሲቀልሱ፣ የሞቀ፣ የደረጀና የደመቀ ኑሮም ሲኖሩ አየሁና እኔስ «ሁ ማይነስ ሁ?» በማለት፣ ከቅን ልቦና በመነጨ ስሜት፣ ገና የትዳርን ሀሁ ሳላጠና፣ እንደ ብልጦቹ ሀብትና ንብረት ሳላደራጅ፣ ...የማገኛቸውን ሰዎች ሁሉ ሚስት ይፈልጉልኝ ዘንድ ተማጸንኩ። በኋላም ከታላቅ ወንድሞቼ አንደኛው:-
«የእውነት ሚስት ማግባት ትፈልጋለህ?» ይለኛል
«እንዴታ ምን ጥያቄ አለው?» (ፍርጥም ብዬ)
«እንግዲያውስ አንዲት እህት አለች፣ ትዳር ትፈልጋለች፣ ስልኳን ልስጥህና ደውልላት።»
«ስራ አላት?»
«አዎ አላት።»
«ደሞዟ ምን ያህል ነው?»
«አንድ ሁለት ሺ ምናምን… ለዚያውም ‹‹ኤን ጂ ኦ›› ውስጥ ነው የምትሰራው።»
«እውነትህን ነው?... በል እንዲያ ከሆነ ፈጥነህ ስልኳን ወዲህ በል።»
ስልኳን ሰጠኝ።
አፍታም ሳልቆይ ደወልኩላት። ከዚያኛውም ጫፍ
«ሀሎ» የሚል ውብ የእንስት ድምጽ በጆሮዬ አንቃጨለ፡፡
«ሄሎ ሣራ ነሽ?» (ለባለታሪኳ ጥንቃቄ ለጊዜው ስሟን ቀይሬዋለሁ። ምናልባት ሣራ መጣጥፌን እያነበብሽ ከሆነ ‹‹አሰላም አለይኩም›› ብያለሁ በአረብኛ ቋንቋ፡፡ ሰላም ላንቺ ይሁን እንደማለት ነው፡፡)
«አዎ ማን ልበል?»
ስሜን ነገርኳት። ስልኳንም ከወንድሜ ሳይሆን ከሌላ ሰው እንዳገኘሁ አረዳኋት። (ወንድሜ ስልኳን ከእሱ እንዳገኘሁ እንዳልነግራት አስጠንቅቆኝ ነበርና፡፡) ለደቂቃዎች ያህልም በቀጥታ ለምን እንደምፈልጋት አወራኋት። የበለጠ ተገናኝተን እንድናወራም ወፍራም ቀጠሮ ያዝን።
በቀጠሮውም ቀን የክት ልብሴን በተለይም አንዲት በፍጹም የማልረሳት «ስትወርድ ስትዋረድ» የመጣች ታሪካዊ ኮቴን ሽክ ብዬ ወደ ቀጠሮው ስፍራ አመራሁ። «ፎር ዩር ሰርፕራይዝ» ቤታቸው ነበር የቀጠረችኝ። ከግቢያቸውም ዘልቄ የዋናውን በር ሳንኳኳም «ግባ» የሚል ድምጽ ሰማሁ፣ ገባሁ።
ግባ ያለችኝ ሴት ከተንጋለለችበት ረጅም ሶፋ ላይ ቀና እያለችና እየጨበጠችኝ፡
«ሀይ ሰላም ነህ? ቁጭ በል ቁጭ በል፣ ትንሽ እግሬን ወለም አለኝና ስራ ሳልሄድ ቀረሁ።» አለች።
«አም ሶሪ ተጎዳሽ በጣም?» እያልኩ ቁጭ ብዬ በውስጤ የሳልኳት ሳራ እስክትመጣ ጣራ ጣራውን ሳይም፣
«አንተ ነህ አይደል ዳዊት?» ትለኛለች
«አዎ እኔ ነኝ፣ ሳራስ የት አለች ነው ወይስ አንቺ ነሽ?»
«ሳራ እኔ ነኝ፤»
«እኔም እኔ ነኝ፡፡»
ተሳሳቅን። ዕድሜ፣ ስራችንን፣ የወር ገቢያችንን፣ የምንጠላውን፣ የምንወደውን፣ ወዘተ… ቋቅ እስኪለን ድረስ አወራን። የእውነት ግን ለመናገር በስልክ ውስጥ የሳልኳት ሴት አይነት አልነበረችም። እሷም እኔን እንደዚያ። እናም ጨዋታችን ሁሉ ለዛ እያጣ ሲመጣ፣
«ባሌ እንዲሆን የምፈልገው ሰው አድርግልኝ ያልኩትን ሁሉ የሚያደርግልኝ፣ ሁንልኝ ያልኩትን ሁሉ የሚሆንልኝ ሰው ነው። »
«አንቺስ እሱ ያለሽን ሁሉ ልትሆኚ ዝግጁ ነሽ?»
«እኔን አይመለከትም፡፡» (ፍርጥም ብላ)
«እንዴት ምን ማለት ነው?»
