Saturday, March 3, 2012

የበላንን የሚያክልን ማነው?

‹‹እንደራሴዎቻችን›› እንደራሳቸው ወይስ እንደራሳችን?
እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ብዙውን ጊዜ ኢቴቪን የምከፍተው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ የተባለ ሰሞን ነው፡፡ ለምን ቢሉ የሚናገሯቸው በዋዛ የተዋዙት ቁምነገሮች ይመስጡኛልና ነው፡፡ የእውነት ለመናገር ጠቅላይ ሚንስትራችን አንደበተ ርዕቱ ናቸው፡፡ ቅመም ንግግራቸው  የባተሌውን ቀልብ ሳይቀር የሚስብ ነው፡፡ የሰሞኑንም የፓርላማ ንግግራቸውን ለመስማት ከቴሌቪዥኔ ፊት ተሰይሜያለሁ፡፡ 


እንግዲህ ብዙ ጊዜ ሌሎች አካላት ሪፖርት ሲያቀርቡ የፓርላማውን ድባብ መመልከት መንፈስን ዘና ሚያደርግ ነገር አለው፡፡ እንዴት?. . . ቢሉ ‹‹ካሜራ ማኑ›› ተሳስቶ አሊያም ሆነ ብሎ በቴሌቪዥናችን መስኮት የሚያስቃኘን አንዳንድ ግርም የሚሉ ትዕይንቶች አሉና፡፡
 ለምሳሌ አንዳንዴ አንደኛው የተከበሩ ‹‹እንደራሴ›› ካንገታቸው ጎንበስ ደግሞ ቀና ሲሉ ያሳየናል፡፡ ታዲያ በሪፖርቱ መስማማታቸውን ከመግለጽ ውጪ ጭንቅላትን ማነቃነቅ ምኑ ላይ ነው ክፋቱ ይባል ይሆናል፡፡ እውነት ነው፤ ክፋትማ የለውም፡፡ ችግሩ እኚያ የተከበሩ ‹‹እንደራሴ›› ጭንቅላታቸውን እንዲያ መወዝወዛቸው እርስዎ እንዳሰቡት በሪፖርቱ መስማማታቸውን ለመግለጽ ሳይሆን፣ እንደ የቁርጥ ቀን ባላጋራ በድንገት ከመጣባቸው እንቅልፍ ጋር ትንቅንቅ ገጥመው መሆኑ ነው እንጂ፡፡ (በእርግጥ የወከሉት ሕዝብ ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳ እንጂ በእንቅልፍ የሚያዳፋ ባይሆንም)
ብዙ ጊዜ ግን ሪፖርቱን የሚያቀርቡት የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ መላው የተከበረው የፓርላማ ዕድምተኛ ማለፊያ ቡና እንደጠጣ ጎበዝ የተነቃቃ ይሆንና በፓርላማው ሳቅና ደስታ ይሆናል፡፡ ይሁንና ዛሬ ብዕሬን የመዘዝኩት ስለ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጨዋታ አዋቂነት አንዳች ነገር ለማለት ሳይሆን፣ ስለ ‹‹እንደራሴዎቻችንን›› ጥቂት ነገር ለማለትና አክዬም በዚህ ጽሑፍ ላይ ለራሴ በሰጠሁት የ‹‹እንደራሴነት›› ሥልጣን ተጠቅሜ ለተከበሩ ጠቅላይ ሚንስትራችን ጥቂት አቤቱታዎች ላሰማ ፈልጌ ነው፡፡
እንግዲህ ካልተሳሳትኩ አንድ ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ሕዝብን ወክሎ ፓርላማ ሲገባ ዓላማው የሕዝቡን ጩኸት ለመጮህ፣ በሕዝቡ አንደበት ብሶቱን፣ ሐዘኑን፣ ደስታውንና በአጠቃላይ ስሜቱን ለማሰማትና የአዕላፋትን ሐሳብ በጥቂት ሰዎች አንደበት ለመግለጽ ይመስለኛል፡፡ በሌላ አነጋገር እንደቃል አቀባይ ማለት ነው፡፡ ስማቸውም ‹‹እንደራሴ›› አይደል?. . .
