1-
በጥንት ጊዜ መሬትና ጥንቸል ጓደኛሞች ነበሩ ይባላል፡፡ አብረውም ዕቁብ ይጠጡ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ጥንቸል ዕቁብ ደረሳት፣ ዕቁቡንም ከበላች በኋላ ተራዋ ደርሶ ‹‹ክፈይ›› ስትባል ‹‹ወገቤን›› አለች፣ አሉ፡፡ ይኸው እስከዛሬም አሻፈረኝ እንዳለች፣ ከመሬት እንደሸሸች አለች ይላሉ አበው ጣፋጭ ወጋቸውን ሲሰልቁ፡፡
የኛንም ትውልድ በኔ መነጽር ስመለከት እንዲህ አይነት ነገር ይታየኛል፡፡
ሁለት አይነት ዕዳዎችም እያሳደዱን እንዳሉ እገነዘባለሁ፡፡ የበላነውና ያልበላነው፡፡ እንደ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ሁሉ፤ አባቶቻችን በብዙ ዕዳ ማጥ ውስጥ የተዘፈቀች አገር ነው ያስረከቡን፡፡ የኛ ትውልድ ደግሞ ያልበላውን ዕዳ ሲገፈግፍ የራሱን ለሚቀጥለው ትውልድ ያሸጋግራል፡፡ ታዲያ የሚያሳድደን ዕዳ በየፈርጁ ብዙ ነው፡፡ ምን የማያሳድደን ዕዳ አለ? . . . እንደ ግለሰብና ማኅበረሰብ የቤተሰብ ዕዳ፣ የአገር ዕዳ፣ የወገን ዕዳ፣ የፈጣሪ ዕዳ፣ የፍቅር ዕዳ፣ የመንግሥት ዕዳ፤ ሲያሳድደን፤ እንደ መንግሥት ደግሞ የሕዝብ ዕዳ መግቢያ መውጪያ አሳጥቶናል፡፡ ከሁሉም የከፋው ግን የገዛራስ ዕዳ ነው፡፡ ገና በቤተሰብ ቁጥጥር ውስጥ ያሉ ህጻናት፣ ወይም ደግሞ አቅመ ደካሞችና ህመምተኞች ካልሆኑ በቀር ሁላችንም የየራሳችንን ዕዳ ራሳችን እንሸከማለን፡፡ ነገር ግን ዕዳችንን መሸከም ካቃተን በቤተሰብና ማኅበረሰብ ወይም መንግስት ጫንቃ ላይ ፊጥ ማለታችን የማይቀር ነው፡፡ ጤና እያለ፣ ሙያና ዕውቀቱ፣ ጉልበቱና ችሎታው እያለ፣ መስራት እየቻሉ፤ ነገር ግን ዕዳቸውን በሌላው ጫንቃ ላይ እንደ ሚከምሩ ሰዎች የከፋ ነገር የለም፡፡ ከዚህ አይነት ዕዳስ አምላክ ይሰውረን፡፡

በአንድ ወቅት ነው፤ በሆነ ገጠራማ ስፍራ ትንሹ የበጎች እረኛ በጎቹን ሊያሰማራ ማለዳ ከቤቱ ሲወጣ መንደሩን የሚያቋርጠውና ብቸኛ የነበረው የባቡር ሐዲድ ከፊሉ ብረት በሽፍቶች ተቆርጦ ያያል፡፡
እረኛው ደነገጠ፡፡ የደነገጠው ለብረቱ መዘረፍ ሳይሆን በዚያው ሰዓት ሕዝብ ጭኖ ለሚመጣው ባቡር ነበር፡፡ በተቆረጠውም ሀዲድ ምክንያት በሰዎች ላይ የሚደርሰው አደጋ ታየውና በጣም ዘገነነው፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገብቶት ሳለም፣ ባቡሩ ከሩቅ ጥሩንባውን እያሰማ ሲመጣ ተመለከተ፡፡ ብዙ ሰውና ንብረት ጭኗል፡፡ ባቡሩ ውስጥ ያሉት ሰዎች ከፊታቸው ስላለው አደጋ አንዳችም የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ትንሹ እረኛ ግን አስቀድሞ ጉዳቱን ተረድቷል፡፡ ታዲያ ምንድነው የሚያደርገው ? አንድ ሀሳብ መጣለት፡፡ የለበሰውን ቀይ ሹራብ አውልቆ ባቡሩ እንዲጠነቀቅ በማውለብለብ ምልክት መስጠት፡፡ እንደዚያም አደረገ፡፡ ነገር ግን የትንሹ እረኛ ድርጊት የባቡሩ ሠራተኞች አልገባቸው ኖሮ ባቡሩ ሳይቆም ቀረ፡፡ እረኛው ልጅ በትንንሽ እግሮቹ ከባቡሩ ጎን ጎን እየሮጠና ቀዩን ሹራብ እያውለበለበ ‹‹ሐዲዱ ተቆርጧል፣ ሐዲዱ ተቆርጧል›› ይላል፡፡ ቀጭን ድምጹ ግን በባቡሩ ሞተር ድምጽ በመዋጡ ማንም ሰው የሚለውን አይሰማም፡፡ ቧቡሩ ወደ ግብዓተ መሬቱ እየገሠገሠ ነው፡፡ እረኛው ልጅ የመጀመሪያ ሙከራው እንዳልተሳካለት ሲረዳም፣ ያንን ሁሉ ሕይወት ለመታደግ አንድ ሀሳብ ብልጭ አለለት . . . ሀሳቡንም ተገበረው፡፡
