አንድ
ጊዜ አንድ ወዳጄ ያጫወተኝ ገጠመኝ ነው፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ አንዱ የሆነ አካባቢ እየሄደ ሳለ ገና ከጉዳዩ ሳይደርስ ሆዱን ክፉኛ ያመዋል፡፡ በነበረበት አካባቢ አንዳችም የሕዝብ መፀዳጃ ቤት የሚባል ነገር የለም፡፡ በእርግጥ ሆቴሎችና ቡና ቤቶች የነበሩ ቢሆንም እዚያ ገብቶ አንዳች የሚበላም ሆነ የሚጠጣ
ነገር አዞ ፊኛውን የሚያቀልበት ቤሳ ቤስቲን የለውም፡፡ ጉድ ፈላ! በድንገት በጠላት እንደተፈታ ከተማ ሆዱ ተሸበረ፤ የት ሄዶ ይተንፍስ? እምን ውስጥ ገብቶ እፎይ ይበል? ጫካ የለ፣ ጉድባ የለ፣ ሰርጥ የለ፣ ብቻ ወዲህ ቢያይ ግዙፍ የመንግሥት መሥርያ ቤት፣ ወዲያ ቢያይ የግል ድርጅት፣ ወዲህ ቢል ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ፣ ወዲያ ቢያይ በሰዎች የተሞላ ካፌ፤ የሆዱን ጉድ የሚገላገልበት ቦታ ፈጽሞ አልነበረውም፡፡ በመጣበት እግሩ ወደራሱ መኖርያ ተመልሶ ነፍሱን ሊዘራ ቢሞክርም፣ እንደ ደራሽ ወንዝ የሆነበት ታችበሌ ፋታ የሚሰጠው አልሆነም፡፡ “ጉዲ ሰዲ!” ይሏል እዚህ ላይ ነው እንግዲህ፡፡
ዘርቶ
በቃመባት፣ ወልዶ በሳመባት አገር በመፀዳጃ ቤት እጦት ብቻ ሊዋረድ? ጡጦ እንዳልጣለ እንቦቀቅላም ሊበላሽ ሲሆንና የአገር ቡና መጠጫ መሆኑ ሲገባው እንዲህ አደረገ፡፡ ማዶ ወደነበረው ግዙፍ ድርጅት ሕንፃ አጥር ሥር ጠጋ አለና ዓይኑን ጨፍኖ ቀበቶውን ፈታ፤ ይዞት የነበረውንም ጋዜጣ በመዘርጋት ፊቱን ሸፍኖ. . (የተቀረውን ታሪክ አንባቢያን ጨርሱት፡፡)
የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና ብቻ ሳትሆን የአኅጉራችን የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባችን ፅዳት የዕለት ተዕለት ችግር ከሆነ ዘመናት ሄደው ዘመናት መጡ፡፡ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎቿም ሰርክ በማለዳ ተነስተን ወደየትካራችን ስንሄድ፣ በየአደባባዩና አውራ ጎዳናው፣ በየታዛውና ፌርማታው፣ በየጥጋጥጉና ስርጓጉጡ፣ ኧረ ምኑ ቅጡ ሳንወድ በግድ የምናየውን ጉዳንጉድ፣ ምገን የምንተነፍሰውን የተበከለ አየር፣ ፅዱ መሬት ፍለጋ እንደ መሰናክል ሯጭ አትሌት የምንሆነውን ሁሉ ቤት ይቁጠረን፡፡
ውብና
የቅንጦት መኪኖችን ከሥሩ ካስጠለለ ሰማይን ከሚታከክ ዘመናዊ ሕንፃ ሥር፣ ወይም በእግረኞች መሀል መንገድ ላይ፣ አሊያም ከሕዝብ መናፈሻ አረንጓዴ ሳር ላይ፣ ፌርማታ ወንበር ላይ፣ ጭሱ እየተንቦለቦለ፣ እንደ አንዳች ጠረን በአፍንጫዎ የሚሰርገው “መዓዛ” የበሉትን ምግብ “ካልወጣህ” ብሎ ግድ ሲል፣ ኧረ ስንቱ ጉድ እቴ!