ታዲያ ብዙ ጊዜ ‹‹እንደራሴዎቻችን›› እዚያ ፓርላማ ውስጥ ከሚጠይቋቸው ጥያቄዎች፣ ከሚሰጧቸው አስተያየቶች ተነስቼ በትንሽዬ አዕምሮዬ ስታዘብ፣ ‹‹እንደራሴዎቻችን›› እንደራሳችን ሳይሆን እንደራሳቸው እየሆኑብን፣ የበላንን የሚያክልን እያጣን ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች የስብስባ ተካፋዮች ብቻ ሲሆኑ ማየት ደግሞ ደስ አይልም፡፡ ‹‹ወንድምህ ሆዱ ዳቦ ሲፈልግ አንተ ግን በደህና ሂድ፤ እሳትም ሙቅ አትበለው፤›› እንዲል መጽሐፉ፡፡
ሆዱን ለራበው ሰው እራፊ ጨርቅ ምኑ ነው?. . . ምኑም፡፡ ይልቅስ የተራበ ሆዱን እንዴት ማስታገስ እንዳለበት መላ ሲመታ፣ የውርጭና የንዳድን ግርፋት ከነመፈጠራቸውም ይረሳቸው እንደሁ እንጂ፡፡ በአጭር ቃል በአደባባይ የሚታየው እውነታና ‹‹እንደራሴዎቻችን›› በፓርላማ የሚሟገቱት ለየቅል እየሆነ ነው፡፡
አጥንታችን ድረስ ዘልቆ ስለገባው የኑሮ ውድነት፣ በአከራይና በተከራይ መካከል መተዛዘንን ስላጠፋው የመኖሪያ ቤት እጦት፣ ቅጥ አምባሩ ስለጠፋውና እንደ ሰደድ እሳት ስለተስፋፋው ልመና፣ በየቀበሌውና በየመንደሩ ስለተንሰራፋው ወንጀል፣ በፍርድ መጓደል ምክንያት የፍትሕ ያለ ስለሚሉት ወገኖቻችን፣ ስለ መልካም አስተዳደር እጦትና የሰብዓዊ መብት መጓደል፣ ወደ ዓረብ አገሮች ስለሚሰደዱትና ስለሚሰቃዩት እህቶቻችን፣ ንፁኅንን በየሰዓቱ ስለሚቀጥፈው የትራፊክ አደጋ፣ የአገራችን መዲናና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ስለሆነችው አዲስ አበባ የፅዳት ችግር፣ ወዘተ. . . ቅድሚያ ተሰጥቶ ለምንድነው በፓርላማ ለውይይት የማይቀርቡት?
ይህም በመሆኑ ለዛሬ ብቻ ራሴን በ‹‹እንደራሴነት›› ሥልጣን ሾሜ የሚከተሉትን አቤቱታዎች ለተከበሩት ጠቅላይ ሚኒስትራችን አቤት እላለሁ፡፡
‹‹‘በካብ ላይ ብሠራ እባቡ መከራ፣ በዛፍ ላይ ብሠራ አሞራው መከራ፣ በምድር ላይ ብሠራ እረኛው መከራ፣ የት ውዬ የት ልደር አድር ብዬ’ አለች ወፍ››
ክቡር ሆይ አገራችንን በማዕበል እየተንገላታች እንዳለች መርከብ እያናወጣት ያለው ሙስና ወይም በእርስዎ ‹‹አሪፍ›› አገላጽ ‹‹ሌብነት›› ብቻ ሳይሆን (በነገርዎ ላይ አካፋን አካፋ ስላሉ ጌታ ይባርክዎ) ሕዝባችን ኑሮ ‹‹የእሳት ጥጃ›› እንደ ወለደችው ላም ዓይነት ሆኖበታል፡፡ በቅጡ እንዳይኖር እንደሚያውቁት ኢኮኖሚው እግር ተወርች ኮድኩዶታል፡፡ የታባቱ ለየትኛው ነፍሴ ነው እስከዚህ ድረስ ብሎ ደግሞ እስከወዲያኛው በራሱ እንዳይፈርድ፣ ነገ ሌላ ቀን ነው፣ ማን ያውቃል ያልፍልኝ ይሆናል በሚል ባዶ ተስፋ ዛሬን እንደ ምንም ይሻገራል፡፡ ግና ነገሩ ሁሉ አድሮ ጥጃ እየሆነ ነው፡፡ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ፣ በተለይም ለአዲስ አበባ ነዋሪ፣ ኑሮ ብርቱ የወይን ጠጅ ጠጥቶ መራመድ እንደተሳነው ሰው ሆኖበታል፡፡