ባቡሩም የተቆረጠው ሐዲድጋ ሊደርስ ጋት ያህል ሲቀረው ቆመ፡፡ የብዙ ሰው ነፍስም ዳነ፡፡ የባቡሩ አሽከርካሪና ሠራተኞች በባቡሩ አጉል ቦታ ላይ መቆም በጣም ተበሳጭተው ወረዱ፡፡ ልጁም ምን አንዳች ነገር ቢያደርግ ነው የባቡሩን ጉዞ ሊገታ የቻለው? በማለት ወደ ባቡሩ ሞተር ሲመለከቱ፤ ያ ቅድም ቀይ ጨርቅ እያውለበለበ ከባቡሩ ጎን ጎን ሲሮጥ የነበረው ትንሽ እረኛ እንዳልነበር ሆኖ ነበር፡፡ ባቡሩንም ሊያስቆመው የቻለው ዘሎ ሞተሩ ውስጥ በመግባቱና አጥንቶቹ የሞተሩ ጥርስ ውስጥ በመቀርቀራቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም የወገኖቹ ፍቅር ዕዳ ነበረበትና፡፡
ምንም እንኳ ታሪኩ በጣም የተጋነነና እውነት የማይመስል ቢመስልም ትውልዳችንን መድረሻ ካሳጡት ዕዳዎች አንደኛውና ዋነኛው የፍቅር ዕዳ ለሚለው ንዑስ ርዕሴ አሪፍ ግብአት ስለሆነልኝ ልጠቀምበት ወድጄያለሁ፡፡
አንዲት የሦሥት ልጆች እናት የሆነች ዘመድ አለችኝ፤ ጥሎባት ዘመዶቿን አለቅጥ የምትወድ፡፡ የሷ መውደድ ከሌላው ለየት ያለ ነው፡፡ በቃ አለ አይደል ሳይጠይቋት ቢቀሩ ሥልክ መታ፣ አሊያም ባካል ተገኝታ ‹‹ምን አስቀይሜህ ነው ያልጠየከኝ፣ ያስለመድከኝን ነገር የነፈግኸኝ፣ እኔኮ እወድሀለሁ፣ ባለቤቴም ስላንተ አንስቶ አያባራም፣ ለልጆቼማ ካፋቸው ውስጥ እንዳለ ከረሜላ ነህ፣ . . .›› እያለች የፍቅር መወድሷን የምታዥጎደጉድ፡፡ በልቼ የጠገብኩ፣ ጠጥቼ የረካሁ፣ ለብሼ ያልሞቀኝ፣ ምቾት አንገላቶኝ ሳለ፣ ያልደላኝ የማይመስላት፡፡ አንዳች ነገር አድርጌላት እንዳይመስላችሁ፤ ሻሽ እንኳ ገዝቼላት አላውቅም በቃ ዝም ብላ ትወደኛለች፡፡ እንዲህ አይነቱን ፍቅር ፈረንጆቹ /Unconditional love/ ይሉታል፡፡ በእከከኝ ልከክልህ /Tit for Tat/ ላይ ያልተመሠረተ ወረት የማያውቀው ፍቅር፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ከርስዎ ዘመድም ውስጥ ቢፈልጉ አያጡም፡፡ እርስዎ ለነርሱ ልዩ ሰው ነዎ፡፡ አንዳንዴ መላእክት የሆኑ ሁሉ ሊመስልዎ ይችላል፡፡ አይድረስብዎ እንጂ እንኳንስ ክፉው ደርሶብዎ፤ በበጎው ጊዜውም ሁሌ ፍቅራቸው ትኩስ ነው፣ አያረጅም፡፡ አገኙ፣ ያው፤ አጡ፣ ያው፤ አማሩ፣ ያው፣ አስቀሙ ያው፤ ያው ነው ፍቅራቸው፡፡ አቤት ደስ ሲል እንዲህ አይነት ሰብዕና! . . . ይታደሏል እንጂ አይታገሉም ይሏል ይሄኔ ነው፡፡
ታዲያ እንዲህ አይነት ፍቅር እኔ በበኩሌ ጭንቅ ይለኛል፡፡ ለምን ቢሉ ባለዕዳ ያደርገኛልና ነው፡፡ የፍቅር ባለ ዕዳ፡፡ በተወደድኩኝ ልክ ካልወደድኩ የፍቅር ባለ ዕዳ ነኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በተሰፈረልኝ ቁና ሙሉ ፍቅር ከፊሉን እንኳ መመለስ የማልችል ምስኪን መሆኔን ሳስበው ምን ዓይነት መቅመቆ ብጋት ነው እንደነዚያ ሰዎች ቅንጣት ፍቅር የሚጣባኝ? ብዬ አስባለሁ፡፡ የዕዳ አይነት አውቃለሁ የፍቅር ዕዳን ያህል ግን ከባድ አላየሁም፡፡ የፍቅር ዕዳ ያለበት ሰው ነፍሱን ከሞትጋ እንኳ ያወራርዳል፡፡