በምኖርበት ሠፈር (ዝነኛ ሠፈር፣ ታላላቅ ሕንፃዎች፣ የመገበያያ ቦታዎች፣ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች፣ ወዘተ ባሉበት) ዘወትር ብዙ ሕዝብ ወደየምግባሩ የሚሄድበት አንድ ዕድለ ቢስ መንገድ አለ፡፡ ከመንገዱ ግራና ቀኝ ደግሞ የመኖርያ ቤቶች አሉ፡፡ የተወሰኑት ሥሩ ሁሌ በሚወረዛ የግምብ አጥር ሲታጠሩ፣ የተወሰኑት ደግሞ መላ አካላቸው ያልፎሂያጅ ሽንት በበጣጠሰው ቆርቆሮ የታጠሩ ናቸው፡፡ እንግዲህ ከዋናው አስፓልት መንገድ ከታክሲ ወርደን ወደ መኖርያ ቤቶቻችን ስናቀና በዚያ መንገድ ማለፍ የግድ ነውና፣ የቻለ ወይ እየሮጠና እየዘለለ፣ ያልቻለ ደግሞ ወይ በነጠላዋ አሊያም በሸሚዙ ክሳድ አፍንጫውን አፍኖ አንዳች ነገር፣ እርግማን ይሁን ምርቃት ያልለየ ነገር፣ እያልጎመጎሙ መጓዝ ነው፡፡
ታዲያ
ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ይሆናል፡፡ በአጋጣሚ እኔ በዚያ “የማያልፍለት መንገድ” እያለፍኩ ነበር፡፡ ሁለት ወጣቶች በመጠጥ ናላቸው የዞረ የሚመስሉ፣ ከቆርቆሮው አጥር ተጠግተው ፊኛቸውን እያቀለሉ ሳለ፣ ያልጠበቁት የእጣቢ ዝናብ ከግቢ ነዋሪዎች ተበርክቶላቸዋል፡፡ ለኃጢያን የመጣ እንዲሉም፣ እኔ ከደሙ ንፁህ የሆንኩት ሳልቀር ከጠበሉ ደርሶኛል፡፡
ኧረ
ለመሆኑ መቼ ነው ጎበዝ የአዲስ አበባና የፅዳት ፍጥምጥም የሚሆነው?
አንድ
ጊዜ ወላጆቹን አውቃቸው የነበሩ አንድ ሆላናዊ ሕፃንን እንዲህ ስል ጠየቅኩት፤ “How did you get Addis
Ababa?” በውስጤ
እንደ ወላጆቹና ሌሎቹም ፈረንጆች “Wow Addis Ababa is a
beautiful city with a hospitable people. Really I liked it so much. . .” ይለኛል ብዬ ተስፋ ሰንቄ፡፡
መቼም
ትልቅ ሆነው፣ አዋቂ ተብለው፣ ሕፃን መሆን ሳይሆን እንደ ሕፃን መሆን ጥሩ ነውና፣ ደግሞም መጽሐፉ “እንደ ሕፃን ካልሆናችሁ መንግሥተ ሰማይን አትወርሱም” ሲል ደምድሟልና፡፡ ያ ሕፃን በጣፋጭ አንደበቱ “. . .Dirty!” ቢለኝ ከመቅጽበት ጭራዬን ሸጉጬ ከአካባቢው እብስ አልኩ፡፡
ስለ
ናይሮቢ አሊያም ስለ ጆሐንስበርግ ወይም ስለሌላው ከተማ ፅዳትና ውበት በዓይን በብሌናቸው ያዩ ሰዎች “በናይሮቢ አስፓልት ላይኮ እንጀራ አንጥፈህ ወጥ እየጠከስክ መብላት ትችላለህ፤” ሲሉ ይሰማል ብዙ ጊዜ፡፡ ምንም እንኳ ሄጄ ባለየውም፡፡
ወይ
አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ፣
አንቺም በቆሻሻ
ትታሚያለሽ ወይ?