ክቡር ሆይ  ለመሆኑ ‹‹ቁምሳ›› ወይም ‹‹አምስት አሥራ አንድ›› ስለሚባለው ጉዳይ ሰምተው ይሆን? ቁርስና ምሳን ባንድ ላይ የመብላት ጥበብ ነው፡፡ ኑሯችን ያስተማረን ዘዴ፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ‹‹ቁምራ›› በሚለው ቃል ተተክቷል፤ ቁርስ፣ ምሳና እራት አንድ ላይ መብላት ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ወይስ ?. . . ‹‹ልመና ያልተበላበት ኢንቨስትመንት››
ክቡር ሆይ! አንድ ጋዜጣ ላይ ነው አንዱ የገጠመውን እንዲህ ሲል ያሰፈረው፡፡ ‹‹ከታክሲ ስወርድ አንዲት አዛውንት ‹‹የኔቢጤ›› አየሁና ከታክሲ የተመለሰልኝን የመልስ ዝርዝር ሳንቲሞች ሰጠኋቸው፤ በኋላም አንድ ትንሽ ልጅ እየሮጠ ቀረበኝና …››
‹‹ጋሼ፣ ጋሼ ሁለት ጊዜ ተሸወዱ›› አለኝ፤
ግራ እየገባኝ፣ ‹‹እንዴት ?. . . ምን ማለት ነው?›› ብለው፣
‹‹ገንዘብዎን ሁለት ጊዜ ተበሉዋ›› ይለኛል፤
‹‹እኮ እንዴት?››
‹‹አንድም ለታክሲው ከፍለው፣ ደግሞም መልሱን ለየኔቢጤዋ ሰጥተው፤›› ሲለኝ፣
‹‹ታዲያ መሸወዴ የቱ ጋ ነው?›› ማለት፤
‹‹የተሳፈሩበት ሚኒባስ ታክሲኮ የራሳቸው ነው፤››
‹‹እኮ የማ?››
‹‹የየኔቢጤዋ የራሳቸው ነዋ፤››
‹‹እንዴት ሊሆን ይችላል?››
ባለታሪኩ በማመንና ባለማመን መካከል ሆኖ ወደ ጉዳዩ ከመሄድ በቀር ያደረገው አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡
አሁንማ ግራውንድ ፕላስና አፓርታማም እያላቸው አከራይተው የሚለምኑ ሰዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ ታዲያ ይኼን ወሬ ያቀበለኝ ሰው፣
‹‹ምክንያቱ ሌላ ነው›› ነው ያለኝ፡፡
‹‹ምንድነው ምክንያቱ ?››
‹‹ሱስ››
‹‹ምን?››
ምንም እንኳ በልመና ያለፈላቸውና እንደ መኪናና ቤት የገዙ ‹‹ነዳያን›› ቢኖሩም ቅሉ እንደ ሀሺሽ፣ ጫትና ሲጋራ ሁሉ ልመናም ሱስ ስለሆነባቸው ሥራዬ ብለው፣ ሐሩሩና ብርዱ  እየገረፋቸው መለመንን የሙጥኝ ያሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
ይሁንና ልመና አለቅጥ በመስፋፋቱ ምክንያት የከተማችን ነዋሪዎችና የውጭ ዜጎች በእጅጉ ተማረዋል፡፡ በቦሌ መስመር ብቻ እነርሱ ካጥር ጥግ ቁጭ ብለው ሕፃናት ልጆቻቸውን በልመና ‹‹ሥራ›› (ለመሆኑ ልመና ሥራ ነው እንዴ ?… ባንድ ወቅት ከትልቁ የመንግሥት ሚዲያ ‹‹በልመና ሥራ የተሰማሩ ዜጎች›› ሲል ስለሰማሁ ነው ቃሏን መጠቀሜ) ያሰማሩ እናቶች ቤት ይቁጠራቸው፡፡ አሁን አሁንማ ጤነኛ የሚመስለው፣ ሠርቶ መብላት የሚችለው ሁሉ መለመን ‹‹ፋሽን›› የሆነ ይመስላል፡፡