እዚህ ላይ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መመልከት እንችላለን፡፡ ታላቅ ክብሩን አስትቶ፣ ከሰማየ ሰማያት ያስወረደውና እንደ ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ ያስዋለው ሌላ አልነበረም፣ የፍቅር ዕዳ የሚሉት ትልቅ ጉዳይ ዘንቆ ይዞት እንጂ፡፡
አሁን አሁን ግን ከትውልዳችን የምንሰማውና የምናየው ድርጊት ዕድሜልካችንን ከምናውቀው ባህልና ወግ ያፈነገጠ እየሆነብን ነው፡፡ ግሎባላይዜሽኑ ያመጣብን ጣጣ ይሆን? . . . እንጃ፡፡ ለምሳሌ አንዳንዱ የፍቅር ዕዳውን የሚወጣው ‹‹ከራሴ በላይ አፈቅራታለሁ›› በሚላትና ‹‹በሚሳሳላት›› ሴት አካል ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት በመፈጸም ነው፡፡ በሚወዳት ፍቅረኛው ወይም ሚስቱ ፊት ላይ አሲድ ይደፋና አሊያም አይኖቿን በስለት ይጓጉጥና ምነው? ቢሉት አንዳች ሳይፀፀት ‹‹በቃ ስለማፈቅራት ነው!›› ብሎ መልስ የሚሰጥ ትውልድ አባል ነን፡፡ የምንመራበት የእምነት መመሪያና ግብራችን እርስበርሱ ይጣረሳል፡፡ መጽሐፉ ‹‹ስለ ወዳጅህ ነፍስህን አሳልፈህ ስጥ፡፡›› ሲል፤ የእኛ ‹‹አፍቃሪ›› ትውልድ ግን ‹‹ወዳጄንስ ከማጣት፣ ይሻለኛል አይኗን ባጠፋት!›› ይሆናል መልሱ፡፡
-2-
በድሮ ጊዜ ‹‹ዱቤ ከልል›› የሚሉት ኮፍያ አደራረግ አለ አሉ፡፡ ኮፍያን ከወደ ግንባር ዝቅ አድርጎ አይንን በመከለል ከአበዳሪ ዕይታ የመሰወር ጥበብ ነው፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን የዘመኑ ‹‹ፍሪኪዎች›› ይጠቀሙበታል፡፡ ከዕዳቸው ለመሸሽ ሳይሆን ለ‹‹መፈረክ›› ወይም ለመዘነጥ፡፡
ገና የመጀመርያ ደረጃ ክፍል ተማሪ እያለሁ አንድ ጓደኛ ነበረኝ፤ በዚያች እድሜው ሸንኮራ አገዳ ሸጦ ምስኪን ቤተሰቡን የሚደጉም፡፡ ትዝ ይለኛል ጓደኛዬ ከትምህርትቤት እንደተመለስን ቶሎ ብሎ ቢላዋውንና ሸንኮራውን ይይዝና ከቤታቸው ጥቂት ፈንጠር ብላ ወደ በቀለችና ዘወትር ከጥላዋ ስር፣ ሥራ አጥ ወገኖች ቁጭ ብለው ‹‹ድድ ከሚያሰጡባት›› የግራር ዛፍ ስር ቁጭ በማለት ሸንኮራውን ይቸረችር ነበር፡፡ ገና በብላቴናነቱ ቤተሰቡን የማገልገል የዕዳ ቀንበር አርፎበታልና፡፡ ‹‹ያባት ዕዳ ለልጅ›› ይሏል እዚህጋ ነው፡፡ ታዲያ አንድ ጊዜ አንድ የሠፈራችን ጉልቤ ልጅ
‹‹ሸንኮራ ቁረጥልኝ!›› ይለዋል፤
‹‹የስንት?›› ጓደኛዬ እየፈራ
‹‹የአምስት ሳንቲም፡፡››
‹‹እሺ፡፡››
ግማሽ አንጓ ቆረጠለት፡፡ ጉልበተኛውም ልጅ አምስቷን ሳንቲም ሳይከፍል ሲሄድ ጓደኛዬ እምባው እየመጣበት፡-
‹‹ሂሳብ አልከፈልከኝም እኮ፣ አምስት ሳንቲሜን ክፈለኝ እንጂ!›› ይለዋል እየተከታተለ
ጉልቤውም ልጅ በሰፊው አፉ ሸንኮራውን እያሸረመደ
‹‹ይከፈልሃል!›› ይለዋል ቆጣ እያለ
‹‹መቼ ነው ምትከፍለኝ?››