«በ…ቃሀ። እኔ ብቻ፤ ለምሳሌ ማታ ቴሌቪዥን እያየ ከሆነ ቲቪውን ጥፍት አድርጌበት ወደ መኝታ ክፍሌ እየጎተትኩት ስሄድ ጸጥ የሚለኝ፣ ደግሞ ጋዜጣ እያነበበ ከሆነ ጋዜጣውን ንጥቅ አርጌው እንዲያወራኝ ስፈልግ ደስ ብሎት ሚታዘዘኝ፣ እ…ህ… ደግሞ አንዳንዴ አለ አይደል… ደስ ሲለኝ በጥፊ ሳጮለው ስቆ ዝም የሚለኝ ወዘተ…»
«እንግዲያውስ አንቺ ሰው ሳይሆን «ሮቦት» ነዋ የምትፈልጊው?» ተናድጄ ነበር። ሳቀች።
‹‹አይ አንተ ሮቦት አልክ››
‹‹አንቺ የምትመኝው ወንድ በምድር ላይ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡››
«ሞልቷል፡፡ ምራቁን የዋጠ ስንት አለ መሰለህ፡፡ በዚያ ላይ አንተ በእድሜ አትበልጠኝም፣»
ቀድሞ ይሄን አውቄ ኖሮ አስቀድሜ "ከሌላ ሰው አንድ አምስት አመት ተበድሬ" ሰላሳ አመቴ ነው ብያት ነበር።
«እሱስ እውነትሽን ነው። ግን ለትዳር የግድ ወንዱ መብለጥ አለበት እንዴ?»
«አዎ። ምክንያቱም እኩያሞች ከሆንን እንናናቃለን። ለምሳሌ አንተ ብትመታኝ ዝም አልልህም፣ መልሼ ነው የምደረግምብህ።»
«አስቀድሞ ነገር በባልና ሚስት መካከል ጠብ ያለሽ በዳቦን ምን አመጣው?»
«አንዳንዴማኮ ይኖራል፣ አለ አይደል እንደ የፍቅር ዱላ አይነት ነገር ያስፈልጋል።»
ብዙ አወራን፣ ብዙም ተፈላሰፍን፤ ይሁን እንጂ የሁለታችንም አሳብ እንደ ሰሜንና ደቡብ ዋልታ ሳይገናኝ ቀረ። በመጨረሻም፡-
«እንግዲህ እኔና አንቺ አልተመቻቸንም መሰል፤»
«መሰለኝ፡፡»
«ታዲያ ሌላ ሰው፣ አንቺ የምትፈልጊው አይነት ሰው ባመጣልሽ ፈቃደኛ ነሽ?» (አንድ እሷ እንደምትፈልገው አይነት በእድሜ ገዘፍ ያለ፣ ከወደግንባሩ ገባ ያለ ወዳጄ ታውሶኝ፡፡)
«ደስ ይለኛል ስልኬን ስጠው፡፡»
ሰጠሁት።
የለም የለም እሷ ራሷ ይዘከው ና ባለችኝ መሠረት ይዤው ቤቷ ድረስ ከተፍ አልኩ እንጂ። ወዲያውም ተግባብተው፣ እኔንም ረስተው ለብዙ ሰዓታት አወሩ። ልጅቱ ከድሮው ቃሏ አንዳችም ፍንክች አላለችም። ትዳር የሞረሞረው ወዳጄም የምትይው ሁሉ ልክ ነው እያለ፣ እሷም ደስ እያላት ከቆይታ በኋላ ተመቻቹ። ግንኙነታቸውም በፍጥነት ተጀመረ። ዕነሆም የፍቅርን ሀሁ አሀዱ ማለት ጀመሩ፡፡ ከጊዜያት በኋላም ያን ሰው አገኘሁትና፡-
«የትዳሩ ጉዳይ እንዴት እየሄደልህ ነው?»
«ጥሩ ነው፣ እስካሁን ደህና ነን፣ ግን ምን እንደምትል ታውቃለህ?»
«አላውቅም።»
«ጠንቀቅ በል፣ ትለኛለች።»
«ምን ማለት ነው?»
«ፍቅር እንዳይዝህ ተጠንቀቅ፤»
«እንዴት?»
«እንጃ፡፡»
«እንዲህ ስትልህ ታዲያ አንተ ምን ትላታለህ?»
«ምን እላታለሁ አንቺ ራስሽ ተጠንቀቂ እላታለሁ እንጂ»
«እውነትህን ነው?»
«አዎ ግን ለራሴ ነው በሆዴ። ለሷ ባፌ እሺ እጠነቀቃለሁ እላታለሁ፤ ለራሴ ግን በሆዴ ባክሽ ራስሽ ተጠንቀቂ እላለሁ።»
«የማያጠግብ እንጀራ፡፡» አልኩ ለራሴ። በቃ የትም ድረስ መጓዝ እንደ ማይችሉ አንዳች ነገር ሹክ አለኝ። በሌላ ጊዜ ቆይቶ ተገናኘን ከዚሁ ወዳጄ ጋር።
«ዘንድሮስ እንዴት ናችሁ?»
«አንተ ደግሞ የሞተ ዘመድ የለህም እንዴ?... የመቸውን?»
«እንዴት … ተለያያችሁ እንዴ?»
«አዎ ሳንጋባ ተፋታን።»
No comments:
Post a Comment
ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