ጡት ያልጣለ ሕፃን በጉያቸው ይዘው በተሞላቀቀ አማርኛ ‹‹ነፍሱ ዳቦ መግዢያ ሙላልኝ›› የሚሉ ወጣት ሴቶችንም ማየት የዘወትር ገጠመኝ ነው፡፡
ታዲያ ‹‹ኧረ ይኼ ነገር ወዴት እየወሰደን ነው?›› ብዬ የጠየቅሁት አንድ ወዳጄ፣ ‹‹እባክህ ተወኝ ልመና የዘመኑ ያልተበላበት ኢንቨስትመንት መሆኑን ስላላወቅክ ነው፤›› ሲል ፈገግ አሰኝቶኛል፡፡
በዚህ ርዕስ ዙሪያ ሳስብ ሁሌ ሆዴን የሚበላኝ ነገር፣ ገና ከአሁኑ ትናንሽ እጆቻቸውን ወዳላፊ አግዳሚው በመዘርጋት የልመናን ሀሁ የተማሩት ጡት ከጣሉ አንድ ሐሙስ የሆናቸው ሕፃናት ናቸው፡፡ በተኮላተፈ አንደበታቸው ‹‹አባባ አባባ ለታቦ መግሺያ. . .›› ብለው፣ በልመና የሕይወትን አቡጊዳ ከጀመሩ መመረቂያቸው ምን ይሆን? ኧረ ይኼ ነገር መቋጫው የቱጋ ነው?
 በአንድ ወቅት ልመናን ታሪክ ለማድረግ በሚል ቆርጠው በመነሳት ቁጥሩን በውል የማላውቀው በርካታ ገንዘብ የሰበሰቡት ሰዎችስ ወዴት ገቡ? ያነገቡት ዓላማስ ከምን ደረሰ?
‹‹ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለው ዝነኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መቼ ይሆን የሚፈጸመው? በማለት ሳስብ ግራ ይገባኛል፡፡ ምክንያቱም በእኔ ዕድሜ ስለ አገራችን የተባለውና እየሆነ ያለው ለየቅል ስለሆነ፡፡ ሐውልታቸው ከአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ሕንፃ ቅጥር ግቢ የቆመላቸው ክዋሜ ንክሩማህ እንኳ ይኼንን ጥቅስ ቃል በቃል ከተናገሩት ግማሽ ምዕት አለፈኮ፡፡
‹‹ያማከሩት ዳኛ ያግዛል፣ የመተሩበት እጅ ይወዛል››
‹‹ሰው አይወድም በደል፣ ከብት አይወድም ገደል››
ክቡር ሆይ! መቼም ነገሬን እያረዘምኩብዎ እንደሆነ ይገባኛል፤ ግና ራሱን የሾመ ‹‹እንደራሴ›› አይደለሁ? የሕዝባችንን አቤቱታ ከአራት አንዱን እጅ እንኳ ላቀብልዎ ብዬ ነው፡፡
የዛሬን አያድርገውና በጥንት ጊዜ ቢሆንማ ኖሮ እንደርስዎ ያለ ያገር መሪ ተራ ሰው ተመስሎ፣ መናኛ ልብስ ለብሶ፣ በሕዝቡ መኸል ገብቶ ነበር አሉ፣ ሕዝቡ ስለ መንግሥቱ ያለውን ስሜት የሚያውቀው፡፡ በዚህ ዙሪያም ልጅ ሳለሁ አያቴ ጥቂት የማይባሉ ተረቶች ነግረውኛል፡፡ ይሁንና ዕንቁ ጊዜዎን ላለመሻማት ያህል ተረቶቹን በይደር ላቆያቸውና ወደ ሦስተኛው ትካሬ ልግባ፡፡
እንዲህ ነው የሆነው፡፡
ሐኪሙን፣ መሐንዲሱን፣ ያገር መሪውን፣ ጋዜጠኛውን፣ ወታደሩን፣ ወዘተ. . . ሁሉ የሚቀርፁ መምህራን ወዳጆች አሉኝ፡፡ ባንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምሩ፡፡