‹‹ነገ!››
ነገ ነገን ሲወልድ፣ ሳምንት ሲሆን፤ ሳምንት ሳምንትን ወልዶ ወር ሲጠባ፤ ወርም ወርን እየወለደ አመት ሲሆን፤ ጉልቤው ልጅ የውሀ ሽታ ሆነ፣ ዕዳውንም በዚያው ረሳ፡፡ ጓደኛዬ ግን ‹‹የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም›› እንዲሉ፤ ድንገት የሆነ ቦታ ወይ ኳስ ሜዳ አሊያም ትምህርት ቤት ልጁን ሲያየው ይሮጥና፡-
‹‹አምና የተበደርከኝን የአምስት ሳንቲም ሸንኮራ ሂሳብኮ አልከፈልከኝም›› ሲለው
ጉልበተኛው ልጅ ደረቱን እየነፋ የሚያውቃትን ቃል ‹‹ይሰጥሀል!›› ይላል፡፡ መቼ እንደሚሰጠው ግን እንኳን ጓደኛዬ እሱ ራሱም አያውቅም፡፡ ለጉልቤውም ልጅ ቅፅል ስም አወጣንለት፣ ‹‹ይሰጥሀል›› ብለን፡፡ ይኸው እስከዛሬ ከዚያ የህፃንነት ጓደኛዬጋ ስንገናኝ ስለ ‹‹ይሰጥሀል›› ትዝታ ስናነሳ፤ ምንም እንኳ ጓደኛዬ ትልቅ ደረጃ ላይ ቢደርስም ቅሉ፤ አምስት ሳንቲሟን ግን ፈጽሞ አይረሳትም፡፡ ዕዳ ናትና፤ የገንዘብ ዕዳ፡፡
አሁን አሁን ለምን እንደሆነ እንጃ እንጂ ብዙ ሰው ዕቃም ሆነ ገንዘብ ተበድሮ መመለስ አይሆንለትም፡፡ ያበደሩት እርስዎ ከሆኑ ወይ ከሩቅ ይሸሽዎታል አሊያም ይደበቅዎታል፡፡ ይባስ ካለ ደግሞ አንዳች በደል የበደሉት ያህል ያኮርፎዎታል፡፡ ለምንድነው ግን መበደር የሚያስደስተንን ያህል መመለስ የሚያስከፋን?. . .
አንድ ጓደኛ ነበረኝ፣ ሁሌ ደሞዝ ሲደርስ ደርሶ የሚከፋው፡፡ ለምን መሰላችሁ? መላ ደሞዙ ቀድሞ በብድር ስላለቀ ነው፡፡ ከሚቀጥለው ወር ደሞዙ ላይ ‹‹ኢንአድቫንስ›› በመውሰድም ሠራተኛውን ይመራ ነበር፡፡ ታዲያ ሁሌ ደሞዝ ሊቀበል ሲሄድ አንድም ቀን ‹‹እስቲ ደሞዜን ልቀበል›› ብሎ አያውቅም፤ ይልቁንስ ‹‹እስቲ ደሞዛቸውን ልቀበልላቸው፡፡›› ነበረ እንጂ የሚለው፡፡ ከገጠመኜ አንድ ላክል፤
እፍኝ በማትሞላ ደሞዜ ‹‹አልበላም አልጠጣም›› ብዬ የገዛኋት አንዲት ጥቁር የቻይና ‹‹ሱፍ››፣ የክት ልብስ ነበረችኝ፤ ብዙ ጊዜ ከነጭ ሸሚዝጋ እለብሳት ስለነበረም ብዙ ሰዎች ሐኪም ያዘዘልኝ ይመስላቸው ነበር፡፡ ‹‹ሳይተርፋት አበድራ፣ . . .›› እንዲሉም የቤት አከራዬ ‹‹ፍንዳታ›› ልጅ፣ ባንድ የተረገመች ቀን ከምወዳት የክት ልብሴ አለያይቶኛል፡፡ እንዲህ ነው የሆነው አንድ ቀን ጸጉሩን እየቋጨብኝ፡- ‹‹ባክህን ሠርገኛ ነኝና ሱፍህን አውሰኝ፡፡›› ይለኛል፡፡ ምን ችግር አለው፣ ውሀ ለሚጨርሰው ልብስ ብዬም ያልጠየቀኝን ነጯን ሸሚዜን ጨምሬ አውሰዋለሁ፡፡ በሠርጉም ዕለት ደመቀበት፣ ‹‹ካይን ያውጣህ››ም ተባለ፡፡ በኋላም ባለው ቀን ልብሴን መመለስ ‹‹ረሳ››፡፡ ከሩቅ ሲያየኝ ሲሸሸኝ፣ እኔም ላለማሳፈር ያላየሁ ለመምሰል ስጥር፣ ድንገት ደግሞ የሆነ ቦታ ስንገናኝ ቀንዷን እንዳሏት ላም ፈጥኖ በሌላ መንገድ ሲቀይስ ብዙ ጊዜ ሆነ፡፡ ወደቤቱም በጣም አምሽቶ ነው የሚገባው፡፡ ‹‹ለማኝ እንትን›› ሳይልም ወደ ሚሄድበት ይሄዳል፡፡ እናም አንድ ቀን ሲብስብኝ አፍ አውጥቼ ልብሴን መልስ እንጂ ብሎ መጠየቅ ከሱ ይልቅ ቢያሳፍረኝ ከኔ ይልቅ ልጁን ይቀርበው ለነበረ ጎረቤቴ አማከርኩት፤ ጎረቤቴም ያገኘውና፡- ‹‹የሰው ልብስ ተውሶ አለመመለስ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ባለታሪካችንም ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው? ‹‹ከፈለኩ አልሰጠውም! ምን ያመጣል?