የሚልን ዝማሬ መቼ ይሆን የምንሰማው
ከፀዱት መንገዶች
ላይ እህል የምንበላው?
ወይ
በሰንበት አሊያም በጥምቀት ካልሆነ ባሻት ሰዓት ከከንፈር ወዳጇ ጋር እንዳትገናኝ በቤተሰቦቿ “ማዕቀብ” እንደተጣለባት ልጃገረድ፣ ክፉ ልማድ ሆኖብን የአዲስ አበባ ፅዳት ጉዳይ ብዙውን ጊዜ በወርኃ ህዳር በ“ህዳር ሲታጠን” ወይም የአፍሪካ መሪዎችና የዓለም እንግዶች ሊመጡ አንድ ሐሙስ ሲቀረው መሆኑ ዘወትር ሆዴን ይበላኛል፡፡
ዘወትር ማለዳ መንገድ ጠራጊዎች የከተማዋን ዋና ዋና ጎዳናዎች ማፅዳታቸው እሙን ነው፡፡ ቢሆንም ይኼ ጉዳይ ሁልጊዜ ማለዳ ማለዳ ፊቷን እየታጠበች፣ ነገር ግን የተቀረ አካሏን “ኤዲያ ፊቴን ከታጠብኩ ይበቃኛል” ብላ ቸል እንዳለች ሰነፍ ሴት ከማስመሰል አያግደውም፡፡
ኑሮውን አሜሪካ
ያደረገ አንዱ የእኛ ሰው የገጠመውን ነገር ሲያወራ ውስጤ የቀረ አንድ ነገር አለ፡፡ በ“ሃይዌይ” መንገድ ላይ ጣፋጭ ብስኩት እየኮረሸመ መኪናውን እየጋለበ ነበር በአንድ ወቅት፡፡ በአንድ ነጭ ሰውዬ የምትሽከረከር መኪናም በአገር አማን ጥሩምባዋን እያንባረቀች የእኛን ሰው ትከተለዋለች፡፡ የእኛ ሰው ደግሞ ምን ጉድ መጣብኝ ብሎ ፖሊስ የሚከተለው መስሎት ምን አንዳች ጥፋት ሠርቼ ይሆን? እያለና ፍጥነቱን እያቀዘቀዘ ሁኔታውን ለማወቅ ፈለገ፡፡ ነጩ ሰውዬ እንደ ጠበቀው ፖሊስ ሳይሆን ይልቁንስ አካባቢ በቆሻሻ ሲበከል እንቅልፍ የሚነሳው ተቆርቋሪ ዜጋ ነበርና “ስማ የእኔ ወንድም መኪናህን አዙረህ የጣልካትን ቆሻሻ ቶሎ ብለህ አንሳ” ይለዋል፡፡
ለካንስ “የቤት አመል” እንዲሉ ብስኩቱን ከኮረሸመ በኋላ እንደ ዘበት በመኪናው መስኮት አሽቀንጥሮ የጣለው የብስኩት ልጣጭ እዚያ አገር በዋዛ አይታለፍም ኖሯልና ጣጣ አመጣበት፡፡ ንፅህና ባህሉ የሆነ ሕዝብ እርሱ ምስጉን ነው ማለት ይኼኔ ነው፡፡
ስለገዛ ንፅህናው
ግድ የሌለው ሰው ስለአካባቢው መበከል ደንታ አይሰጠውም፡፡ ለመሆኑ እነዚያ በአንድ ወቅት ጋሽ አበራ ሞላን ተከትለው በመላው አዲስ አበባ እንደ አሸን ፈልተው የነበሩትና ዝማሬያቸው ሁሉ “ፅዳት፣ ፅዳት” የነበረውን ወጣቶች ምን ዋጣቸው? መፈክራቸው ብዙ ነበር፡፡ አንዳንዱ አስተማሪ፣ አንዳንዱ አስፈራሪ፣ ሌላው አሳፋሪ፡፡ ለምሳሌ “ፅዳትን ከድመት እንማር”፣ “ከምትሸናበት አፅድተህ ተኛበት”፣ “ዋ ትሸናና ትሸነሸናለህ!”፣ “በየግንቡና አጥር ሥር የሚሸና ውሻ ብቻ ነው”፣ ወዘተ የሚሉ ነበሩ፡፡ ኧረ ሲፀዳዳ የተገኘን ሰው አምስት ብር አስከፍለው “ቢል” የሚሰጡም የተደራጁ ወጣቶች እንደነበሩ ትዝ ይለኛል፡፡