 ታዲያ እነኚህ ወጣት መምህራን በትምህርት ቤቱ አስተዳደር ስብዕናቸውን የሚነካ ነገር ተፈጽሞባቸውና በደል ደርሶባቸው በማያውቁት ነገር ከሥራ ይባረራሉ፡፡ እነርሱ እንደሚሉት የተባረሩበት ምክንያት ከዲሞክራሲ መብቶቻቸው አንዱ የሆነውን ማኅበር  በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በማቋቋማቸው ነው፡፡ ነገር ግን ለሠራተኛው የሚሟገት አካል ሲመጣ ደስተኛ ያልሆነው የትምህርት ቤቱ አስተዳደር አንዳችም ዓይነት ሥራ በማይገኝበት በክረምት ያለ ቤሳ ቤስቲን ከሥራ ያፈናቅላቸዋል፡፡
 መምህራኑም ጉዳዩን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት ያመራሉ፡፡ አንቀጽ ጠቅሰውም በፍትሕ አገር ግፍ እንደተዋለባቸው ያስረዳሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም ትምህርት ቤቱ ያባረራችሁ ማኅበር በመመሥረታችሁ አይደለም፤ ይልቁንስ በዚህ ምክንያት ነው እንጂ ብሎ እነርሱ የማያውቁትን ነገር ጭብጥ ያስይዛቸውና ለዚያ መልስ ይሰጡ ዘንድ ግድ ይላቸዋል፡፡
 መምህራኑም ከበቂ በላይ የሰው ምስክር ስለነበራቸው መልስ ይሰጣሉ፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ከመንፈቅ በላይ እሰጥ አገባና የፍርድ ቤት መመላለስ በኋላ፣ የፍርዱ ሚዛን ወደ ትምህርት ቤቱ አጋደለና የመምህራኑ ዕጣ እንባን ወደ ላይ ረጭቶ፣ ‹‹አንቺ እናታችን አንቺ ውዷ የእኛ፣ መች እናገኝ ይሆን ያልተዛባ ፍርድ እኛ?›› በማለት ማንጎራጎር ነበር፡፡
ክቡር ሆይ! እንዲህ ዓይነት በርካታ ታሪኮች ቢዘረዘሩ ጊዜውም ሆነ ሁናቴው አይመችም እንጂ ስንቱ ኢትዮጵያዊ በተዛባ ፍርድ ቁም ስቅሉን እያየና መፈጠሩን እየጠላ እንደሆነ ቢያዩ በእውነት ያዝናሉ፡፡ ‹‹በልቶ መጠጥ ያጣ ተበድሎ ፍርድ ያጣ›› እንዲሉ፡፡
‹‹ትናንት ልጄን ዛሬ እናቴን ምን ይበጃል ዘንድሮ አለ አውራ ዶሮ››
ክቡር ሆይ! ባለፈው ጊዜ አንዷ ወዳጃችን ገርጂ የሚገኙትን ዘመዶቿን ለመጠየቅ ታስባለች፡፡ ይሁንና ሥር በሰደደ የትራንስፖርት ችግር ምክንያት ጊዜው ላይን ያዝ ሲያደርግ ከስፍራው ትደርሳለች፡፡ ከታክሲ ወርዳ ወደ መንደሩ የሚያስገባውን ቀጭን የእግረኞች መንገድ እንደተያያዘችም ሁለት ሰዎች ይከተሏታል፡፡ ብርክ በያዛቸው እግሮቿ ፈጠን ፈጠን ስትል ሰዎቹም ፈጠን ሲሉ፡፡ ስትሮጥ ሲሮጡ፤ በመጨረሻም ብዙ ነገሮቿን የያዘውን ቦርሳዋን ‹‹ተረክበዋት›› ይሰወራሉ፡፡ እግዚሐር ይስጣቸውና አካላዊ ጉዳት አላደረሱባትም፡፡