›› . . . እውነትም በጊዜው ምንም የማመጣው ነገር ስላልነበረ፤ እሱም ሳይመልስልኝ እኔም ዳግመኛ አፌን ሳላበላሽ በሰላም ተለያየን፡፡. . . የሰው ገንዘብ እና ዕቃ እግር አውጥቶ፣ አክናፍ አበጅቶ የሚያሳድደው ትውልድ አባል ነን፡፡

-3-
አንድ የማልረሳቸው ዘመድ አሉኝ፤ የኮርያ ዘማች፡፡ ከልጆቻቸው አንዷ ውጪ አገር ትኖር ነበረ፡፡ የጉብኝት ፈቃድ አግኝተውም ሊያዩዋት ሄዱ፡፡ ልጅ ወደስራዋ ስትሄድም ኮፍጣናው የኮርያ ዘማች፣ ‹‹የጠቅል አሽከር!›› ቤት ተቀምጦ በማያውቁት ‹‹የወፍ ቋንቋ›› የሚለፈልባቸውን ቴሌቪዥን መመልከቱ ቢሰለቻቸው፣ አንድ ሀሳብ ብልጭ አለባቸው፤ ወጣ ብሎ ሽርሽር ማድረግ፡፡ ወጡም፡፡ ግና መመለሱ እንደመውጣቱ ቀላል አልነበረምና፣ የጭንቅ አማላጅቱን ሲማጠኑ ያየ ያገር ልጅ መሳይ ሰው፣ በርሳቸው አባባል በ‹‹ ወፍ አፉ›› አንዳች ነገር ቢላቸው፣ አማርኛ የረሳ ሀበሻ ነበር የመሰላቸው፡፡ እንዳልገባቸውም ሲረዳ ትቷቸው ወደ ጉዳዩ ቢሄድ ጭራሽ አንጀቱ የጨከነ የወንዛቸው ልጅ መስሏቸው እንባቸው አቀረረ፡፡ የማታ ማታም ሁኔታውን ሁሉ ሲረዱ፤- ‹‹ለካንስ ቆዳው የጠየመ ሁሉ የወንዝ ልጅ አይደለምና፡፡›› ብለዋል፡፡ (የደማሙ ብእረኛ መንግሥቱ ለማን ዘመን አይሽሬ ተወዳጅ ግጥም እዚህጋ ያስታውሷል፡፡ ‹‹ባሻ አሸብር ባሜሪካ››ን)
በአገር ቤት የጎሪጥ ሲተያዩ የነበሩ ሰዎች ባህር ማዶ ሲገናኙ እንደናት ልጅ ያህል ተቃቅፈው ይላቀሳሉ ይባላል፤ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ባላውቅም፡፡
አንደኛው ኢትዮጵያዊ በባዕድ አገር ያጋጠመውን ላክልና ወጌን ልቀጥል፤ ገና ከናት አገሩ መለየቱ ነበር፤ ዙሪያ ገባው ሁሉ ነጭ በሆነበት በባዕድ ምድር፤ እሱን የሚመስሉ ሁለት ሰዎች ያይና ፊቱ ሁሉ ጥርስ በጥርስ ሆኖ፡-
‹‹በጣም ደስ ይላል እናንተን በማግኘቴ ኢትዮጵያውያን ናችሁ አይደል?›› ይላቸዋል፡፡ ሰዎቹም ለጊዜው ስሙን በማልጠቅሰውና ያገራችን ብሔር ከሆነው አንዱን ጠርተው ‹‹የለም፤ እኛ እንዲህ ነን›› ብለውታል በእንግሊዝኛ፡፡
እዚያ ሩቅ ምን አስወሰደን እዚሁ ባለንበት አገር አይደል እንዴ ስንቱ ስላልተማረና ቦታው ስለማይመጥነው ሳይሆን በዘር ሐረግ አለመገናኘት ብቻ ስንት ነገር የሚያመልጠው ? . . የወገን ዕዳ የሚያሳድደው ትውልድ አባላት ነን፡፡
-4-
ያላንዳች ዋጋ ንጹህ ውሀዋን ተጎንጭተው፣ መልካም መዓዛ ያለው አየሯን ምገው፣ ያለ ሰባራ ሳንቲም የታሪክ ጉልላቶቿንና ቅርሶቿን፣ ለም ሸንተረሮቿንና ወንዞቿን፣ ብርቅዬ እንስሶቿንና አራዊቶቿን፣ ተዘክሮ የማያልቅ ባህሏንና ትውፊቷን ሚያገኙት ባገርዎ ነው፡፡