ታዲያ
በዚያን ጊዜ ነው አሉ አንዱ ፊኛው የተወጠረ አልፎ ሂያጅ ሊተነፍስ ሱሪውን ቢያላላ ፊት ለፊቱ ካለው ግንብ ላይ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ያነባል፡፡ “በየግንቡና በየአጥሩ ሥር የሚሸና ውሻ ብቻ ነው” ይላል፡፡ ሰውዬው ጽሑፉ ብዙም ግድ ሳይሰጠው፣ ደግሞም ሳይፈራና ሳያፍር፣ “ታዲያ ለዛሬ ውሻ ብሆን ምን ይለኛል?. . ምንም” ብሎ ራሱን ጠይቆ ደግሞም ለራሱ መልስ ሰጥቶ ተግባሩን አከናውኖ ሄዷል ተብሎም ሰምተናል፡፡
የሆነው ሆኖ ሕዝብ በብዛት በሚገኝበት፣ በሚገባና በሚወጣበት አካባቢ ደረጃውን የጠበቀ መታጠቢያ ቤት ያለው መፀዳጃ ቤት ተሠርቶ ዜጎች ወይ በነፃ አሊያም ኪስን በማይጎዳና ማንኛውም ኅብረተሰብ ያገልግሎቱ ተጠቃሚ በሚሆንበት መልኩ አገልግሎት የምናገኝበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የሚመለከተው አካል እንዲህ ቢያደርግ በአንድ ድንጋይ ከሁለት በላይ ወፎች የመግደል ያህል ይመስለኛል፡፡ አንድም በመፀዳጃ ቤት እጦት ምክንያት በያገኝበት ለሚፀዳዳው የኅብረተሰብ ክፍል እፎይታ ይሰጣል፤ ብሎም ለሥራ አጥ ወገኖች የሥራ ዕድል ይከፍታል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አዲስ አበባችን ትፀዳለች፡፡
“ያልተራበ ስለ ረሃብ አያውቅም” ነውና ብሂሉ በንፁህ አካባቢ ለሚኖር ሰው ስለቆሻሻ መንደር ሺሕ ጊዜ ቢነግሩት መደናቆር ነው ትርፉ፡፡
ለመሆኑ መሪዎቻችን
ይህን ጉዳይ አይተውት
አሊያም ሰምተውት ምን አሉ? እንደ ነዋሪው የአማርኛውን “ጉድ!” ብለው እጃቸውን ባፋቸው ላይ ጫኑ? ወይስ የእንግሊዝኛውን “ጉድ” ተጠቅመው ከንፈራቸውን አሸርምመው፣ “ጉዳዩን ሰምተናል፣ አይተናል፣ አንድ ቀን መፍትሔ ይፈለግለታል አሉ?” ማነው ስለዚህ ጉዳይ የሚገደው? ለመሆኑ ይህች ከተማ የማናት? ሰምታችኋል ቻይኖቹ ያሉትን? ያንን የቀለበት መንገዱን በሚሠሩበት ሰሞን ቀን ያጠሩት የብረት አጥር ሌሊት ተቆርጦ ሲዘረፍ፣ እንዲህ አሉ አሉ፣ “ቆይ ለመሆኑ እናንተ ኢትዮጵያውያን ሌላ አገር አላችሁ እንዴ?” አዲስ አበባችን የእኔ፣ የአንተ፣ የአንቺ፣ የእናንተ፣ የእነሱ፣ በአጠቃላይ የእኛ አይደለችምን? ነው ወይስ በዓለም የአየር ንብረት መለወጥ ምክንያት የበለፀጉት አገሮችን ተጠያቂ እንዳደረግን አሁንም ለከተማችን የአየር ብክለት እነርሱኑ እንወንጅል?