እኔ ይህቺን አልኩ እንጂ እያንዳንዱ ነዋሪ ዕድል አግኝቶ ቢተነፍስ ተመሳሳይ የሆነው የወንጀል ታሪክ ቋት ሞልቶ ይተርፋል፡፡ በአንዳንድ የከተማችን አካባቢዎች ወንጀልና ወንጀለኞች እንደ አሸን በመፍላታቸውም ሕዝበ አዳም እንደ ዶሮ በጊዜ ወደ ቆጥ መስፈር የውዴታ ግዴታ ሆኖበታል፡፡ ቀጥሎ የሚፈራው የተደራጀ የወንጀለኞች ቡድን ከተማዋን ተቀራምቶ መውጪያ መግቢያ እንዳናጣ ነው፡፡
‹‹ሁለተኛ ግፌ ጫንቃዬን ተገርፌ ልብሴን መገፈፌ››
ክቡር ሆይ! ይኼኛውን ታሪክ ልብ ብለው ይስሙኝማ፤ እንዲህ ነው የሆነው፡፡ ልጅ እግሩ አባወራ አንዲት ሚስትና ለሥራ ያልበቁ አራት ልጆች አሉት፡፡ በአንድ የግል ክሊኒክ ውስጥ በጥበቃ ሥራ ያገለግላል፡፡ እፍኝ ከማትሞላ ደመወዝም ስድስት ራሱን ያስተዳድራል፡፡ አምላክ ያሳይዎ በአዲስ አበባ ኑሮ፣ ስድስት ራሱን በዚህች ደመወዝ ሲመራ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉሮሯቸውን ደፍነው ከሚያድሩበት ጊዜ ይልቅ ጦም ማደሩ ሲያይል፣ አውጥቶና አውርዶ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ውሳኔውንም ለትዳር አጋሩ አሳወቀ፤ የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ሚስትና የልጆቹን እናት ወደ ዓረብ አገር መላክ፡፡
 ለጊዜው መለያየቱ ቅስም ቢሰብርም፣ ያለ አጋር መክረሙ አጥንት ድረስ ዘልቆ ቢሰማም፣ ያለ እናት ኦና ቤት ማደሩ አንጀት ድረስ ዘልቆ ቢያምም፣ ጦም ውሎ ከማደር ይሻላልና ተስማሙ፡፡ የነገን ወፍራም ዳቦ እያለሙ፡፡ እንባ ተራጭተውም ተሰነባበቱ፡፡ አዎ ተበድሮና ተለቅቶ፣ ግማሽ አካሉን ወደ ዓረብ አገር ላከ ምስኪን ወንድማችን፡፡
ዳሩ ምን ይሆናል እንዳለመውና እንዳሰበው በግርድና የተገኘውን ዶላር ሳይሆን የልጅ እግሩ አባወራ ዕጣ ፈንታ ሬሳዋን መታቀፍ ነበር፡፡ ግማሽ አካሉ አገር ለቃ በሄደች በጥቂት ጊዜ ውስጥ በሄደችበት ጢያራ አስከሬኗ ተላከ፡፡ ‹‹የግፍ ግፍ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉም ሁለቱም ኩላሊቶቿ በቦታቸው አልነበሩም፡፡
አቤት ባይ በሌለበት ዓለም ላይ እንደመሆኑ ለማን አቤት እንደሚል ለጊዜው ያወቀው ነገር የለም፡፡ የአራት ልጆቹን እናት አስከሬን የሙጥኝ ብሎ ለያዥ ለገናዥ እስኪያስቸግር ድረስ ተንሰቅስቆ ከማልቀስ በቀር፡፡ ‹‹ወንድ ልጅ ብቻውን ነው የሚያለቅስ፤›› እንዲሉ እኚያ በሕይወት የተለዩን ሎሬት፣ ባለታሪካችንም የአጋሩ ትዝታ አንዴ በሥራ ቦታው፣ ሌላ ጊዜ ከማጀቱ፣ እንዲሁም በሕፃናቱ ብቻ በሄደበት ሁሉ እንደ ጥላ እየተከተለው መቆሚያና መቀመጫ አሳጥቶታል፡፡
ክቡር ሆይ! እንደ ሰበዝ አንዷን ብቻ መዝዤ እነሆ እንዲህም ዓይነት ጉድ አለ ለማለት ፈልጌ እንጂ፣ አገር ምድሩ በሞላ የተመሳሳይ ታሪክ ውጤት መሆኑን ለማወቅ ብዙ ጥናትና ምርምር አይጠይቅም፡፡ ‹‹ሰው አለ ወንዙ ብዙ ነው መዘዙ›› አይደል ያሉት አባቶች?