ማለዳ አንድ ሁለት ያሉት የብቅልና ጌሾ ውህድ ካናትዎ ወጥቶ፣ ሆድዎ ያባውን፤ በጓደኛዎ አሊያም በልጆችዎ እናት ላይ ቢያላቅቁ፣ በሀገርዎ ነው፤ በወገንዎ መሀል፡፡ ቢበሉና ቢጠጡ፣ ቢለብሱና ቢያጌጡ ከወገንዎ መሀል ሆነው ነው፡፡ ‹‹ሁሉም በሀገር ነው፡፡›› እንዲል ድምጻዊው፡፡ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ግን ባዕድ ምድር ሄጄ እሞክረዋለሁ ቢሉ ራስዎን ዘብጥያ ያገኙታል፤ ያኔም ያገር ዕዳ ምን ማለት እንደሆነ ይገባዎታል፡፡
ይሁንና እንዳለመታደል ሆኖ ላውሮፓ እግርኳስ ያለውን ስሜት ያህል ላገሩ ባህልና ወግ ደንታ የማይሰጠው ትውልድ አባላት ነን፡፡ ‹‹ለመከራ የጣፈው. . .›› ሆኖባትም ውዲቷ አገራችን ጎረቤት ሄዳ ‹‹ሽሮ አበድሩኝ›› ካለች ዘመናት አለፉ፣ መንግስታት ተፈራረቁ፡፡ ዕዳውም እንደ ጎበዝ ገበሬ ክምር ሲከመር ሲከመር ሰማይ ነካ፡፡ የበላውም ትውልድ እያለፈ፣ ያልበላው ትውልድ ተተካ፡፡ መቼም አንዴ ዕትብቱ ካፈሯ ተዋህዷልና እዳው ገብስ ነው፡፡ ግና ትውልዱ መቼ ይሆን የዕዳው ክምር እንደ እምቧይ ካብ እሚናድልን? ሲል ራሱን ሲጠይቅም ዕድሜልኩን ዕዳው በሄደበት ሁሉ እንደ ቀትር ጥላ ይከተለዋል፡፡
አበው መጨረሻዬን አሳምርልኝ የሚሏት ነገር አለቻቸው፡፡ መጀመርያው አምሮ መጨረሻው ሲበላሽ እንደማየት የሚያስፈራ ነገር የለምና፡፡ የአያሌ አፍሪካ መሪዎች ዋናው ችግር ሌብነት፣ ስግብግብነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ብሔራዊ ስሜት አልባነት፣ ቸልተኝነትና ንቀት ብቻ ሳይሆን መጨረሻን አለመገመትም ነው፡፡ የተራበ እባብ በቀጭኑ የጠርሙስ አንገት አስግጎ ወተት ወዳለበት የጠርሙስ ሆድ ሲገባ በጣም ይቀለዋል ይባላል፡፡ ሲወጣ ግን ጭንቅ ነው፤ ወተቱን ጠጥቶ ሆዱ ተወጥሯልና፡፡ ምናልባት ያለ ችግር ለመውጣት የጠጣውን ሁሉ መትፋት ይኖርበት ይሆናል፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ከሥልጣን የተገረሰሱትም ሆነ ከሥልጣን ኮርቻ ላይ ያሉት የሕዝባቸው ዕዳ አለባቸው፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕዳ፣ የዲሞክራሲ ዕዳ፣ ሀሳቡን በነጻነት ይገልጽ ዘንድ አጨብጭቦ መንበር ላይ ለሰቀላቸው ሰው ዕድል ያለመስጠት ዕዳ፣ ያልተዛባ ፍትህ ዕዳና ወዘተ . . . ለዚህም ነው የብዙዎቹ መጨረሻ እንደ ጅማሬያቸው የማያምረው፡፡ አብዛኞቹ የወተቱ ጠርሙስ ውስጥ እስኪገቡ ድረስ ነው ለሕዝብ የቆሙ የሚመስሉት፡፡ አንተ ድምጽህን ስጠን እንጂ እንዲህና እንዲያ እናደርግልሀለን ካሉ በኋላ የራሳቸውን መደብ ነው የሚያበጁት፡፡ ይሁንና አጨብጭቦ ከዙፋን የሰየመ እጅ፣ ቁልቁል ጎትቶ ሲያወርድ ርህራሄን አያውቅም፡፡
አያቴና አባቴ ከዚያም በላይ ያሉቱ ሰዎች ከኖሩበት ዘመን ጀምሮ የአገራችን መንግስታት ሕዝባቸውን የመውደድና የማክበር ዕዳ፣ የእኩልነትና የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የነጻነት ዕዳ፣ ባጠቃላይ የመልካም አስተዳደር ዕዳ አለባቸው፡፡ ሕዝቡ ብቻ በየዘመናቱ ለሚፈራረቁት ገዢዎች ሳይወድ በግድ ሲሰግድና ሲያረግድ፣ ራሱ ሳይጠግብ ገዢዎችን ሲያጠግብ፣ ጥሪቱን ሲገብር፤ ደግሞ ሌላኛው ሲመጣ፣ እንደ ጭዳ በግ ልጁን ለጦርነት ሲገብር፤ መሪዎችን የጠላት ያህል መጥላትና መፍራት ያዘ፡፡ በብዙ የአፍሪካ አገሮች መሪና ተመሪ፣ መንግሥትና ሕዝብ፣ ትርጉሙ ተዛብቶ እንደ ነብርና ሚዳቋ፣ ማለት ነው፡፡