ጨለማን ተገን አድርገን፣ አሳቻ ሰዓት ጠብቀን፣ ከማጀታችን ያጠዋነውን ጉድ፣ ከጎረቤታችን ደጃፍ ስናዥጎደጉድ፣ ባለፍንበትና ባገደምንበት ቦታ ሁሉ ቀበቷችንን ስናላላ፣ እኛና ንፅህና እንደ ሰማይና ምድር ተነፋፍቀን ለቀረንበት ማነው ተጠያቂው?
እናንተስ መንግሥትና
ሕዝብ አደራ ብሎ በቦታው ላይ ያስቀመጣችሁ አካላት፣ ስም ብቻ ተሸክማችሁ በየወሩ ደመወዝ የምትልጡ፣ አንዳችም የሚፈይድ ሥራ መሥራት ያልቻላችሁና የተበጀተውን በጀት እንዲያው በከንቱ የምታባክኑ እናንተ፣ ጆሯችሁ ላይ የተኛችሁ፣ ዓይናችሁን ያሠራችሁ እናንተ ምን አላችሁ?
በአዲስ አበባ የተበላሸ የፅዳት ይዞታ ምክንያት የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነትን እንጣ እንዴ? ለአፍሪካ ኅብረትና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች መዲና የሆነችው አዲስ አበባችን የኒውዮርክና የብራሰልስን ዓይነት ክብር መታደል ሲገባት በፅዳት መጓደል ምክንያት የሚከተለውን ለምን መገመት ያዳግታል? “ቆሻሻዋና አቧራማዋ ከተማ” እየተባለች በምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች የምትብጠለጠለውን አዲስ አበባን ከእንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ጉድ ውስጥ ማውጣት ካቃተን ውጤቱን በቅርቡ እናየዋለን፡፡
በቅርቡ ለአገሯ
የበቃችው አንዲት ዳያስፖራ ሚዲያ ላይ ስታወራ የሰማሁትን አክዬ ላብቃ፡፡ ባህር ማዶ እያለች የወለደችው ልጇ አገሩ ሲመለስ ወገኖቹ በያገኙበት የሚፀዳዱ ግብዝ መሆናቸውን ልብ ብሎ ኖሮ፤ “ከአህያ የዋለች ጊደር ምንትስ ትማራለች” እንዲሉ፣ እሱም ከዕለታት አንድ ቀን ትንሽዬ ፊኛውን ሊያላላ ከመንገዱ ጥግ ሄደ፡፡
እናቱም “እንዴ ማሙሽ ምን ልታደርግ ነው?”
“ልሸና ነዋ”
“ምናልክ አንተ? እንዲያ ነው ሥርዓቱ? እንዲያ ነው ትምህርት ቤት ያስተማሩህ?”
“እንዴ ማሚ ምነካሽ ያለንበት አገርኮ አሜሪካ አይደለም፡፡”
“Who
cares Mom? We, after all, are not in America” (እንዲህ ይሆን ያላት አፉን በፈታበት ቋንቋ?)
አበቃሁ፡፡ አስተዋይ ልቡና ይስጠን፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
(ይህ ጽሁፍ የካቲት 4፣ 2004 ዓ.ም በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ‹‹እኔ የምለው›› ዓምድ ላይ የወጣ ነው፡፡)
No comments:
Post a Comment
ብዙ ሰዎች አስተየያየት ለመስጠት እንደተቸገሩ ነግረውኛል፤ ነገር ግን ምናልባት ባማራጭነት ከቀረቡልዎ አካውንቶች መካከል እርስዎ የትኛውም ከሌለዎ Comment as Anonymous የሚለውን በመጠቀም በቀላሉ አስተያየትዎን መስጠት ይችላሉ፡፡