‹‹‘በጎዶሎ ቀን የገዛሁት ጋሻ፣ ሳያስገድለኝ አይቀርም’ አለ ፈሪ››
ክቡር ሆይ! በዚህች ጥቂት የሕይወት ዘመኔ እጅግ በርካታ የተባሉ የተሽከርካሪ አደጋዎች አይቻለሁ፡፡ ነገር ግን እንደ ጥቅምት 8 ቀን 2004 ዓ.ም. ከባህር ዳር ስመለስ በዓባይ በረሃ ያየሁትን ዓይነት የመኪና አደጋ ከቶም አይቼ አላውቅም፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ጉዳዩ ሰፊ ሽፋን አግኝቶ በመዘገቡ ለጆሮዎ አዲስ አይመስለኝም፡፡ እኔም በዓይኔ በብረቱ በማየቴ ‹‹ማን ያውራ? የነበረ፤ ማን ያርዳ? የቀበረ፤›› እንዲሉ፣ ጉዳዩን ከማንም በላይ አሳምሬ መተረክ እችላለሁ፡፡ ይሁንና አገር ያወቀውን ፀሐይ የሞቀውን ጉዳይ ለማመንዠክ ሳይሆን ዓላማዬ፣ በመላው አገራችን በየሰዓቱ ልዩነት ስለሚፈጠረው የተሽከርካሪ አደጋ አንዳች የሚፈይድ ነገር ምን እየታሰበ ነው? ለማለት ፈልጌ እንጂ፡፡
ዘወትር ማለዳ ወደ ሥራዬ ስሄድ በአዲስ አበባ በ24 ሰዓታት ውስጥ ስለተከሰቱት የትራፊክ አደጋዎች በየሬዲዮው የትራፊክ ፖሊስን ቃል አቀባይ ‹‹መርዶ›› ስሰማ፣ ነገስ ማን ይሆን ተረኛው? እንዳልኩ ሁሌ ራሴን እንደጠየቅኩ ነው፡፡ ‹‹ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ›› መሆንን ማን ይወዳል?
አቤት በየቀኑና በየሰዓቱ በመላው አዲስ አበባ ስንቱ ጠቃሚ ዜጋ በሰው ሠራሽ መኪና አደጋ እስከወዲያኛው እያሸለበና በከባድ የአካል ጉዳት እየማቀቀ እንደሆነ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ይቁጠረው፡፡
የሆነው ሆኖ  ‹‹ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል›› እንዲሉ እኔም  ጉዳዬን እዚህ ላይ ጨርሻለሁ፡፡ ምናልባት ግን ክቡርነትዎ ይህን ያቤቱታ ጽሑፍ አንብበው ከሆነ እንደ ግለሰብና እንደ አገር መሪ ምን ብለው ይሆንየእውነት ለመናገር ክቡርነትዎ በብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ሥራዎች ባይወጠሩ ኖሮ የምጠይቅዎ ብዙ ጉዳይ ነበረኝ፡፡ ለዛሬ ግን አንኳር አንኳሩን ካነሳሁ ይበቃኛል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስለ ዲሞክራሲ መብቶች፣ ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ መልካም አስተዳደር፣ ስለ ዜግነት ክብር፣ ወዘተ የማነሳቸው ጥያቄዎች ይኖሩኝ ይሆናል፡፡ 
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡

(ይህ  ፅሁፍ በሪፖርተር ጋዜጣ ፣ ረቡዕ ዕትም፣ የካቲት 7፣ 2004 ዓ.ም የወጣ ነው፡፡)

No comments:

Post a Comment

ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