አንድ አፍሪካዊ ህጻን አንድን ፖሊስ ሲያይ ድመት እንዳየች አይጥ ቢበረግግ ምክንያቱ ሌላ ሳይሆን፤ ለአፍሪካዊው ህፃን ፖሊስ ማለት በያዘው በትር ሰውን የሚነርት፣ በከስክስ ጫማው ቅልጥም የሚሰብር፣ በያዘው ጠመንጃ ሰደፍ ካፈር የሚያደባይና ሲያልፍም ምላጭ ስቦ ነፍስ የሚቀጥፍ ስለሆነ ነው፡፡ ለብዙ የአፍሪካችን ሕዝብ ገዢ ማለት አስተዳዳሪ ሳይሆን አስጨናቂ፣ መሪ ሳይሆን አንበርካኪ፣ አርአያ ሳይሆን የጭካኔ አምሳያ፣ አዋኪና ነጣቂ ነው፡፡ ለዚህም ነው የብዙ አፍሪካ አገራት መንግስትና ሕዝብ ዕጣ ፈንታቸው አንድ ላይ እንደበቀሉ አጋምና ቁልቋል የሆነው፡፡ ለዚህም ነው ታሪካችን ሁሉ አንድ እጁ የጦርነት፣ አንድ እጁ የድህነት፣ ሌላው እጅ የሌብነት፣ ሌላው ደግሞ የጎጠኝነት እያለ እያለ የሚሄደው፡፡ መንግስት የሕዝቡን ፍላጎት ተረድቶ ሲያከብርና ፍላጎቱን ሲሞላለት ዕዳው ቀለለለት፡፡ ሕዝብም ያኔ በግዴታ ሳይሆን በውዴታ ለመንግስቱና ለሕጉ ሲገዛ ዕዳው ገብስ ይሆናል፡፡ የነጻነትን ችቦ ሳይለኩሱ ነጻ ሕዝብ መመኘት፣ የዲሞክራሲን ጮራ ሳይፈነጥቁ በመንግሥት ላይ የሚደገፍና የሚታመን ትውልድ መሳል፣ ለእውነት ቆሞ የሚፈርድ የሕግ አካል ሳይገነቡ ከሙስና የጸዳ ትውልድ መጠበቅ በራሱ የዋህነት እንጂ ምን ይባላል?

መንግስት ያልዘራውን ነገር ከሕዝቡ መጠበቅ አይገባውም፡፡ ሕዝብም ያልሰጠውን ነገር ከመንግስት መሻት የለበትም፡፡ ዕዳውን በትክክል መወጣት አለበትና፡፡ ግብሩን በጊዜና ባግባቡ ሳይከፍል፣ የመሠረተ ልማት፣ የትምሕርትና የሕክምና ተቋማት፣ መመኘት ጉምን የመዝገን ያህል ነው፡፡ ሕዝብ በትክክል ዕዳውን ከከፈለ የገዢ ፊት አያስፈራውም፡፡ መንግስትም የሕዝብን ዕዳ ተረድቶ ፈጥኖ ከከፈለ የአብዛኛው በተለይም የአፍሪካ መሪዎች ዕጣ ይገጥመኛል ብሎ አይሰጋም፡፡
አንድ ገበሬ ለበርካታ ወቅት የለፋበትን ምርት በጎተራው ከጨመረ በኋላ ዝም ብሎ መተኛት የለበትም ሌላ ትልቅ የቤት ስራ አለበትና፡፡ ጎተራው ውስጥ ያሉትን ነቀዞች ፈጥኖ ማጥፋት አለበት፡፡ አለዚያ ነቀዝ ነቀዝ ነውና ያ ሁሉ ምርት በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንዳልነበር ይሆናል፡፡ ነቀዝ የማጥፋት ዕዳ አለበት ገበሬው፡፡
መንግስትም የሕዝብን ሐብት አላግባብ የሚያባክኑ ነቀዞችን፣ ሌቦችን፣ ስግብግቦችን ማጥፊያ መርዝ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ ፖሊሲና መመሪያ ብቻውን ፋይዳ የለውም፡፡ ሥር ነቀል ርምጃ ካልተወሰደ በቀር፡፡ ሌባ እንዴት እንደሚሰርቅ ከማሰቡ በፊት እኛ እንዴት አድርገን እንደምትጠነቀቀው ካወቅንበት ችግር የለውም፡፡ አለዚያ ‹‹በራቸውን ሳይቆልፉ፣ ሰውን ሌባ ይላሉ፡፡›› እንዳለችው ውሻ መሆን ነው ትርፉ፡፡ ሕዝብና መንግሥት እርስበራሳቸው ዕዳቸውን በትክክል ካልተወጡም የዕዳው ገፋች ቀማሽ የሚሆነው ትውልዱ ነው፡፡

-5-
የቄሳርን ለቄሳር እንደከፍልን ሁሉ የፈጣሪን ዕዳ ለፈጣሪ መክፈል ደግሞ ብልኅነት ነው፡፡ ዕዳችንን እንድንወጣ ግድ ተብለናልና፡፡ መጽሐፉ ራሱ ዕዳውን ላምላኩ የማይከፍልን ሰው ‹‹ሌባ›› ይለዋል፡፡ ደግሞም ራሱ ፈጣሪ ‹ሰርቃችሁኛል›› ይላል፡፡ ‹‹ጥቂት ስጡኝና በብዙ ልመልስላችሁ፡፡›› ሲልም ያክላል፡፡ ‹‹ያኔ የሰማይን መስኮት ባልከፍትላችሁ፣ የምድርንም በረከት ባላትረፈርፍላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፡፡›› እያለም ይቀጥላል፡፡
ከብዙ ሰዎች ብልጥግና ጀርባ ለፈጣሪ የሚከፈለውን ዕዳ በትክክልና በሰአቱ ከመክፈልጋ ይያዛል፡፡
ከብዙ ሰዎች ብልጥግና ጀርባ ለፈጣሪ የሚከፈለውን ዕዳ በትክክልና በሰአቱ ከመክፈልጋ ይያዛል፡፡
ማክዶናልድ የተባለው ዝነኛ አሜሪካዊ የበርገር አምራች ኩባንያ ባለቤት ሲናገር ይህን እውነት ነው ያስረዳው፡፡ ማክዶናልድ ቅዱስ መጽሐፉ እንደሚያዘው ከመቶ አስሩን እጅ አይደለም ለፈጣሪው የሚሰጠው፤ ይልቁንስ ዘጠና እጁን እንጂ፡፡ ያም ሆኖ በረከቱና ሐብቱን መቆጣጠር ሌላ የቤት ስራ ሆነበታል፡፡
ለመሆኑ ለፈጣሪያችን የምንሰጠው እርሱ አጥቶ ነው እንዴ ?. . . አይደለም፡፡ ብሩና ወርቁ፣ አልማዙና ፈርጡ የእርሱ ሆነው ሳለማ እንዴት ያጣል ?. . .ነገር ግን በኛ ጥቂት ስጦታ ሊባርከን አስቦ ነው እንጂ፡፡
ገበሬ ዘሩን ከበላ፣ ለከርሞ ራሱንና ቤተሰቡን ብሎም ሀገሩንና ወገኑን ረሀብ ላይ ይጥላል፡፡ ነገር ግን ለከርሞ የሚዘራውን ዘር ከፍ አድርጎ ነቀዝና አይጥ እንዳያጠቁት ከጎጆው ምሰሶ ላይ ሊሰቅል ይገባዋል፡፡ ታዲያ በጎጆው ውስጥ አንዳች የሚላስም ሆነ የሚቀመስ ነገር ቢያጣ ያንን ዘር ቀቅሎም ሆነ ቆልቶ አይበላውም በረሃብ ይሞታታል እንጂ፡፡ ለምን ቢሉ ዘር ነው ነው መልሱ፡፡ ዘር አይበላም ነውር ነው፡፡
ይሄ ሚስጥር እኛጋም ይሰራል፡፡ የቄሳርን ለቄሳር (የመንግሥትን ለመንግሥት) እንደ ሰጠን ሁሉ፤ የፈጣሪንም ለፈጣሪ ልንሰጥ ይገባናል፡፡ ድህነትን፣ ረሀብን የማስወገጃ ዋናው ቁልፍም ይህ ነው፡፡ ዘርን አለመብላት፡፡ ነገር ግን ካሳለፍነው ረጅም ታሪካችን እንደምንረዳው የዘር መብላት ዕዳ አለብን፡፡ ጀርባችን ላይ እንደ መርግ የተጫነን እዳ ብዙ ነው፡፡ ብንቆጥረው ብንቆጥረው የማንዘልቀው፡፡ ሁላችንም በተሰማራንበት መስክ የየራሳችን ዕዳ አለብን፡፡ የራስ ዕዳ፣ የቤተሰብ ዕዳ፣ የጎረቤት ዕዳ፣ የወገን እዳ፣ የአገር እዳ፣ የመንግሥት ዕዳ፣ የፈጣሪ ዕዳ፣ የፍቅር እዳ፣ የዘመድ ዕዳ፣ የገንዘብ እዳ፣ እዳ፣ እዳ፣ እዳ. . . ዕዳውን ሳይከፍል ከሚያልፍ ትውልድ ይታደገን፡፡ ዕዳችንንም ሳንከፍል ከማለፍ ይሰውረን፡፡ ሌላውስ ሌላ ነው፣ እዳው ገብስ ነው፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !!
(ይህ መጣጥፍ በሪፖርተር ጋዜጣ የካቲት 14 ቀን 2004 ዓ.ም ረቡዕ እትም የወጣ ነው፡፡)
(ይህ መጣጥፍ በሪፖርተር ጋዜጣ የካቲት 14 ቀን 2004 ዓ.ም ረቡዕ እትም የወጣ ነው፡፡)
No comments:
Post a Comment
ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